Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊመንግሥት አሳታፊ ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ እንዲያዘጋጅ ጥሪ ቀረበ

መንግሥት አሳታፊ ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ እንዲያዘጋጅ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

ኢትዮጵያ እንደ አገር ሁሉንም ያሳተፈ ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ ስለሌላት፣ መንግሥት አሳታፊና ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ እንዲያወጣ ጥሪ ቀረበ፡፡

ላንድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ በተቋማት፣ በመመርያና በአዋጅ ተበጣጥሶ የሚገኘውን የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ሰብሰብ አድርጎና በብሔራዊ ደረጃ አዋቅሮ ፖሊሲ ቢዘጋጅ በኢትዮጵያ ከመሬት አስተዳደር፣ ከምግብ ዋስትና፣ ከልማትና ከመሬት ነክ ጉዳዮች ጋር ተያይዘው ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን መፍታት ይቻላል በሚል፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ እንዲኖራት ግብዓት ለማግኘት ባስጠናው ጥናት ላይ ባለፈው ሳምንት ውይይትና ግምገማ አስደርጓል፡፡

ቀደም ባሉትና በአሁኑ ሥርዓት ኢትዮጵያ ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ ኖሯት ባያውቅም በነበሩና በተበጣጠሱ የመሬት አስተዳደር ቀረፃ ሥርዓቶች ላይ የተሠራው ጥናት ቡድን መሪ መሳይ ሙሉጌታ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ የአብዛኛው ሕዝብ ሕይወት በቀጥታ ከመሬት ጋር የተያያዘና የተመሠረተ፣ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ ቀጥተኛ ከመሬት ጋር የተቆራኘ ሕይወት ያለው ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ራሱን የቻለና የተጠቃለለ የመሬት ፖሊሲ የላትም፡፡

- Advertisement -

የመሬት ፖሊሲ ተበታትኖ በአዋጅ፣ በፕሮግራሞች፣ በሕገ መንግሥቱ በተለያዩ አንቀጾች ይኑር እንጂ ራሱን ችሎ የኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲ የሚል ሰነድ ባለመኖሩ ምክንያት፣ ምን ችግሮች ታይተዋል የሚለውን ያየው ጥናቱ አተገባበር ላይ ያሉ ችግሮችን ቃኝቷል፡፡

አንድ የመሬት ጉዳይ ለመተግበር የተለያዩ ዶክመንቶች ታይተውና ተገናዝበው በመሆኑ የባለሙያዎችን ጊዜ የሚወስድ፣ የሚያሰለችና አተገባበሩ ግልጽ እንዳይሆን ማድረጉ ተገልጿል፡፡

ከመሬት ጋር ባሉ ችግሮች ለምሳሌ አካባቢን በአግባቡ አለመጠበቅ፣ የአፈር መሸርሸር፣ የደን ውድመት፣ የውኃ አካላት መድረቅ፣ የዱር አራዊት መጎዳትና ሌሎችም ለመከሰታቸው ወጥ የሆነ፣ የተጠቃለለና ወቅቱን የጠበቀ የመሬት ፖሊሲ በኢትዮጵያ ውስጥ አለመኖሩ በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡

ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ተበታትነው መገኘታቸውም ዘርፉ የተለያዩ ችግሮች እንዲኖሩበት ማድረጉ፣ በቂ የካሳ ክፍያና ከገበያ ጋር ተያይዞ የመሬት ዋጋ ግምት ላይ ግልጽ አቅጣጫ አለመኖር፣ የሚያሻማና ግልጽ ያልሆነ የመሬት ግምገማ ሥርዓት መኖር፣ የመሬት አስተዳደር ደካማ ዶክመንት አያያዝ፣ በየቢሮዎች የተጠናቀረ መረጃ አለማግኘት፣ አተገባበሩ ውስብስብ መሆን በኢትዮጵያ ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ አለመኖር ውጤት ነው ተብሏል፡፡

በደርግ ጊዜ ከነበረው የአሁኑ ቢሻልም የመሬት አዋጅ ሆነ መሬት ነክ ጉዳዮች ሲወጡ ከላይ ባለው የመንግሥት አካል የሚወጣ በመሆኑ የማኅበረሰቡንና የአካባቢውን ሁኔታ ከግንዛቤ ያስገባ አይደለም የሚሉት መሳይ (ዶ/ር)፣ የመሬት አስተዳደር በማዕከላዊነት የሚወጣና በከፍተኛ የመንግሥት አካላት የሚዘጋጅ በመሆኑ ወደ ማኅበረሰቡ ሲወርድ የማያውቀው፣ ያልተገነዘበውና መረጃም ስለሌለው ለትግበራ አስቸጋሪነት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በመሆኑም ብዙ አዋጆችና የስትራቴጂ ዶክመንቶች እያሉ አሁንም ድረስ የአካባቢ ጉዳይ፣ የምግብ ዋስትና፣ የእርሻ፣ የምርታማነት ግር የሚታየው የሕዝቡን ችግር ከግምት ሳያስገባ በየቦታው ተበታትኖ የተዘጋጀ ፖሊሲ በመኖሩ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ለወደፊት ማኅበረሰቡ በተወካዩ በኩል በተገቢው ሁኔታ መሳተፍ እንዳለበት፣ ከእነዚህ በተጨማሪ ከኢንቨስተሩ፣ ከነጋዴው፣ ከምሁራን፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከፖለቲከኞች ከፓርቲዎች በቂ ሐሳብ ተሰባስቦ የማይዘጋጅ ከሆነና ገዥው ፓርቲ ወይም ሥልጣን ላይ ያለው አካል ብቻ ፖሊሲ አውጥቶ ለትግበራ የሚንቀሳቀስ ከሆነ፣ ከዚህ በፊት እንደነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጥማል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የዘርፉ ባለሙያዎችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አንድ ላይ ሆነው ወቅትን፣ ቦታንና አካባቢን ከግምት ባስገባ ሁኔታ ወጥነት ያለው ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ በአንድ ዶክመንት ተሠርቶ ለትግበራ ዝግጁ መሆን አለበት ሲሉም መሳይ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

