Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበውኃ ቀን ስለዓባይ ውኃና ትውፊቱ

በውኃ ቀን ስለዓባይ ውኃና ትውፊቱ

ቀን:

‹‹ውኃ ለተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ነገሮች ነው፡፡ ውኃ ለቤትዎና ለቤተሰብዎ ሕይወት፣ ለኑሮዎ፣ ለባህላዊ ልምዶችዎ፣ ለጤንነትዎ፣ ለአካባቢዎ ያለው ጠቀሜታ ምንድነው? እስቲ ስለ ውኃ ያለዎትን ታሪክ፣ አሳብና ስሜትዎን ያውጉን።››

የመንግሥታቱ ድርጅት በየዓመቱ መጋቢት 13 ቀን (ማርች 22) የሚያከብረው የዓለም ውኃ ቀን፣ ዘንድሮ የውኃ እሴት በሚል መሪ ቃል በበይነ መረብ እንደሚከበር ባስታወቀበት መስመሩ ላይ ነው፣ ሰዎች ስለ ውኃ ያላቸውን ምልከታ እንዲያጋሩት የጠየቀው፡፡

እንደ ተቋሙ መግለጫ የዘንድሮው የክብረ ውኃ ጭብጥ፣ የውኃ ዋጋ ከዋጋውም በላይ እጅግ የሚበልጥ ከመሆኑ ላይ ያጠነጥናል፡፡ ውኃ ለፍጡራን፣ ለምግብ፣ ለባህል፣ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለኢኮኖሚ፣ ለተፈጥሮ አካባቢና ለሌሎችም የማይተካ እሴት አለው፡፡

በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ1992 በተወሰነው መሠረት መጋቢት 10 ቀን የውኃ ቀን ሆኖ የመከበሩ ዋነኛ ዓላማ፣ ስለውኃ ቁጠባና አጠቃቀም እንዲሁም ስለውኃ ነክ ጉዳዮች ትኩረት ለመስጠት፣ ለማስገንዘብና የኅብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ ነው፡፡ በዘላቂ ልማት ግቦች አንቀጽ 6 ትልም መሠረትም በ2030 የውኃ እና የአካባቢ ንጽሕናን ለሁሉም ማረጋገጥ ነው፡፡

ዓባይና ኢትዮጵያ

ዓለም አቀፉ ተቋም ከዘንድሮው የዓለም ውኃ ቀን ጋር አያይዞ ‹‹ስለውኃ ያለዎትን ታሪክ፣ አሳብና ስሜት አውጉ›› ብሎ ባቀረበው ጥሪ መሠረት በታላቁ ዓባይ ወንዝ ላይ ተመሥርተን መጻፍን ወድደናል፡፡

ስመ ገናናውዓባይ ወንዝ ለሥልጣኔ፣ ለባህል፣ ለእምነት ታላቅ ምንጭና ብሔራዊ ኩራት መሆኑ ይወሳል፡፡ አዳምና ሔዋን የተፈጠሩባትን ኤዶም ገነት ከከበቡት ታላላቅ ወንዞች አንዱ ዓባይ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህን ጥናትም መደገፉም ይነገራል፡፡

አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ በዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት ዓባይን እንዲህ ይፈቱታል፡፡ ‹‹አባትያ፣ የወንዞች አባት ከአራቱ ወንዞች አንደኛው መዠመሪያው ወንዝ ታላቅ ዠማ፣ በግዕዝ አዋልድ ፈለግ አባዊ ይባላል፡፡ እሱም በዳሞት ሰኮላ ሚካኤል ከሚባል አገር ከደንገዛ ተራራ ሥር ፈልቆ ጐዣምን ይከባል፣ ምንጩም ግሼ ዓባይ ይባላል፤ በጣና ላይ ዐልፎ ወደ ካርቱም ከዚያም ወደ ምስር [ግብፅ] ይኼዳል፡፡ ፈሳሹም ሰማይ መስሎ ስለሚታይ ጥቁር ዓባይ ይሉታል፡፡››

ገነትን የሚከቡት ወንዞች በምሥራቅ ኤፍራጥስና ጤግሮስ፣ በምዕራብ ኤፌሶንና ግዮን መሆናቸው በድርሳናት ተጽፏል፡፡ ግዮን ጥቁር ዓባይ ነው የሚሉ ቢኖሩም እንደ አለቃ ደስታ አገላለጽ፣ ዓባይን ‹‹ኤፌሶን›› ሲሉት በደቡባዊ አፍሪካ አካባቢ ኒያንዛ ከሚባል ሐይቅ የሚወጣው ነጭ ዓባይን ‹‹ግዮን›› ብለው ይጠሩታል፡፡

