ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ድርድር ያለ ውጤት በመጠናቀቁ ሱዳንና ግብፅ አዲስ የድርድር አማራጭ ከሰሞኑ እያቀረቡ ናቸው።
ከሱዳን መንጭቷል የተባለው አዲስ የድርድር አማራጭ በግብፅ መንግሥት በኩልም ሙሉ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በቅርቡ ሱዳንን በጎበኙበት ወቅት በይፋ ተናግረዋል።
በሱዳን የቀረበው አዲሱ አማራጭ አራት አሸማጋዮች የሚሳተፉበት ድርድር የሚጠይቅ ነው፡፡ እነሱም የአሜሪካ መንግሥት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ናቸው።
በግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር ላይ ሦስቱ የጉዳዮ ባለቤት የሆኑት አገሮች ድርድር በሚያደርጉበት ወቅት የሚፈጠሩ ልዩነቶችን የተጠሩት አካላት ጣልቃ ገብተው፣ በማሸማገል አስታራቂ የመፍትሔ አማራጭ እያቀረቡ የሦስቱ አገሮችን ልዩነት እንዲፈቱ የታለመ ነው።
ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመርያ የውኃ ሙሌት ለማካሄድ ዕቅድ በያዘችበት በ2012 ዓ.ም. ተመሳሳይ የድርድር ጥድፊያ በግብፅ መንግሥት በኩል እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህም የአሜሪካ መንግሥት በዋናነት፣ እንዲሁም የዓለም ባንክ በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ ያደረገችውን ጫና የኢትዮጵያ መንግሥት በየዋህነት ተቀብሎ ሲሳተፍበት እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
በዚህ የአሜሪካ መንግሥት ሚዛናዊ ያልሆነ ተፅዕኖ በጎላበት ድርድር የኢትዮጵያ መንግሥትን የመጠምዘዝና ከዚያ አልፎም የማስፈራራት ድርጊት በአሜሪካ መንግሥት በኩል ሲፈጸም እንደነበር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ ከነበረው ድርድር በስተመጨረሻ ላይ ራሱን ካገለለ በኋላ በይፋ ገልጾታል።
የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በወቅቱ የነበራቸው ሚና ድርድሩን የመታዘብ ቢሆንም፣ በሒደት ግን በተለይ አሜሪካ ራሷን በአደራዳሪነት ከመሰየም አልፋ ሦስቱ አገሮች ስምምነት የሚያደርጉበትን ሰነድ እስከ ማርቀቅ ደርሳ እንደነበር በወቅቱ በድርድሩ ይሳተፉ የነበሩ አንድ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ለሪፖርተር ገልጸዋል።
በወቅቱ በነበረው ድርድር የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በአሸማጋይነት እንዲገቡ ጥያቄ ሲቀርብ የኢትዮጵያ መንግሥት በየዋህነት ጥያቄውን መቀበሉ ስህተት ነበር የሚሉት እኚህ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል፣ በወቅቱ ድርድሩን እንዲታዘቡ ቢፈቀድም አሜሪካ በቀጥታ ግልጽ የወጣ ወገንተኝነት ማሳያቷን ያስታውሳሉ።
የዓለም ባንክ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ የሚነሱ ውዝግቦችን ለመፍታት የሚያስችል ልምድም ዕውቀትም እንዳለው ይታወቃል የሚሉት ተደራዳሪው፣ በወቅቱ ከዓለም ባንክ የተወከሉት ባለሙያዎች በአሜሪካ ተፅዕኖ ሥር ወድቀው ነበር ይላሉ።
‹‹የዓለም ባንክ በራሱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ አድልኦ የለበትም ማለቴ ሳይሆን፣ ቢያንስ አድሎአቸውን ሊገልጹ የሚችሉት በቴክኒካዊ ልባስ ተሸፍኖና ለእውነት የቀረበ መስሎ ይሆን ነበር ለማለት ነው። ነገር ግን የባንኩ ተወካዮች በአሜሪካ መንግሥት በድርደሩ እንዲሳተፍ በተሰየመውና ከባለሥልጣናት ቀጭን ትዕዛዝ እየተሰጠው ይሳተፍ በነበረው የአገሪቱ የገንዘብ ተቋም ተፅዕኖ ሥር ወድቀው የነበረ በመሆኑ ሚና አልነበራቸውም ማለት ይቻላል፤›› ብለዋል።
