Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተጋረጠበት አደጋ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ችግር ውስጥ መሆኑ መነገር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የኮንስትራክሽን ግብዓት ዕቃዎች ዋጋ ከሚገባው በላይ መሰቀል፣ የግንባታውን ዘርፍ በእጅጉ እየጎዳ ነው፡፡

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር እንዳመለከተውም፣ አሁን በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ እየታየ ያለው ችግር አጠቃላይ በግንባታ ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከመፍጠሩም በላይ፣ አፋጣኝ መፍትሔ ካላገኘ የበርካታ ፕሮጀክቶች ሥራ ሊቆም እንደሚችል ነው፡፡

በየትኛውም የግንባታ ዘርፍ ወሳኝ ከሚባሉ የግንባታ ግብዓቶች የሚጠቀሱት ሲሚንቶና የብረታ ብረት ምርቶች በአንድና በሁለት ዓመት ልዩነት ከእጥፍ በላይ ዋጋ መጨመራቸው ኢንዱስትሪውን ፈተና ውስጥ ከቶታል፡፡ የኮንትራክተሮችን ህልውናም እየተፈታተነ ነው፡፡

 እያሻቀበ የመጣውን የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መሸከም ያልቻሉ ኮንትራክተሮች ከዚህ በኋላ አቅም ኖሯቸው ለመቀጠል እንደሚቸገሩም ተገልጿል፡፡ ይህ ደግሞ አገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር የማኅበሩ አመራሮች ረቡዕ መጋቢት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል፡፡ የሲሚንቶና የብረታ ብረት ዋጋ ጎልቶ ይታይ እንጂ ማንኛውም የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ኢንዱስትሪው ላይም ሆነ አገር ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ታይቶ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባም ተገልጿል፡፡   

የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መናርን በተመለከተ እንደማሳያ የሚቀርቡት ሲሚንቶና ብረት ናቸው፡፡ 28 ብር ይገዛ የነበረ አንድ ኪሎ ብረት አሁን ላይ 65 ብር ገብቷል፡፡ ከ300 ብር ያልበለጠ ዋጋ የነበረው አንድ ኩንታል ሲሚንቶ አሁን ላይ በጥቁር ገበያ ወደ 700 ብር ማሻቀቡና በሚፈለገው መጠን አለመገኘቱ በእያንዳንዱ የኮንስትራክሽን ግንባታ ውስጥ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ለኮንትራክተሩም ሆነ ለፕሮጀክቱ አሥጊ እየሆነ መጥቷል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ ጫና ጎልቶ የታየው የብር የምንዛሪ ለውጥ ከተደረገበት ጥቅምት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ሆኖም ይህ የምንዛሪ ለውጥ የሚያመጣው ተፅዕኖ ታይቶ ማስተካከያ ባለመደረጉ የተፈጠረ ችግር መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡  

ብዙዎቹ ኮንትራቶች የተፈረሙት የዶላር የምንዛሪ ዋጋ ከመለወጡ ከጥቅምት 2010 ዓ.ም. በፊት ነው፡፡ በወቅቱ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ 24 ብር አካባቢ ሲሆን፣ የግንባታ ኮንትራቶቹ ሲፈረሙም በወቅቱ የነበረውን የግንባታ ግብዓት ዋጋ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ አሁን አንድ ዶላር 41 ብር እየተመነዘረ በመሆኑ፣ ጫናው ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ እያደገ የመጣና ዛሬ ላይ የደረሰ ስለመሆኑም እኚሁ የዘርፉ ባለሙያ ይጠቅሳሉ፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት 28 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ብረት 65 ብር መግባቱ እንዲሁም ነዳጅ በሌትር ከ16 ብር ወደ 25 ብር ማሻቀቡ ሁሉ ሲታሰብ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ ተቋቁሞ መቀጠል ከባድ መሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡ ስለዚህ አሁን በኢንዱስትሪው ላይ ያለው የግብዓት አቅርቦት እጥረትና ዋጋ ንረትን ተቋቁሞ ለመዝለቅ ፈታኝ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር ዩሱፍ መሐመድ (ኢንጂነር) በሰሞኑ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የዋጋ ንረቱን ተቋቁመን ለአንድ ዓመት ዘልቀናል፡፡ ከዚህ በኋላ መቋቋም ከባድ በመሆኑ መፍትሔ ያሻል ብለዋል፡፡ 

አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋን በ250 ብር ለመግዛት ታሳቢ ተደርጎ የተሞላ ጨረታ፣ አሁን ላይ 700 ብር ሲደርስ በሲሚንቶ ዋጋ ብቻ የግንባታውን ወጪ በእጥፍ እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡ አሁን የኮንትራክተሩ ጭንቀትም ይህ ነው፡፡ ብዙ ፕሮጀክቶች ቆመዋል፡፡ ይህም ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቶቹን ለማንቀሳቀስ ቢታሰብ እንኳን፣ የማጠናቀቂያ ዋጋቸው ከፍተኛ ስለሚሆን ኮንትራክተሮች ሥራውን ሲያቆሙ የያዟቸውን ሠራተኞች ወደ መበተን መግባታቸውም ሌላ አሳሳቢ ችግር ሆኖ ወጥቷል፡፡

የኮንስትራክሽን ማኅበሩ አመራሮች እንደሚገልጹትም፣ በርካታ ኮንትራክተሮች ደመወዝ መክፈል ባለመቻላቸው ሠራተኞችን እየቀነሱ ነው፡፡ ሥራ ያላቋረጡ ቢሆንም፣ ደመወዝ በወቅቱ ለመክፈል እየተቸገሩ ነው፡፡ እንዲህ እያሉ መቀጠል የሌለባቸው በመሆኑ ጉዳዩ አፋጣኝ መልስ ያሻዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

‹‹በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙ ሥራዎች ቆመው በሲሚንቶና ብረት እጥረቶች ስላለባቸውና ኮንክሪት መሙላት አቅቷቸዋል፡፡ በዚህ ሒደት አንድ ዓመት ተንጠልጥሎ ተቆይቷል፡፡ አሁን ኮንትራክተሩ ያለውን ነገር ስለጨመረ ከዚህ በኋላ መክፈል ሲያቅተው ሠራተኛ ወደ መበተን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ዩሱፍ ይኼ አገራዊ ጉዳት የሚያመጣ በመሆኑ ጉዳዩ በአገር ደረጃ እንደ ከባድ ጉዳይ ታይቶ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ከወቅታዊው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴዎች ጋር ያነጋገርናቸው አንድ ኮንትራክተር እንዳመለከቱት፣ አሁን እየታየ ያለው ችግር እየተገለጸ ካለው በላይ ነው ይላሉ፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ የሚባል ገንዘብ የሚፈስበት ይህ ዘርፍ ችግር ውስጥ መግባቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን የሚነካካ መሆኑ መታሰብ አለበት፡፡

ከግብርናው ዘርፍ ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሠራተኛ የያዘውና በአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁነኛ ድርሻ ያለው ይህ ዘርፍ አሁን እየታየ ባለው ችግር እየተመታ ከቀጠለ አገራዊ የኢኮኖሚ ጉዳቱ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡

በተለይ ከዋጋ ግሽበትና ከውጭ ምንዛሪ ለውጥ ጋር ተያይዞ ሲታይ በሦስት ዓመት ውስጥ የዶላር ምንዛሪ ዋጋ በ60 በመቶ ጨምሯል፡፡ አሁን ባለው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ መሠረት ደግሞ፣ የዋጋ ግሽበቱ 20 በመቶ ስለሆነ እነዚህን ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ያገናዘበ የኮንትራት ማሻሻያ መደረግ ነበረበት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ2011 ዓ.ም. በፊት የተፈረሙ ኮንትራቶች በሙሉ አደጋ ላይ መሆናቸውን የሚያመለክት ስለመሆኑ ያስታወሱት እኚሁ ኮንትራክተር፣ ችግሩ በኮንትራክተሩ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህም አልፎ ሌሎች ቢዝነሶችንም ይነካካል ብለዋል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ በዋጋ መወደድና መሰል ምክንያቶች የተስተጓጎለ ፕሮጀክት ጉዳይ ወደ ባንክና ኢንሹራንሶች መሄዳቸው ነው፡፡