በውጮች ዘንድ የኢትዮጵያ ዓባይ ከጣና ሐይቅ የሚነሣውን «ብሉ ናይል» ከማዕከላዊ አፍሪካ የታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የሚወጣውን «ዋይት ናይል» ሲሉት ሁለቱ ወንዞች ሱዳን ካርቱም ተገናኝተው ወደ ግብፅ በሚያደርጉት ጉዞ «ናይል» በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ፡፡ ናይል ጥንተ ቃሉ ከግሪክ ‹‹ኒሎስ›› የተገኘ ሲሆን፣ ፍችውም የወንዝ ሸለቆ ማለት ነው፡፡

በጥንታውያን ግብፃውያን ውኃ ኡዋት (Uat) ተብሎ ሲጠራ፣ ፍችውም አረንጓዴ ማለት ነው፡፡ ውኃና አረንጓዴ ተመሳሳይነት እንዳላቸውና የነፍስ መገለጫም እንደሆነ በአፈ ታሪክ ይነገራል፡፡ ሊዶር ከሮቭኪን፣ የጥንቱ ዓለም ታሪክ ባሉት መጽሐፋቸው፣ ግብፃውያን የዓባይ ወንዝ ከየት እንደሚመነጭ ባለማወቃቸው የዓባይ አምላክ ከሰማይ በባልዲ እየቀዳ ቁልቁል ወደ መሬእንደሚያንቆረቆርላቸውና የጐርፍ ማጥለቅለቅ የሚያጋጥመውም የሚንቆረቆርላቸው የውኃ መጠን ሲጨምር እንደሆነ ያምኑ ነበር፡፡ በመሆኑም ማሳቸውን ያለመልምላቸውና ሕይወታቸውን ይጠብቅላቸው ዘንድ ዓባይን ዘወትር ይማፀኑት፣ ምስጋናቸውን ይዘምሩለትና ውዳሴያቸውን ያቅራሩለት ነበር፡፡

መምህር አእመረ አሸብር ‹‹ዓባይና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን›› በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው እንደገለጹት፣ የዓባይ ወንዝ ይህ ከኢትዮጵያ እምነትና ሥልጣኔ ጋር ልዩ ትስስር ያለው ታላቅ የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡

‹‹የዓባይንና የኢትዮጵያን ትስስር ለማወቅ ምንጭ አድርገን የምንጠቀመው አንዱና ዋነኛው ነገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ዓባይ ወንዝ የምታስተምረውን ትምህርት ነው፡፡ ዓባይ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በመጻሕፍተ ሊቃውንት፣ በታሪክና በትውፊት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ታላቅ የሀገር ሀብት ነው፤›› የሚሉት መምህር አእመረ፣ የግዕዝ በግዕዝ የኦሪት ትርጓሜ ስለ ዓባይ ያስተማራቸውን ታላላቅ ነጥቦችን ይዘረዝራሉ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ግዮን፣ በግዕዝ ዓባይ ተብሎ የሚጠራው ታላቅ ወንዝ “እልኔል” ወይም “ኔል” ተብሎ እንደሚጠራ ያሳያል፤ እልኔል ወይም ኔል የሚለው ስያሜ ደግሞ ናይል ከሚለው የዓባይ ስም ጋር አንድ ነው፡፡ እልኔል ወይም ኔል ማለት ቀለም ማለት ሲሆን ጥቁር ዓባይ ጥቁር ኔል፣ ነጭ ዓባይ ደግሞ ነጭ ኔል ተብለው ይጠራሉ፡፡

ዓባይ የሚለው የግዕዝ ቃል ‹‹ታላቅ›› ማለት ሲሆን ቃሉ የወንዙን ታላቅነት ያመለክታል፡፡

የአንድምታ ትርጓሜው ሲቀጥልም ግዮን የተባለውም እልኔል (ኔል) ነው፣ ከአዜብ ምሥራቅ ተነሥቶ ኢትዮጵያንና ግብፅን አጠጥቶ ወደ ምዕራብ ባሕር ይገባል፡፡