በስተመጨረሻ ኢትዮጵያ ከዚህ ኢፍትሐዊ ድርድር ራሷን ስታገል የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኢትዮጵያ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የግድቡን የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌት ማከናወን አትችልም የሚል መግለጫ በይፋ ማውጣቱ፣ በአገሪቱ መንግሥት በኩል ተይዞ የነበረውን ዓይን ያወጣ አድልኦና ጫና ቁልጭ አድርጎ እንዳሳየም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግሥትን ማስፈራሪያ አዘል መግለጫ ወደ ጎን በማለት የመጀመርያውን ዙር የመጀመርያ ዓመት የውኃ ሙሌት በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. ማከናወኗ በርከት ያለ ጩኸት አስከትሎ የነበረ ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግሥትም ይህንኑ ምክንያት በማድረግ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ድጋፍ ውስጥ የተወሰነውን ማገዱን አስታውቋል።
በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በህዳሴ ግድብ ላይ ይደረግ የነበረው የሦስቱ አገሮች ድርድር ያለውጤት እንዲጠናቀቅ ሁለቱ አገሮች የያዙትን አቋም የተረዳችው ኢትዮጵያ፣ ድርድሩ ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ በነበረው ሳምንት ለሱዳንና ለግብፅ መንግሥታት፣ እንዲሁም ለአደራዳሪው የአፍሪካ ኅብረት በጻፈችው ደብዳቤ ድርድሩ ውጤት ባያመጣም አሁንም በድርድር ልዩነቶችን ለመቅረፍ እንደምትሠራና የህዳሴ ግድብ የመጀመርያ ዙር ሁለተኛ ዓመት የውኃ ሙሌት በ2013 ዓ.ም. ክረምት እንደምታካሂድ አስታውቃለች።
ቀድሞውንም ቢሆን ኢትዮጵያ የመጀመርያውን ዙር የሁለተኛ ዓመት የውኃ ሙሌት ዘንድሮ እንደምታከናውን የሚረዱት ግብፅና ሱዳን፣ ይህ ከመሆኑ በፊት ባቀረቡት አዲስ የድርድር አማራጭ የአውሮፓ ኅብረትንና ተመድን አጃቢ በማድረግ የአሜሪካ መንግሥትን ዳግም ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የህዳሴ ግድብን አጀንዳ ወደ አፍሪካ ኅብረት ያመጡት ለአንድ ዓመት ያህል የኅብረቱ ሊቀመንበር የነበሩት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲራል ራማፎዛ የሊቀመንቀርነት ቆይታቸው እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2021 የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በአፍሪካ ኅብረት ሥር ይካሄድ የነበረው የህዳሴ ግድብ ድርድርም በዚሁ ወር ነበር ያለ ውጤት የተጠናቀቀው።
የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት በኅብረቱ ሥር ይደረግ የነበረውን ድርድር ለማስቀጠል ምንም ዓይነት ፍላጎትም ሳያሳዩና ኢምንት ጥረት ሳያደርጉ፣ ሱዳንና ግብፅ በጋራ ያቀረቡት አዲስ የድርድር አማራጭ በመቀበል ኢትዮጵያ ወደዚህ ድርድር እንድትመጣ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንገድ ምን ሊሆን ይችላል?
በህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት መከናወን ጋር ተያይዞ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ከሚያደርገው ድጋፍ ውስጥ ከፊሉን ያገደ ቢሆንም፣ አዲሱ የአሜሪካ አስዳደር ለኢትዮጵያ እንዳይሰጥ የታገደው ድጋፍ ከህዳሴ ግድብ ጋር መያያዝ የለበትም በማለት ባለፈው የካቲት ወር 2013 ዓ.ም. መወሰኑን አስታውቋል።
ይህ ቢሆንም በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ በተለይም ከትግራይ ክልል ሰብዓዊ ቀውስ ጋር እንዲተሳሰርና ድጋፉም ሁኔታዎች እስኪሻሻሉ ድረስ ታግዶ እንዲቀጥል ወስኗል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ ከሁለት ሳምንት በፊት በተደረገ የበይነ መረብ ውይይት ወቅት የአሜሪካን አቋም በተመለከተ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አመራሮች ጋር ከቀናት በፊት የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸውንና በግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን ተናግረዋል።
የታገደው ድጋፍ ከግድብ ጋር እንዳይያያዝ መወሰናቸውን፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ባለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት ዕገዳው እንዳልተነሳና ድጋፉ የሚለቀቅበትን ፕሮጀክት ልየታ በተመለተከ ምክክር እያደረጉ ስለመሆኑ እንዳስረዷቸውም ጠቁመዋል።
