የሚሠራበት ቦታ ለኮሮና ወረርሽኝ የሚያጋልጥ በመሆኑ ክትባቱን ካገኙት ውስጥ የ36 ዓመቱ አቶ ግርማ ወንድማገኝ አንዱ ነው፡፡ ከጤና ባለሙያዎች ጀምሮ ሌሎችም የኮቪድ-19 ክትባት መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. መሰጠት ሲጀመር ለሁለት የተከፈሉ ይመስል እንደነበር ይናገራል፡፡
ገሚሱ ከየአካባቢው በሚሰማው ወሬ ፍርኃት ውስጥ ገብቶ ክትባቱን አልወስድም የሚሉ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ የመጀመርያ ዕድል እንዳያመልጥ በሚል ክንዳቸውን እንደዘረጉ ይገልጻል፡፡ በወቅቱ አቶ ግርማ በነበረው ሁኔታ ግር ቢሰኝም እንዳያልፈው እንደተከተበ ይገልጻል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ወረርሽኝ ሲከሰት ቀድሞ ይሰጥ የነበረውን ጠቅላላ ሕክምና ወደ ሌሎች ሕክምና ተቋማት በማዘዋወር ለኮሮና ወረርሽኝ ብቻ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ነው፡፡
የጤና ሚኒስቴርም በኢትዮጵያ የመጀመርያውን ዙር የኮሮና ክትባት በመላ ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሰዓት ካስጀመረባቸው ተቋማት ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ይገኝበታል፡፡ በማስጀመሪያው ክትባት ካገኙት ውስጥ አቶ ግርማ ይገኝበታል፡፡
በሆስፒታሉ የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ግርማ፣ ክትባቱን ከወሰደ በኋላ ብዙ ወዳጆቹ ክትባቱን መውሰድ እንደሌለበትና የ666 አባል ነህ ወይ? የደም መርጋት ቢይዝህስ? እንዳሉት ያስረዳል፡፡
ክትባቱን በወሰደ በማግሥቱ የድካም ስሜት እንደተሰማውና ከዚያ በኋላ ምንም ዓይነት ችግር እንዳላጋጠመው ተናግሯል፡፡ ስናነጋግረው በተከተበ በአምስተኛ ቀኑ ሲሆን፣ ከመጀመሪያው ቀን ውጪ ስሜቶቹ ሙሉ ለመሉ እንደጠፉ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡
ከተለያዩ አገሮች የሚወጡ መረጃዎችን ሲሰማ እንደፈራ ነገር ግን ከሪፖርተር ጋር በመጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ውይይት እስካደረገበት ድረስ ምንም ዓይነት የጤና እክል እንዳላጋጠመው ተናግሯል፡፡
በመጀመርያው ዙር አስትራዜኔካ የተባለውን ክትባት የወሰደው አቶ ግርማ፣ ሁለተኛው ደግሞ ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚሰጠው ተነግሮት የቀጠሮ ካርድ እንደተሰጠው ገልጿል፡፡
ጀነራል ዊንጌት አካባቢ የሚገኘው ወረዳ 10 ጤና ጣቢያ የኮቪድ-19 ማገገሚያ ማዕከል በመጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ክትባት ያስጀመረበት ነው፡፡ በዕለቱ ለኅብረተሰቡ መረጃውን ለማድረስ ከመጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ውስጥ ክትባቱን ከወሰዱት አቶ ተመስገን አብርሃም አንዱ ነው፡፡
አቶ ተመስገን ለሪፖርተር እንደተናገረው፣ በአብዛኛው የተከተቡት የጤና ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ በዕለቱ ለዘገባ ከተገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች ውስጥ አንደኛው ሆኗል፡፡ ክትባቱን ከወሰደ ቀናት እንደተቆጠሩ የሚናገረው አቶ ተመስገን ምንም ዓይነት ሕመም እንደሌለው፣ ክትባቱን ወስዶ በማግሥቱ ክንዱ ላይ ከተሰማው የሕመም ስሜት ውጭ ሌላ ሕመም እንዳላጋጠመው ገልጿል፡፡
ይህም የትኛውም የክትባት ዓይነት ክትባቱ በተሰጠበት ቦታ ላይ እንዳየሰው ክትባትን የመቋቋም አቅም የሕመም ስሜት እንደሚኖር የሚታወቅ መሆኑን ያስረዳል፡፡
የኮሮና ቫይረስ የብሔራዊ ሕክምና አማካሪ ቡድን አባል ወልደሰንበት ዋጋነው (ዶ/ር) ክትባቱን መውሰድ ያለባቸውን ሰዎች አስመልክተው እንዳሉት፣ ክትባቱ በሽታው ላለበት ሰው የሚሰጠው በሽታው ከተያዘበት ከአራተኛው ሳምንት በኋላ ነው፡፡ ተፈጥሮአዊ በሽታውን የመከላከል ኃይል ከአራተኛው ሳምንት ጀምሮ ስለሚጨምር ከዚህ በኋላ ስለሚሆን ነው፡፡