የሥነ ፍጥረትን ነገር በስፋት የሚናገረውና አክሲማሮስ በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ፣ ዓባይን ወተት ሲለው፣ የአናቴዎስ ቅዳሴ ደግሞ ዓባይ የብርሃን ወንዝ ነው ይለዋል፡፡

ተረትና ምሳሌ

    ዓባይ ከኢትዮጵያውያን ሕይወት ጋር ጥልቅ ትስስር አለው፡፡ በተለይ የታላቁ ወንዝ መጋቢ በሆኑት አካባቢዎች የሚኖረው ኅብረተሰብ ከእምነቱ ጋር የሚያያይዘው ብዙ ነገር አለው፡፡ ለዓባይ የንግሥ በዓል ሁሉ የሚያደርጉለት አሉ፡፡ ከተረትና ምሳሌ ጋር አቆራኝተው ሕይወታቸውንም ይገልጹበታል፡፡ ይሔሱበታልም፡፡ በአረንጓዴው ዘመቻ ወቅት «ምድሪቱን አረንጓዴ እናለብሳታለን» የሚለውን ‹‹አብዮታዊ ጥሪ›› የሰማ አንድ ገበሬ፡-

 ‹‹አንተ የአገሬ ውኃ አረንጓዴ አትልበስ፤

እጠጣህ ይሆናል ምናልባት ስመለስ›› ብሎ መግጠሙ ይነገራል፡፡

‹‹ውኃ ቀለብ ሆኖ ሰውን ካሳደረ፣

ዓባይና ጣና አገሬ ነበረ፡፡››

የውኃ ጎታዎቹ ዓባይና ጣና ለጥበብ ንሸጣ ዓይነተኛ መሣሪያ እንደሆኑ የአለቃ ገብረ ሐና ጥበባዊ ሥራ ማሳያ ይሆናል፡፡ አለቃ ለያሬዳዊው ማሕሌት ማጀቢያ ያደራጁትንና በልጃቸየሰየሙት ‹‹የተክሌ አቋቋም›› በመባል የሚታወቀውን የአቋቋም ሥርዓት የፈጠሩት ዓባይጣና ሐይቅ ዳርቻ ተተክለው ከነበሩት የሸምበቆ ተክሎች ከውኃው ውስጥ ሆነው ሲወዛወዙ በማየታቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡

“የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው” የሚለው ብሂል ኢትዮጵያ በዓባይ ሀብቷ እስካሁን በምልዓት ላለመጠቀሟ በምሳሌነት ሲጠቀስ ኖሯል፡፡ እስካሁን የዓባይ ዙርያ ኅብረተሰብ በቂ የውኃ አቅርቦት በየደጃፉ እያገኘ አይደለም፡፡ የኤሌክትሪክ ብርሃንም እንዲሁ፡፡ መስኖአዊ እርሻንም እውን አላደረገም፡፡

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

በስደት ኖሮ በስደት ያረፈው በገሞራነት  የሚታወቀው ባለቅኔው ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ፣  “እናትክን!” በሉልኝ! በተሰኘው ዓባይ ተኮር መጽሐፉ እንደገለጸው፣ እስከዚህኛው ዘመን ድረስ በዓባይ ወንዟ አንፃር፣ ሀገረ ኢትዮጵያ ለመንታ አፍሪካውያን አህጉራት [ሱዳንና ግብፅ] እህቶቿ ስትል፣ ከፍተኛ የዕርዳታ መስዋዕትነት ስትከፍል ኖራለች፡፡ መስዋዕት መባሉም፣ የራሷን ሕዝቦች እያስጠማች የለገሰችው በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ሥልጣኔ የመነጨው በውኃ ዳርቻ ላይ ነው›› ቢባልም፣ የዓባይ ውኃ ምንጭ ባለቤት የሆነችዋ ኢትዮጵያ እንደሚፈስላቸው አገሮች ያሉ የፒራሚድ ሥልጣኔያዊ ትዕምርት አላነፀችም፡፡ የፈለገ ግዮን ልደቱም ሆነ መሠረቱ ምድረ ኢትዮጵያ በመሆኑ፣ በኢርቱዕ ንፃሬ ለታችኞቹ ሥልጣኔ ድርሻ ማበርከቱ የማይካድ ነው፡፡