‹‹ህዴሴ ግድብን በተመለከተ አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ከበፊቱ አስተዳደር የተለየ እንደሆነ እያየን ነው፤›› ያሉት አምባሳደር ፍፁም፣ ‹‹ነገር ግን ቸኩለን መደምደም አንችልም፤›› ብለዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን በበኩላቸው የአሜሪካ መንግሥት ይህንን መወሰኑ ጥሩ ጅማሮ ነው ማለቱ አይጎዳም ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ነገሩን በጥልቀትና በዓውዱ መመልከት ካልቻለች ስህተት ሊያመጣ እንደሚችል ያሳስባሉ።
‹‹አሜሪካ ያቋረጠችውን ድጋፍ ከህዳሴ ግድብ ጋር እንዳይገናኝ ያደረገችው በአንድ በኩል የቀደመ ስህተቷን ለማረም፣ በሌላ በኩልም ደግሞ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር የውጭ ፖሊሲ ገለልተኛና ሚዛናዊ ነው የሚል የበግ ለምድ አለመሆኑንም ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤›› ሲሉም አሳስበዋል።
ግብፅና ሱዳን እያቀረቡት ያለውን የአራትዮሽ ሽምግልና ጥሪ ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ባወጣው የፖለቲካ አቋም መግለጫ (Conclusion) ውስጥ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብን የተመለከተ አቋም ተንፀባርቋል።
በመግለጫውም፣ ‹‹የአውሮፓ ኅብረት ሲደረግ በነበረው ድርድር የአውሮፓ ኅብረት በታዛቢነት ሲሳተፍ ቆይቷል፣ አሁንም የአውሮፓ ኅብረት ድርድሩን እንዲያግዝ አስፈላጊ ነው ብለው ሁሉም ወገኖች ካመኑበት ኅብረቱ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል፤›› ብሏል።
የአውሮፓ ኅብረት ባወጣው በዚህ በመግለጫው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በቀጣይ በሚደረገው ድርድር ተሳታፊ ለመሆን ፍላጎቱን በግልጽ ያሳየ ሲሆን፣ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ያቋረጡትን ድርድር በማስቀጠል ሦስቱንም አገሮች በእኩል ተጠቃሚ የሚዳደርግ ዘላቂ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እንደሚያበረታታም አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተመሳሳይ አቋም ከአሜሪካ መንግሥት የተሰማ ሲሆን፣ ይኸውም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ለአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ፊት ቀርበው በተጠየቁበት ወቅት ሲመልሱ የተደመጡት ነው።
የቋሚ ኮሚቴው አንድ አባል ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሦስቱ አገሮች መካከል ያለው አለመግባባት እንዲፈታ አሜሪካ ምን ዕገዛ ልታደርግ እንደምትችል ጥያቄ የቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ፣ ‹‹ሦስቱ አገሮች በጋራ ሆነው ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱና ግጭትን እንዲያስወግዱ፣ አሜሪካ የተቻላትን ሁሉ ታደርጋለች፣ ለዚህም ያሏትን አስፈላጊ ተቋማቶቿን ትጠቀማለች፤›› ብለዋል።
በመሆኑም ከአውሮፓ ኅብረት በተጨማሪ አሜሪካም በህዳሴ ግድብ ቀጣይ ድርድር ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላት መሆኑ ግልጽ ሆኗል። የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበርም በግብፅና ሱዳን በኩል የቀረበውን የድርድር አማራጭ ደግፈው የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ አዲሱ የድርድር አማራጭ እንዲመጣ ሁለት ጊዜ ልዑካኖቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ መላካቸው ታውቋል።
ከላይ የተጠቀሱት እንቅስቃሴዎች በቀጣዮቹ ሳምንታት ተጠናክረው በጫና መልክ እንደሚመጡ የሚያመላክቱ ናቸው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚመጣውን ጫና ለመቋቋም ምን ያህል ዝግጁነትና ቁርጠኝነት አለው የሚለውም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሚያነሱት ጉዳይ ሆኗል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በበይነ መረብ በተደረገ ውይይት ይኸው ጉዳይ ተነስቶ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ውይይት ላይ ንግግር ያደረጉት የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግሥት የቀደመ ስህተቱን እንደማይደግም አስረግጠው ተናግረዋል።