እንደ መሳይ (ዶ/ር)፣ የመሬት ፖሊሲው ሲዘጋጅ እንደከዚህ በፊቱ በማዕከል እንደሚወጣ አዋጅ ወይም ፖሊሲ ቀርፆ ለሁሉም አካባቢ እንዲሆን ማድረግ ሳይሆን፣ አካባቢን ከግምት በማስገባት መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ለደጋ አካባቢ የሚሆን የመሬት ፖሊሲ ለቆላው እንደማይሆን በምሳሌ ያውሱት የአጥኚ ቡድኑ መሪ፣ እንደ አካባቢው ሁኔታ መተግበር የሚቻል ፖሊሲ  ሊኖር ይገባል የሚለውን በአፅንኦት አስቀምጠዋል፡፡ የመንግሥት አካላትም የተጠናውን ጥናት ከግምት በማስገባት ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ እንዲኖር ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አለ ብለዋል፡፡

ምሁራን ተሰባስበው ለኢትዮጵያ ይበጃል ያሉት ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ እንዲቀረፅ የተሠራው ጥናት፣ ለፎርም ፎር ሶሻል ስተዲስ የሚቀርብ ሲሆን፣ ይህ ተቋም ቀምሮ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ገቢ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ከምን እንደደረሰ ክትትል እንደሚያደርግና የመንግሥት አካልም ጥናቱን እንደ ግብዓት ወስዶ ፖሊስ ዶክመንቱን ያዘጋጃል የሚል እምነት እንዳላቸው አክለዋል፡፡

በ2002 ዓ.ም. የወጣው የፖሊሲ አወጣጥ ማንዋል አሳታፊነትን ቢገልጽም የመሬት ጉዳይ ላይ ምሁራን፣ የሚመለከታቸው አካላትና ከኅብረተሰቡ የተወከሉ እምብዛም ሲሳተፉበት አልተስተዋለም ተብሏል፡፡

አሁን ችግሩን ለመቅረፍ ሁለት መልካም አጋጣሚዎች በቀዳሚነት ይነሳሉ ያሉት መሳይ (ዶ/ር)፣ አዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብ አዋጅ ላለፉት አሥር ዓመታት ሲቪል ማኅበረሰቡ የፖሊሲ ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፍ ያደረገውን አዋጅ መሻሩ ጠንካራ ግብዓት ይዞ እንዲመጣ እንደሚያስችልና ሕገ መንግሥቱ ተሳትፎን የሚከለክል አንቀጽ ስለሌለው፣ አሳታፊ የሆነ የመሬት ፖሊሲ ለማዘጋጀት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

በጥናቱ ላይ ከተሰጠው ምክረ ሐሳብ ኢትዮጵያ አሳታፊ ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ ይኑራት፣ ከላይ ከመንግሥት አካል ብቻ  ወጥቶ ወደ ታች የሚወርድ የፖሊሲ አሠራር ሥርዓትን በማስቀረት ከታች ወደ ላይ፣ ከላይ ወደ ታችና የጎንዮሽ ውይይት የሚደረግበት ማለትም መንግሥት ከኅብረተሰቡ፣ ከምሁራን፣ ከሲቪል ማኅበረሰቡና ከዘርፉ ባለሙያዎች የተውጣጡ ሐሳቦችን በመጭመቅ ፖሊሲ ማዘጋጀት ይገባል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

በፌዴራል ደረጃ አጠቃላይ የመሬት ፖሊሲ ኖሮ ክልሎች እንደ አካባቢያቸው ሁኔታ ከብሔራዊ ፖሊሲው እየቀዱ የራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ቢደረግ ጠቀሜታው ይጎላል የሚለውም ከተሰጠው ምክረ ሐሳብ ይገኛል፡፡ 

ፖሊሲው ሲወጣ ለክልሎች ቦታ የሚሰጥ፣ የየአካባቢውን ባህል፣ ወግና ልማድ፣ እንዲሁም ሥነ ምኅዳርና የአየር ንብረት ከግምት ማስገባት ይጠበቅበታል የሚለውም ከተሰጠው ምክረ ሐሳብ አንዱ ነው፡፡

በማዕከል ደረጃ የተያዘውን የመሬት ጉዳይ ለቀቅ በማድረግ የምግብ እጥረትንና የተለያዩ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል የሚለውም  ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህ ጥናት ያተኮረው ኢትዮጵያ ብሔራዊ የመሬት ፖሊሲ ባይኖራትም በየተቋማቱና በየዘርፉ፣ በመመርያና በአዋጅ፣ እንዲሁም በስትራቴጂዎች ተበጣጥሰው የሚገኙትን ፖሊሲዎች መሠረት በማድረግ መሆኑን አጥኚው አስገንዝበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...