የማዳጋስካር ፕሮፌሽናሎች ከክለቦቻቸው ፈቃድ እንዳላገኙ ተገለጸ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በካሜሩን አስተናጋጅነት ከወራት በኋላ ለሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ይበቃ ዘንድ፣ ረቡዕ መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. የማዳጋስካር አቻውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡
ማዳጋስካር በፈረንሣይ ሊጎች የሚጫወቱ ወሳኝ ተጨዋቾቿን በኮቪድ-19 ሥጋት ምክንያት እንደማይሳተፉ እየተነገረ ይገኛል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 11 የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ከማዳጋስካር ጋር ላለበት ጨዋታ ከሳምንት በፊት በባህር ዳር ከተማ ተሰባስቦ ዝግጅት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ ባለፈው ረቡዕ ከማላዊ አቻው ጋር ባደረገው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ 4 ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡
የአቋም መፈተሻ ጨዋታው አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በቀጣይ ለሚጠብቃቸው ወሳኝ ጨዋታዎች ተጨዋቾቻቸው በምን ዓይነት አቋም ላይ እንደሚገኙ ለመገምገም ዕድል ፈጥሮላቸዋል ተብሏል፡፡
ምድቡን በጎል ክፍያ ተበልጣ ከአይቮሪኮስት ጋር በእኩል ሰባት ነጥብ የምትመራው ማዳጋስካር፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በተለይም በፈረንሣይ በሁለተኛውና በአንደኛ ዲቪዚዮን የሚጫወቱ ተጨዋቾቿ ከኢትዮጵያ ጋር ላለባት ወሳኝ ጨዋታ የክለቦቻቸውን ፈቃድ አለማግኘታቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡
የኢትዮ ኪክኦፍ ዘገባ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ የፈረንሣይ የእግር ኳስ ሊግ ባለፈው ሐሙስ ምሽት ባስተላለፈው ውሳኔ፣ በፈረንሣይ ሊግ በአንደኛና በሁለተኛ ሊግ የሚጫወቱ አፍሪካውያን ተጨዋቾች በሚቀጥለው ሁለት ሳምንታት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ አገራቸውን ወክለው መጫወት እንደማይችሉ አስታውቋል፡፡
ማዳጋስካር ችግሩን ተከትሎ ከአምስት የማያንሱ ፕሮፌሽናልና ወሳኝ ተጨዋቾች ከብሔራዊ ቡድኑ ውጪ በመሆናቸው ምክንያት፣ በአገሪቱ የውስጥ ሊግ ለሚጫወቱ ተጨዋቾች ጥሪ መደረጉ ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚህ መዘናጋት እንደሌለበት የሚናገሩ አልጠፉም፡፡
በሌላ በኩል ከሳምንት በኋላ በሜዳው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው የአይቮሪኮስት ቡድን፣ በአውሮፓና በሌሎችም አገሮች የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎችን ጥሪ በማድረግ የቡድን ስብስቡን ይፋ አድርጓል፡፡ ጥሪ ከተደረገላቸው ፕሮፌሽናሎች መካከል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወቱት የቶተንሃሙ ሰርጂዮ ኦሬር፣ የአርሰናሉ ኒኮላስ ፔፔ፣ የክርስቲያን ፓላሱ ዊል ፍሬድ ዛሃ፣ በጣሊያን ሴሪኤ የሚጫወቱት የኤሲ ሚላኑ ፍራንክ ኬሴይ፣ የላዚዮው ጂያን ዳንኤል እና በሌሎችም አገሮች በመጫወት ላይ የሚገኙ ፕሮፌሽናሎች መካተታቸው ታውቋል፡፡