‹‹በእኛ በኩልም ሁለተኛ ወደ እንደዚህ ዓይነት ድርድር አንገባም። ድርድሩ ወደ አፍሪካ ኅብረት የገባ በመሆኑ በዚያው መንገድ ነው የምንሄደው፤›› ብለዋል።
በግብፅና ሱዳን በኩል የቀረበው አዲስ አማራጭ ድርድር እንዳልሆነ የሚናገሩት ሚኒስትሩ፣ አዲስ የቀረበው የአራትዮሽ የሽምግልና ጥያቄ እንደሆነ አመልክተዋል። ሽምግልና ውስጥ ለመግባት የተቀመጡ ሥነ ሥርዓቶች መኖራቸውን የሚገልጹት ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ሥነ ሥርዓቶች ሳይሟሉ ወደ ሽምግል ሊገባ እንደማይችል ገልጸዋል።
ወደ ሽምግልና ለመግባት ከተቀመጡት መሥፈርቶች አንዱ ሌሎች የተቀመጡ የአለመግባባት መፍቻ መንገዶችን አሟጦ መጠቀም ሲሆን፣ መሠረታዊው ግን ወደ ሽምግልና ለመግባት ሦስቱም አገሮች የጋራ ስምምነትን የሚጠይቅ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ከቀደመው ትምህርት ወስዶ ወደ እዚህ መንገድ ላለመመለስ አቋም መያዙን አመልክተዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጀንዳ ሊደርስ የሚችልበት የመጨረሻ የፖለቲካ የጡዘት ደረጃ ላይ የገባው ከዓመት በፊት እንደሆነ አስታውሰው፣ ጡዘቱ ተጠናክሮ ኢትዮጵያን የሚፈትናት ቢሆንም ጊዜው የመንበርከክ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
‹‹ይህንን አቋም መያዝ የሚያስከትለው አሉታዊ ጎን ቢኖርም ተባብረን እንወጣዋለን፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ይህንን አቋም በመያዛችን ከሚገጥሙን ፈተናዎች አንዱ የእጅ አዙር ግጭት ነው፡፡ ይኸውም በመተከል በኩል ተጀምሮ ዓይተነዋል፤›› ብለዋል። የመተከል ግጭት አሁን ላይ ዕልባት እያገኘ ቢሆንም፣ ጨርሶ ያልተጠበቀው የሱዳን ድንበር ወረራ መከተሉን አክለዋል።
‹‹የሱዳን መንግሥት ድንበር መውረር ቀጥታ ግንኙነት ባይኖረውም በተዘዋዋሪ መንገድ ግን፣ በግድብ ድርድር ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል።
የእጅ አዙር ግጭት በመቀስቀስ በኢትዮጵያ አለመረጋጋት ለመፍጠር ከሚደረገው እንቅስቃሴ በዘለለ አሳሳቢ ነገር እንደማይኖር የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በግድቡ ላይ ጥቃት የመሰንዘር እንቅስቃሴ ይኖራል ብለን አናስብም። ቢኖርም ግድቡ አስተማማኝ የሆነ ጥበቃና የጥቃት መከላከያ ሥርዓት ተበጅቶለት በክትትል ውስጥ የሚገኝ ፕሮጀክት በመሆኑ የሚያሳስብ ነገር የለም፤›› ብለዋል።
በመሆኑም በእጅ አዙር ግጭት በመቀስቀስ አለመረጋጋት ውስጥ ለመክተት የሚፈነቅሉትን ድንጋይ ኢትዮጵያዊያን ተባብረው መዝጋት ከቻሉ የሚቀራቸው መንገድ ወደ ተመድ የፀጥታ ምክር ቤት መሄድ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችን አደራጅቶ ለመመከት በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
‹‹እኛ እስከ ዛሬ አንስተነው ወደማናቀውና እነሱ ወደማይፈለጉት የክርክር ጉዳይ ውስጥ እንገባለን፤›› ብለዋል። የሚመጣው ጫና ቀላል ባይሆንም ኢትዮጵያ እንደምትወጣው የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የግድቡ ሁለተኛ ዓመት የውኃ ሙሌት በመጪው ክረምት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ውኃ ላለመያዝ የምትስማማ ቢሆን ግንባታውን ማዘግየት ነበረባት የሚሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ግድቡን በመጪው ክረምት ከመሙላት የሚያቆመን ምድራዊ ኃይል አይኖርም፤›› ብለዋል።
ግድቡ አሁን ከደረሰበት የግንባታ ደረጃ አንፃር በመጪው ክረምት የሚመጣው ውኃ ወደታች ሊፈስ የሚችለው በግድቡ አናት ላይ እንደሆነ ያስረዱት ሚኒስትሩ፣ በመሆኑም ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ላይካሄድ የሚችለው በመጪው ክረምት ዝናብ ካልጣለ ብቻ እንደሚሆን አስረድተዋል።