ይህም ፕሮጀክቱ አልሄድ ሲል አሠሪው ወይም የፕሮጀክቱ ባለቤት ሥራው አልተሠራልኝም ብሎ ኮንትራክተሮች ያስያዙትን ቢድ ቦንድና ዋስትና አምጡ ብሎ ወደ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ይሄዳል፡፡ ስለዚህ ከኮንትራክተሮች በላይ በሆነ ምክንያት የተፈጠረ ችግር ወደ ባንኮችና ኢንሹራንሶች በመሄድ ለሰጣችሁት ዋስትና የተያዘውን ገንዘብ አምጡ እየተባሉ ነውና ችግሩ አንድ ቦታ ላይ የማይቆም መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

ፕሮጀክቶች በቆሙ ቁጥር ባንኮች ለፕሮጀክቶቹ የሰጡት የቅድሚያ ክፍያ ቢድ ቦንድና ኢንሹራንስ ጥያቄ በመጨመሩ፣ ባንኮቹ በጉዳዩ ላይ ብሔራዊ ባንክን እስከመምከር ደርሰዋል፡፡ በቅድመ ክፍያ ዋስትናና ከተያያዥ ዋስትናዎች ጋር ተያይዞ ወደ ባንኮች የሚመጣው ጥያቄ መጨመር ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ የሚጠይቅ ሆኖ በመገኘቱ ችግሩ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ለተለያዩ ግንባታዎች የቅድመ ክፍያ ዋስትናና መሰል ዋስትና የሰጡ ባንኮች ለዋስትናው የሰጧቸው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ይህንን የዋስትና ዓይነት እንዳይሰጡ በብሔራዊ ባንክ ታግደዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም፣ ከዚሁ ዋስትና ጋር ተያይዞ 11 ባንኮች አዲስ ዋስትና እንዳይሰጡ በብሔራዊ ባንክ ታግደዋል፡፡ በመሆኑም ያለው አካሄድ አደገኛ ነው፣ በዚህ አካሄድ አንድ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር አይኖርም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በውሉ መሠረት ስለመገንባታቸው ደግሞ ባንኮችን የሚፈትን ነገር ሊመጣ ይችላል ተብሎ እየተሠጋም ነው፡፡ ይህም ለእያንዳንዱ የግንባታ ፕሮጀክት ቢድ ቦንድ የተያዘ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በአግባቡ አልተሠራልኝም ያለ አካል ባንኮችን ያስያዛችሁትን ቢድ ቦንድ ክፈሉ የሚል መሆኑ ባንኮችን ችግር ውስጥ ሊከት ስለሚችል ሊታሰብበት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር ኢንጂነር ያሲን በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ለኮንትራክተሮች ቅድሚያ ክፍያ እንዳይፈጽሙ የሚለው ዕገዳም ሌላው ለኮንትራክተሩ ፈተና የሆነ ጉዳይ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወሰዳቸው ዕርምጃዎች ብዙ ባንኮች ላይ የቅድመ ክፍያዎችና ቢድ ቦንድ እንዳይሰጡ መታገዳቸው ችግር ፈጥሯል፡፡ በዚህ ምክንያት አንዴ ጋራንቲ አስይዞ ሥራ የጀመረ ሌላ መጠቀም የማይችልበት ደረጃ በመድረሱ ኮንትራክተሮች እየተቸገሩ ነው፡፡ ጋራንቲ ከሌላ ቦታ ለማምጣት ያስያዘውን ጋራንቲ ማስለቀቅ ስለማይቻል ኮንትራክተሩ የራሱ ባልሆነ ጥፋትና ችግር እየተጎዳ ያለበት ሒደት ከፍተኛ ነው፡፡ ኮንትራክተሩ ሥራ ቢያገኝ የጨረታ ማስያዣ ቢድ ቦንድ ማሠራት የማይችል መሆኑ የኮንትራክተሩን ችግር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል የሚል እምነት አላቸው፡፡  