ከ16 ዓመት በታች ለሚገኙ ሕፃናትና ለነብሰ ጡር እናቶች የኮሮና ወረርሽኝ ክትባት አይሰጥም፡፡ ክትባቱ ሲሠራ የሚሞከረው አዋቂዎች ላይ በመሆኑ ሕፃናትና እርጉዞች ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖም አይታወቅም፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ ክትባት ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ክትባት ሲሠራ መጀመርያ የሚሞከረው ጤነኛ አዋቂ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ነብሰጡሮችና ሕፃናት ላይ ስለማይሞከር ጽንስ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ አይታወቅም፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በተለየ ሁኔታ ነብሰ ጡሮችና ሕፃናትን የሚያጠቃ ስላልሆነም ክትባቱን ይውሰዱ የሚል አስገዳጅ ሁኔታ የለም፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ (ዶ/ር) ዮሐንስ ጫላ እንደተናገሩት፣ የኮሮና ወረርሽ ምልክት የታየበት ሰው ክትባቱን ባይወስድ ይመክራሉ፡፡
ዮሐንስ (ዶ/ር) ኮሮና ወረርሽኝ ተይዘው የለቀቃቸው ሰዎች ከአንድ ወር በኋላ መውሰድ ይችላሉ ይላሉ፡፡ እንደ አገር አቀፍና እንደ ከተማ የማስጀመር ሥራዎች የተሠራ ሲሆን፣ ክትባቱን ለማስቀጠል መረጃዎች እየተሰባሰቡ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ተናግረዋል፡፡ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለሆኑም ከሁሉም ጤና ተቋማት መረጃ እየተሰባሰበ ነው፡፡
እንደ ሌላው ክትባት በቁጥር የሚመጣ ሳይሆን ሁሉም በየተቋማቱ ያለው ሠራተኛ ቁጥር ታይቶ የሚበቃው ዶዝ እንዲደርሳቸው ይደረጋል ያሉት ዶ/ር ዮሐንስ፣ በማስጀመሪያ ወቅት ከ70 በላይ የጤና ባለሙያዎበች ክትባቱን ያገኙ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳላጋጠማቸው ገልጸዋል፡፡
ይኼ ማለት ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ችግር የለበትም ማለት ሳይሆን፣ እንደሚባለውና በሚወራው ልክ የጎላ ችግር እንዳላመጣ ገልጸዋል፡፡ ከ17 ሚሊዮን በላይ የአስትራዜኔካ ክትባት ከወሰዱት 37 ሰዎች ላይ ብቻ የደም መርጋት አጋጥሟል ተብሎ አንዳንድ አገሮች እስኪጣራ ድረስ ክትባቱ እንዳይሰጥ ማገዳቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የአስትራዜኔካ ክትባት ከመውሰዳቸው በፊት ይሁን ከወሰዱ በኋላ የሚታወቅ ነገር እንደሌለና ከዓለም ጤና ድርጅት፣ የኦክስፎርድ የምርምር ተቋምና የእንግሊዝ የመድኃኒት ጥራት ቁጥጥር ተቋም የደም መርጋት ስለማስከተሉ እንዳላረጋገጡ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ውዥንብሮችን ትቶ የክትባቱን አስፈላጊነት ኅብረተሰቡ አጽንኦት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
በክትባቱ ምክንያት የሚደርስ ከፍተኛ የጤና እክል ሲኖር መድሐኒቱን የሠራ ድርጅት ኃላፊነት የሚወስድበት አካሄድ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ በዋናነት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በጥንቃቄ መራመድ፣ ማጤን ያለበት ጉዳይ በኮሮና ቫይረስ ከዕለት ወደ ዕለት የሚያዙ ሰዎች ቁጥርና የሚሞቱ ሰዎች እየጨመረ መምጣቱንና የመጀመርያ አማራጭ አድርጎ መውሰድ ያለበት ቅድመ መከላከል ላይ መሆኑን ኃላፊው አሳስበዋል፡፡