 ‹‹የብሩህ ተስፋና የሩቅ ምኞት አለኝታ ሆኖ፣ ለብዙኃን ኢትዮጵያውያን ወገኖች የህልውናቸው ዋስትና፣ የሕይወታቸው ኅብስተ መና ይሆናል ተብሎ እምነት የተጣለበት ዓባይ ወንዝ ነው፤›› የሚለው ገሞራው በሌላው ገጹ እንዳሰመረበት፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብሯንና አገራዊ ይዘቷን ለማስከበር የሚያቅታት አይሆንም፡፡ ለዘመናት በዘፈቀደ ሲፈሱ የኖሩ ወንዞቿን ለማስከበር ልጆቿ ወደ ኋላ አይሉም፡፡

ሕዝቦቿ ይህን ነጥብ አስመልከተው፡-

‹‹በቆላው ሀገር ውስጥ ለሚቧርቅ ፈረስ፣

በታችኛው ምድር ለሚፈነጭ ፈረስ፣

እንደዠማ ውኃ በመስክ ለሚደንስ፣

ልጓሙ ደጋ ነው ከያዙት የማይፈስ…›› እያሉ ቢዘምሩ ብሂላቸው ላያስደንቅ ነው፡፡

ገሞራው በስደት ዓለም ውስጥ ሆኖ ለኢትዮጵያ ያልበጀውን ለባዕዳን ስለጠቀመውዓባይ ወንዝ አረ እንዴት ነው ነገሩ ሲል አንጎራጉሯል፡፡ የውኃ ጥማት ለፈጀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሮሮአዊ ስንክሳር ነበር በክታቡ ያስገነዘበው፡፡

ባለቅኔው በዚህ አገላለጹ ብቻ አልተወሰነም፡፡ ፍኖተ ዓባይን፣ መልክአ ዓባይን እንዲህ በቁጭት ይፈክረዋል፡፡

‹‹ቋጥኝና ገረገንብ በሚበዛበት አካባቢ ሁሉ፣ የዓባይ ወንዛዊ ጥልቀት እጅግ ቅርብ ነው፡፡ በአንፃሩ እንደዚያ ያለው አካባቢ ሁሉ፣ ጎናዊ የሆነ ስፋት አለው፡፡ አንድን ቋጥኝ አልፎ ቆልቋላማ ሥፍራ ባገኘበት ሥፍራ ሁሉ፣ ዓባይን ሲዘል ላየው ሰው ደራጎን ምስጋና ይንሳው፡፡ በዚያም ወቅት፣ የሚከሰተው ድምፅና የውኃዎች ርጭት፣ ከሰማያዊ መብረቅና ነጎድጓድ በምንም አያንስም፡፡ በአንክሮ ለሚያው፣ እጅግ አስደናቂና አስደሳች ትርዒት ነው፡፡

‹‹እንደ መቅደላ አፋፍ ባገጠጡ ቋጥኞች ላይ፣ እየተንደረደሩ የሚወርዱት የዓባይ ፏፏቴዎች፣ ልዩ ተዓምራት መሥራት የሚችሉ ጉልበታዊ ኃይሎች ነበሩ፡፡ ጉብታ መሬቶች ለማለፍ፣ እየተምዘገዘገ የሚወርደው የዓባይ ቁጡ የፏፏቴ ውኃ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኰረንቲ ወለድ ሻፍቶችን ማንቀሳቀስ የሚያስችል፣ የሚሊዮን ፈረሶች ጉልበት ኃይል አለው፡፡ ከዚያ ሁኔታ ላይ ሊፈጠር የሚችለው ኮረንቲያዊ የኃይል ምንጭ፣ በበኩሉ ማዕሠረ ድህነት ኢትዮጵያን በወራት ዕድሜ ብቻ መፍታት በቻለ ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ እነዚያን የኮረንቲ ኃይል ለማመንጨት፣ ከሚገደበው ግድብ ውስጥ የሚንጣለለው ውኃ በመስኖ የውኃ አከፋፈል ጥበብ ተገዶ፣ በየአካባቢው ክፍለ ሀገር ሊሠራጭ በሚችልበት ወቅት፣ ከሚፈጥረው የእርሻ ምርታዊ ውጤት ይልቅ፣ የልምላሜው ውበት ብቻ ስንት ተመልካቾችን ጭምር በሳበ ነበር፡፡ እርግጥ ‹‹ምድረ ገነት›› ይፈጥር ነበር! ዕሴቱማ አይነገር!!

