Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአፋር ክልል ሦስት ቀበሌዎች በሶማሌ ክልል የምርጫ ጣቢያነት መካለላቸው ተቃውሞ ቀሰቀሰ

የአፋር ክልል ሦስት ቀበሌዎች በሶማሌ ክልል የምርጫ ጣቢያነት መካለላቸው ተቃውሞ ቀሰቀሰ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም አፋርና ሶማሌ ክልሎችን ሲያወዛግቡ የነበሩ ሦስት ቀበሌዎችን የሶማሌ ክልል አድርጎ፣ በሥራቸው 32 የምርጫ ጣቢያዎችን ማዋቀሩ በአፋር ክልል ቅሬታና ተቃውሞ ቀሰቀሰ።

ምርጫ ቦርድ በጊዜ እጥረት ምክንያት 2007 ዓ.ም. የተዋቀሩ የምርጫ ጣቢያዎች ለዘንድሮ ምርጫ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በመደረጉ የተፈጠረ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይም ውሳኔ እንደሚሰጥበት እያስታወቀ ነው።

በአፋር ክልላዊ መንግሥት የአስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ ሦስት ቀበሌዎችን የክልሉ አጎራባች ወደ ሆነው የሶማሌ ክልል የአስተዳደር አካል ተካተው መቅረባቸው ትክክል አለመሆኑን ጠቅሶ፣ ማስተካከያ እንዲደረግ በመጀመሪያ ያመለከተው ለሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ነው። 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአሁኑ ወቅት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ነዋሪዎችም ተቃውሟቸውን እያሰሙ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድ አፋጣኝ ማስተካከያ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።

ምርጫ ቦርድ በአገር አቀፍ ደረጃ የምርጫ ክልሎችንና የምርጫ ጣቢያዎችን አደራጅቶ ከአንድ ወር በፊት ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ ከአፋር ክልላዊ መንግሥት አቤቱታ እንደቀረበለት ገልጾ ነበር፡፡ በዚህ መግለጫውም ከክልሉ የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ የዕጩዎች ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት ውሳኔ እንደሚሰጥበት አስታውቆ ነበር። 

ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ለአቤቱታው ምላሽ አለመስጠቱን በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል። በዚህም የተነሳ በተጠናቀቀው ሳምንት የተወሰኑ የአፋር ክልል ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን አደባባይ ይዘው እንደወጡ ከሥፍራው የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ነዋሪዎቹ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ የሚወስደውን የትራንስፖርት መንገድ ለአንድ ቀን ዘግተው መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የክልሉ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ አህመድ ካሊዮታ፣ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የምርጫ ክልልና የጣቢያዎች አደረጃጀት ላይ፣ የአፋር ክልል የአስተዳደር ወሰን አካል የሆኑ ሦስት ቀበሌዎች የሶማሌ ክልል የምርጫ ቀበሌዎች ሆነው መደራጀታቸው ትክልል እንዳልሆነ በመጥቀስ፣ የክልሉ መንግሥት አቤቱታውን እንዳቀረበ አረጋግጠዋል።  የክልሉ መንግሥት አቤቱታውን እንዳስገባ የገለጹት ቃል አቀባዩእስካሁን ምላሽ እንዳልተገኘና እሳቸውም ከዚህ ሌላ ተጨማሪ መረጃ የሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹ጉዳዩ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ከምርጫ ቦርድ መጠየቅ ትችላላችሁ፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን በአፋር ክልል ስለተስተዋሉ የጎዳና ላይ ተቃውሞዎች መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያዎች አወቃቀር መሠረት የሶማሌ ክልል አስተዳደር አካል ሆነው ተጠቅሰዋል የተባሉት ሦስት ቀበሌዎች አዳይቱ፣ ኡንዱፎና ገዳማይቱ መሆናቸውን ቅሬታቸውን ያቀረቡ የክልሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

እነዚህ ቀበሌዎች በሶማሌ ክልል የሚገኙ የምርጫ ቀበሌዎች ሆነው በሥራቸውም 32 የምርጫ ጣቢያዎች እንደተደራጁ ይገልጻሉ። ከክልሉ መንግሥት በተጨማሪ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ አቤቱታ በማሰማት ላይ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹም ምርጫ ቦርድ ዕርማት እንዲያደርግ በይፋ ደብዳቤ ጠይቀዋል።

ከእነዚህ ፓርቲዎች መካከልም የአፋር ሕዝብ ፓርቲ አንዱ ሲሆንስህተቱ እንዲታረም ለምርጫ ቦርድ በጽሑፍ ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁም ምንም ዓይነት ይፋዊ ምላሽ አለማግኘቱን ለሪፖርተር ገልጿል። 