በፅኑ ሕሙማን ክፍልና በኦክስጂን ማቅረብ በኩል እጥረት እየገጠመ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዮሐንስ አሁንም ኅብረተሰቡ በእጁ ያለውን ቅድመ መከላከያ መንገዶችን እንዲተገብር ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ክትባቱ ተወሰደ ማለት መቶ በመቶ ተጠብቀናል ማለት እንዳልሆነ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ጥንቃቄ ማድረጉ እንደሚበጅም ተናግረዋል፡፡
(ዶ/ር) ዮሐንስ እንደ ጤና ባለሙያ ክትባቱን በመውሰድ፣ አርዓያ ለመሆንና ከኅብረተሰቡ የሚነዛው አላስፈላጊ መረጃ ትክክል አለመሆኑን ለማሳየት በመጀመርያው ዙር ክትባት ወስደዋል፡፡
በዚህም እስካሁን ምንም ዓይነት የጤና እክል እንዳለጋጠማቸውና ሙሉ ለሙሉ ሥራቸውን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው በተደጋጋሚ አጽንኦት ሰጥተው አሁን ኅብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው የሚያድንበት መንገድ ቅድመ መከላከል መሆኑን ነው፡፡ (ዶ/ር) ወልደሰንበት በበኩላቸው፣ በመጀመርያው ዙር የታቀደው የክትባት ብዛት 20 በመቶውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚሸፍን ሲሆን፣ የተቀሩት ለመድረስ ጊዜ ስለሚወስድ ቅድመ መከላከሉን ጠበቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ቢያንስ 75 በመቶ የኅብረተሰቡ ክፍል ክትባቱን ካልወሰደ ቅድመ መከላከሉ ሊቀጥል የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምግብና መድሐኒት ባለሥልጣን የመድሐኒትና ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ አብደላ ቃሶ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ ፈቃድ አግኝተው የገቡት ሁለት የኮሮና ወረርሽኝ ክትባት ዓይነቶች ናቸው፡፡
የመጀመርያው በኮቫክስ ሥር ከሚገኘው አስትራዜኔካ 2.2 ሚሊዮን ዶዝ የገባ ሲሆን፣ ሁለተኛው የቻይና መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ያስገበው ሳይኖ ፋርማ ክትባት ገብቷል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት በዕርዳታም በገንዘብም ለማስገት የኮሮና ወረርሽኝ ክትባት አምራቾች ጋር ስምምነት ለማድረግ በሒደት ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ ክትባት በአስቸኳይ ጊዜ አጠቃቀም መመርያ መሠረት እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በመመርያው በተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት እንዲሁም በተለያዩ አገሮች፣ በተለያዩ የዕድሜ ክልልና በተለይም የአፍሪካ ዘረመል መጣጣምን ባገናዘበ መልኩ የተጠኑ ጥናቶችን እንዲቀርቡ እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ክትባቱ ጥቅም ላይ ሲውል የሚያጋጥሙ ችግሮች በምን መልኩ ይፈታሉ፣ አምራቹ ያለው ተጠያቂነት ምን ይመስላል የሚለውም እንዲገባ ተደርጓል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ከፈቀዳቸው ውስጥ በህንድ የተመረተው አስትራዜኔካ፣ የቻይና ምርት የሆነው በድንገተኛ ጊዜ አጠቃቀም መመርያ መሠረት ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ጥምረት ኮቫክስ (Covax) አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጀርመን አውስትራሊያ፣ ብሪቴን፣ ቻይና በዋናነነት በጥምረት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በእነዚህ የሚሰራጨው ክትባት ብዙ አገሮች ገንዘብ አዋጥተው ግዢ ፈጽመው ለ92 አገሮች ዕርዳታ የሚሰጡበትም ነው፡፡