ገሞራው እንጉርጉሮውን ይቀጥላል፡፡

‹‹በእርግጥም ዓባይ የሚያስቡትና የሚቀልቡት ድልብ ሠንጋና ቅልብ ሙክት አይደለም! በሰባና በደለበ ወቅት እንዲታረድ የሚጠበቅ እርድ!! እዚያ ምድራችን ላይ እየተወዛወዘ፣ የሆነ ሱፐርቡልዶዘር ይመስል፣ ለዘመናት ማርማ፣ ወተትማ ውኃችንን፣ ወርቅማ እቁማ አፈራችንን እንዳጋዘ ሊኖር? እንዲያ የለየለት ዋልጌ ሆኖ እንዳሾፈና እንዳላገጠ ሊኖር? አጠገቡ ሆኖ ‹የውኃ ያለህ!› እያለ ሲጮህ፣ ደራሽ ውኃ ያጣው ወገኑ እንደ ገረረ ጀንዲ ደርቆ ሲያልቅ፣ ለቀሪው ቋሚ ወገኑ ፈለገ ዓባይ የዘለዓለም መቆጫ (የሚቆጭበት) ምክንያት ትዝብት ሆኖ ሊኖር ነው፡፡

ገሞራው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹ውኃችን አፈር ይዞ እንዳይሄድ ወንፊት ይዤ ልቅረብምይል ይሆናል ብሎ ባንፀባረቀ 23 ዓመታት በኋላ እርሱ በሕይወት እያለ ዕውን የሆነው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለመገንባት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጉባ የመሠረት ድንጋይ መጣሉና ሥራው መጀመሩ ነው፡፡

መጋቢት 24 ቀን 2003 .. ‹‹የሚሌኒየም ግድብ›› (አስቀድሞ ሲጠነሰስ ‹‹ኤክስ ፕሮጀክት››) በሚል በፌዴራላዊ ሪፐብሊኩ የመጀመርያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካይነት የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የግድቡ ሥራ ዘንድሮ አሥረኛ ዓመቱን ይዟል፡፡

በቅርቡ የወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ የግድቡ ፕሮጀክት ክንዋኔ 79 በመቶ ደርሷል፡፡ ዓምና በክረምቱ የመጀመርያው ዙር የውኃ ሙሌት እንደተከናወነው ሁሉ ዘንድሮም እንደሚከናወን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቅርቡ አስታውቋል፡፡

የገሞራው ጸሎት

ከቤተ ክርስቲያን የ‹‹አባታችን ሆይ›› ጸሎት በመነሳት፣ በኢትዮጵያ ‹‹መሪዎች ነን›› ባዮች ቅድመ አብዮት ‹‹አባታችን ብሬዥኔቭ ሆይ…››፣ ድኅረ አብዮትም ‹‹አባታችን ጆርጅ ቡሽ ሆይ…›› የሚባል ጸሎት ማላዘናቸውን ያስታወሰው ገሞራው፣ ‹‹አማራጭና ተገቢ ጸሎት›› ያለውንና በወንዘ ዓባይ ላይ ያቀናበረውን ከ32 ዓመታት በፊት እንዲህ ጸልዮታል፡፡ አስተጋብቶታልም፡፡

     አማራጭና ተገቢ ጸሎት

አባታችን የዓባይ ወንዝ ፈጣሪ ሆይ!

በጣና ሐይቅና በሰሜን ኢትዮጵያ የምትኖር!

ስምህ ይቀደስ!

ፈቃድህ በምድረ ሱዳንና በምድረ ግብፅ እንደሆነ ሁሉ!

እንዲሁም በመላዋ ምድረ

ኢትዮጵያም ይሁን!

የዓመት የውኃ ጠለ ምሕረትህን ስጠን ዛሬ!

ለሚቀጥሉት ዓመታት በየግድቦቹና በየመስኖዎቹ ውስጥ አስቀምጥልን!

ከዝናብ ማጣትና ከአፈራችን መጋዝ ይቅር በለን!

የምንጠጣውም ውኃ ሆነ የምናበቅልበት አፈር የለንምና!

ከሀሩር ድርቀት አርቀን!

ወደ ምድረ በዳነት አታግባን!

አርጣቢዋ ውኃ የአንተ ናትና!

ኃይልና ሥልጣን ከነችሎታው!

ለዘለዓለም ይኑር!

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...