በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ዜጎችን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ለመከተብ የሚፈልጉ የውጭ ኤምባሲዎች፣ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት የሚችሉት የክትባት ዓይነት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የተፈቀደ ብቻ መሆን እንዳለበት መንግሥት ወሰነ፡፡
እስካሁን ክትባቱ የሚሰጠው በመንግሥት ስለሆነ፣ በተለያዩ ኤምባሲዎች በኩል ዜጎቻቸውን ለመከተብ ሲጠይቁ፣ የአስቸኳይ ጊዜ መመርያ የፈቀዳቸውን የክትባት ዓይነቶች ብቻ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እንደሚያደርግ፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የመድኃኒት ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ አብደላ ቃሶ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እነዚህን የክትባት ዓይነቶች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በግምገማ ላይ መሆናቸውን፣ አንደኛው ግምገማው ተጠናቆ ተጨማሪ የምርመራ ውጤቶች እንዲቀርቡ ጥያቄዎች መላካቸውን አቶ አብደላ ተናግረዋል፡፡ ግምገማውን አልፈው የገቡት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች አስትራዜኔካ ሳይኖቫክስ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌሎችም ክትባቶች የሚያመርቱ ድርጅቶች ለማቅረብ መንገድ ላይ መሆናቸውን፣ የአገሪቱን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ መድኃኒቶች እንዲገቡ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቀዱት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች፣ በተለይም ከሁለት እስከ ስምንት ዲግሪ ሴልሺየስ ቅዝቃዜ ቦታ መቀመጥ የሚችሉ ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌሎች በ70 እና በ80 ኔጌቲቭ ዲግሪ ሴሊሺየስ የሚቀመጡ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች፣ የሚከማቹበት መሠረተ ልማት ስለሌለ፣ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ አይደረግም ብለዋል፡፡
ከቻይና መንግሥት በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኤጀንሲዎች ዜጎቻቸውና ሠራተኞቻቸውን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሠራተኞቹን ለመከተብ ፈቃድ ከጠየቁት ውስጥ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ መሠረት የቻይና መንግሥት 18 ሺሕ ሳይኖ ቫክስ የተባለ የኮሮና ቫይረስ ክትባት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ 9,000 የቻይና ዜጎች ለመከተብ ፈቃድ አግኝቶ ማስገባቱን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በቻይና የሚመረተውን ሳይኖ ቫክስ፣ በህንድ የሚመረተውን ኮቫ ሼልድ፣ እንዲሁም የሩሲያውን ስፑትኒክ ፋይቭ ለማቅረብ ባለሥልጣኑ በግምገማ ሒደት ላይ የሚገኝ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በግዥ ወይም በዕርዳታ ለማስገባት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