አሁን የገቡት ሁለቱም የኮሮና ቫይረስ ክትባት ምርቶች በኮቫክስ ጥምረት አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ ወደ አገር ውስጥ የገቡት ኮቫክስ ጥምረት አስትራዜኔካና ቻይና ለዜጎቿ ያስገባችው የሳይኖ ፋርማ ምርት ናቸው፡፡
መድኃኒቱ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ክትትል የሚያደርግበት መንገድ እንዳለው ባለሥልጣኑ ጠቁሟል፡፡ ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች የተጠበቁም ሆነ ያልተጠበቁ ክስተቶች ክትትል የሚደረግና የሚገቡበት መንገድም በጥንቃቄ በመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ፣ ተመሳስለው የሚሠሩ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች እንዳይኖሩ ከፍተኛ ጥንቃቄና የቁጥጥር ሥርዓት፣ የመረጃ ልውውጥ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል ብለዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ክትባት ከመግባቱ በፊት የኮቫክስ ጥምረት ፕሮቶኮል ስምምነት መደረጉን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በተለይ ከመድኃኒቱ ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ ጉዳቶች እንደሚከፈል ስምምነት ተድርጓል፡፡
ለደረሰው ጉዳት መድኃኒት አቅራቢው ብቻ የሚከፍለው ሳይሆን መንግሥት ጭምር እንዲከፍል ነው፡፡ የአስትራዜኔካ እስካሁን ባለው መሠረት አደረሰው የተባለው ጉዳት ክትባቱ እንዳይሰጥ የሚከለክል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ አብደላ እንደተናገሩት፣ በተለይም የተከተቡ ሰዎች የሚጠበቅም ሆነ ያልተጠበቀ ክስተት ካጋጠማቸው ለምግብና መድሐኒት ባለሥልጣን ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ክትባቱ ችግር ካስከተለ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆም ችግሩ የሚፈተሽ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በኮቫክስ ጥምረት የተገኙ መድሐኒቶችን ተጠቅመው ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የካሳ ፕቶኮልም ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም ክትባቱን ወስደው ከፍተኛ ጉዳት (የአካል ጉዳት) ለደረሰባቸው የካሳ ክፍያ ይሰጣል፡፡ የካሳ ክፍያው ሥርዓት ግለሰቡ የደረሰበት ጉዳት በመቶኛ ተሠልቶ በአሜሪካ ሜዲካል አሶሴየሽን ኢምፔይርመንት ጋይድ መሠረት ተገምግሞ እንዲከፈል ይደረጋል፡፡
ይህንን ክፍያ ሊያገኙ የሚችሉት በኮቫክስ ሊስት የገቡት አገሮች ብቻ ናቸው፡፡ የዚህ የአከፋፈል ሥርዓት በኮቫክስ ኢንሼቲቭ ውስጥ የተካተተ ክትባት ከሆነ ብቻ እንደሆነ ፕሮቶኮሎ ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ለሁሉም ለተጎዱ ሰዎች ካሳ የመክፈል ግዴታ እንደሌለበት ያስቀምጣል፡፡
በጣም በተደጋጋሚ በአንድ ጤና ተቋም ተጎጂዎች መኖራቸውን የተረጋገጠ መሆን አለበት፡፡ በአሜሪካ ሜዲካል አሶሴሽን ኢምፔይ ጋይድ መረሠት መቅረብ ያለበት ሲሆን አገሪቷ (ግለሰቡ) ራሱ ማገናዘብ እንዳለበት ፕሮቶኮሎ ያዛል፡፡ በተለይም ክፍያውን ሊያገኙ የሚትሉት Advanced Market Commitment ( AMC)አባል አገሮች ውስጥ መሆን አለባቸው፡፡
ከእነዚ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ላይቤሪያ፣ ማዳጋስጋር፣ ኒጀር፣ ሩዋንዳ፣ ቶጎ፣ ኡጋንዳ፣ ኤርትራን ጨምሮ በአጠቃላይ 92 አገሮች ከኮቫክስ ክትባቱን እንዲያገኙ ስምምነት አድርገዋል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅትና ኮቫክስም በክትባቱ ምክንያት ጉዳት ለሚገጥማቸው ሰዎች ካሳ ለመክፈል ስምምነት አድርገዋል፡፡