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ለቦርዱ በላከው ደብዳቤ በአፋር ክልል የአስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ ብቻ ሳይሆኑ፣ በአፋር እምብርት ውስጥ ያሉ አካቢቢዎችን የተለያዩ አዳዲስ የምርጫ ጣቢያ ስያሜዎች በመስጠት፣ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ውስጥ ማካለሉ፣ የአፋር ክልልን ሉዓላዊነት የጣሰና ሕገ መንግሥቱንም የሚቃረን እንደሆነ አስገንዝቧል። 

‹‹በአገራችን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በበዙበትና አገራዊ አንድነት ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ በሆነበት ወቅት፣ እንዲህ ዓይነት ከፋፋይና ጠብ አጫሪ የሆነ አካሄድ ገለልተኛ ነው፣ ፍትሐዊ ምርጫን የማካሄድ አቅም አለው ብለን ካመንነው ተቋም የማንጠብቀውና እጅግ ያሳሰበን ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ሲል ፓርቲው ለቦርዱ በላከው ደብዳቤ አመልክቷል።

ቦርዱ አሳስቶ ያወጣው የምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር እጅግ አደገኛየሕዝቦችን አብሮ የመኖር ሰላማዊ መንፈስ የሚጎዳና የሚያደፈርስ እንደሆነ የሚገልጸው የአፋር ሕዝብ ፓርቲ፣ ያለ ቦታቸው የተከለሉት የምርጫ ጣቢያዎች ወደ ባለቤቱ ክልል እንዲመለሱና ምርጫ ቦርድም ለስህተቱ ይቅርታ መጠየቅ አለበት ብሏል። 

ይህ የመብት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ካላገኘ በምርጫ መሳተፉን ፋይዳ ቢስ እንደሚያደርገውና ራሱን ከምርጫው እንዲያገል የሚገፋው መሆኑን ያስታወቀው ፓርቲው፣ ‹‹ሕዝባችንን ይዘን አስፈላጊውን ትግል እንደምናደርግ እናስታውቃለን፤›› ብሏል።

ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን ለሚዲያዎች በሰጠው መግለጫ፣ የዘንድሮውን ምርጫ ለማካሄድ ካለው የተጣበበ ጊዜ አንፃር 2007 ዓ.ም. ምርጫ ጥቅም ላይ የዋለው የምርጫ ጣቢያዎች አወቃቀር ማሻሻያ ሳይደረግበት፣ በዘንድሮ ምርጫ አገልግሎት ላይ እንዲውል በመወሰኑ የተፈጠረ እንደሆነ አስታውቋል።

አቤቱታ የቀረበባቸው ሦስቱ ቀበሌዎችና በሥራቸው የተደራጁ የምርጫ ጣቢያዎች 2007 ዓ.ም. ምርጫ በሶማሌ ክልል ሥር ተካለው ምርጫ እንደተካሄደባቸው የሚገልጸው ቦርዱ2007 ዓ.ም. የምርጫ ጣቢያዎች አከላለል ለዘንድሮው ምርጫ በመላ አገሪቱ ጥቅም ላይ እንዲውል በመወሰኑ የተጠቀሱት ቀበሌዎች በሶማሌ ክልል ውስጥ ተካለው መቅረባቸውን ይገልጻል።

የምርጫ ጣቢያዎች አከላለልም ሆነ የምርጫ ጣቢያዎቹ አስፈላጊነት ምርጫ ለማካሄድ እንጂ፣ የአስተዳደር ወሰን ለማበጀት እንዳልሆነና ይህንንም የማድረግ ሥልጣን እንደሌለው ቦርዱ ገልጿል።

ነገር ግን ለምርጫው ሰላም ሲባል ማስተካከያ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥበት፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሰሞኑን ገልጸው ነበር። 

አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሔሬ ሀመዱ የተጠቀሱት ቀበሌዎች፣ የአፋርና የሶማሌ ክልሎችን ለበርካታ ዓመታት ሲያጋጩ እንደነበሩ ጠቅሰውየፌዴራል መንግሥት ጣልቃ በመግባት ሦስቱ ቀበሌዎች በአፋር ክልል የአስዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የሶማሌ ተወላጆች የሚኖሩባቸው ልዩ የአፋር ቀበሌዎች እንዲሆኑ 2007 ዓ.ም. ጥቅምት ወር መወሰኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ሦስቱም ቀበሌዎች በአፋር ክልል ሥር ሆነው ምርጫ እንደተካሄደባቸው በመግለጽ፣ ምርጫ ቦርድ የሰጠው ምላሽ የተሳሳተ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

ለዚህም ማስረጃ ማቅረብ እንደሚቻል የገለጹት ምክትል ሊቀመንበሩቅሬታ የቀረበባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ዘንድሮ አዲስ ስም ተሰጥቷቸው በሶማሌ ክልል ሥር መካለላቸውንም ተናግረዋል። 

ሪፖርተር ወደ ኅትመት ከመግባቱ አስቀድሞ በጉዳዩ ላይ በምርጫ ቦርድ የተላለፈ አዲስ ውሳኔ አለመኖሩን፣ ከቦርዱ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ አረጋግጧል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...