የማኅበሩ አመራሮች ሌላው ችግራቸው ብለው የጠቀሱት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በእጅ የሚያዘውን የገንዘብ መጠን ከ1.5 ሚሊዮን ብር ወደ 200 ሺሕ ብር ማውረዱ ነው፡፡ ‹1.5 ሚሊዮን ብር በላይ መያዝ አይቻልም› የሚለው ሕግም በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ይታወቅ ነበር ያሉት ኢንጂነር ግርማ፣ ጭራሽ ወደ 200 ሺሕ ብር መውረዱ የነበረውን ችግር አብሶታል ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ከከተማ ራቅ ብለው የሚሠሩ እንደ መንገድ፣ ድልድይና የመሳሰሉት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን የሚያንቀሳቅሱ ኮንትራክተሮች በዚህ ገንዘብ ሥራቸውን መሥራት እንዳይችሉ ያደረገ በመሆኑ ይህም አሠራር እንዲታይላቸው ይፈልጋሉ፡፡

ችግር ውስጥ ያለውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመታደግ የተለያዩ መፍትሔዎች ተሰንዝረዋል፡፡ በዋናነት የሚጠቀሰው ደግሞ የግንባታ ኮንትራቶችን መከለስ የሚለው ነው፡፡ ያለውን የዋጋ ንረት ለመፍታትም ሥራ ተቋራጮችና ግብዓት አምራቾች በቀጥታ የሚገናኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡

በዚህ ረገድ ያነጋገርናቸው ኮንትራክተሮች፣ የዋጋ ግሽበቱን ያገናዘበ ማስተካከያ ካልተደረገ ከዓመታት በፊት በወቅቱ በነበሩ ዋጋዎች በተፈረሙ የግንባታ ኮንትራቶች አሁን ባለው ዋጋ ይሠሩ ከተባለ ለኮንትራክተሩም ለፕሮጀክቱም የማይበጅ በመሆኑ መንግሥት ይህንን ታሳቢ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

እኚሁ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ባለሙያ ያለውን ችግርና ከዓመታት በፊት የተፈረሙ ኮንትራቶች አሁን ባለው ዋጋ ይፈጸሙ ቢባል ያለውን ልዩነት ለማሳየት እንደ ምሳሌ ያነሱት የታላቁ ህዳሴ ግድብን ነው፡፡

የህዳሴ ግድብ ሲጀመር በ4.8 ቢሊዮን ዶላር ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር፡፡ ግንባታው ሲጀመር በወቅቱ የአንድ ዶላር ምንዛሪ ዋጋ 16 ብር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የዶላር ምንዛሪ 41 ብር ገብቷል፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት 80 ቢሊዮን ብር ነበር፣ አሁን 180 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ እዚህ የደረሰው አንድም በምንዛሪ ለውጥና በዋጋ ግሽበት ነው፡፡ ሌሎችም ፕሮጀክቶች በዚህ አንፃር ሊታዩ ይገባል፡፡ የብር ምንዛሪ ለውጡንና የዋጋ ግሽበቱን ያገናዘበ ማስተካከያ ያሻል ብለው ያምናሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንዎች የቅድሚያ ክፍያና ለኢንሹራንስ የሚያስይዙት የገንዘብ መጠን እየጨመረ መሆኑ፣ ባንኮቹንም ችግር ውስጥ ስለሚከት ማስተካከያ መደረግ አለበት ብለው ያምናሉ፡፡

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የአገሪቱ ባንኮች ለተለያዩ ግንባታዎች የሰጡት የቅድመ ክፍያና ተያያዥ ዋስትናዎች ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ይህም አገሪቱ ባንኮች ካላቸው የካፒታል መጠን በላይ በመሆኑ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ የተፈጠረው ችግር ብዙ ቢዝነሶችን የሚነካ መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ መንግሥት ትኩረት ያድርግበት እየተባለ ነው፡፡  

አጠቃላይ ዘርፉን ከባህሪው አንፃር ማየት ያስፈልጋም ተብሏል፡፡ የማኅበሩ የቦርድ ሊቀመንበር ኢንጂነር ግርማ እንደገለጹት ደግሞ፣ በመንግሥት በኩል ኮንትራክተሮች የዋጋ ማስተካከያ እንደተወሰነላቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በፊት የዋጋ ማካካሻ እንዳይሰጥ የሚለው ተነስቶ ማካካሻው እንዲሰጥ ሰሞኑን መወሰኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች