Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ የምርጫ ማኒፌስቶውን ይፋ አደረገ

ኢዜማ የምርጫ ማኒፌስቶውን ይፋ አደረገ

ቀን:

በሥራ ላይ ያለው የአገሪቱ የፌዴራል አወቃቀር ሥርዓት በዋናነት በዘርና በቋንቋ ላይ መመሥረቱ ለአገራዊ አንድነትም ሆነ የሕዝብ አብሮነትን አደጋ ላይ መጣሉን የገለጸው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ቢይዝ ለዚህ ችግር መፍትሔ ማዘጋጀቱን ማኒፌስቶውን ይፋ ሲያደርግ አስታወቀ፡፡

ፓርቲው ለዚህና መሰል ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሔ ይሰጣል ያላቸውን ሐሳቦች የገለጸው ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የምርጫ ማኒፌስቶው አማካይነት ነው፡፡ የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ የምርጫ ማኒፌስቶውን ይፋ አድርገዋል፡፡

በአገሪቱ ያለውን በዘርና በቋንቋ የተመሠረተ የፌዴራል ሥርዓት ለማስተካከል ያቀረባችሁት መፍትሔ ምንድነው ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ፣ ‹‹እስካሁን ያለው የፌዴራል አወቃቀር ቋንቋን፣ ብሔርንና ዘርን ብቸኛ ቅድመ ሁኔታ ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ወጣ ስንል ሰፋ ባሉ መሥፈርቶች ለምሳሌ ባህል፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ አስተዳደራዊ ፍትሕ፣ ወዘተ በሚለው የተቃኘ ይሆናል፤›› በማለት የፓርቲው መሪ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በፌዴራል ሥርዓት ላይ ችግር የለብንም፤›› በማለት ያብራሩት የፓርቲው መሪ፣ ያልተማከለ አስተዳደር እንደሚያስፈልግም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ያልተማከለ አስተዳደሩም ከቀበሌ ጀምሮ መሆን አለበት፡፡ የቀበሌው ሕዝብ የቀበሌውን መሪዎች መምረጥ፣ እንዲሁም እያለ ደረጃ በደረጃ የሚሄድ ከታች ጀምሮ የሚከናወን ራስን በራስ የማስተዳደር ሥርዓት መኖር አለበት፤›› የሚል እምነት ፓርቲው እንደሚያራምድ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡

የዘውግ ፅንፈኝነት የአገሪቱ ሥጋት እንደሆነ የገለጸው ኢዜማ ከዚህ ባሻገር ግን፣ ‹‹በቅርቡ እያቆጠቆጠ የሚገኘው የሃይማኖት ፅንፈኝነት በአሁኑ ወቅት ከምናልባታዊ የደኅንነት ሥጋት፣ ወደ ተጨባጭ የደኅንነት ሥጋት እየተቀየረ ይገኛል፤›› ሲል ሥጋቱን ገልጿል፡፡

ስለሆነም የዘውግ ማንነትን መሠረት ያደረገውን አግላይ መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥርዓትና አደረጃጀትን፣ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት ወደ የሚስተናግዱበት መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመቀየር ቁርጠኛ መሆኑንም ኢዜማ በማኒፌስቶው ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹ለተቋም ግንባታ ከፍተኛ ዋጋ በመስጠት በከፍተኛ ደረጃ በሠለጠኑ ባለሙያዎች የሚመሩ የደኅንነት ማኅበረሰብ፣ የመከላከያ ኃይልና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኛነት በፀዳ መልኩ የሚገነቡ ሲሆን፣ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የአገርና የሕዝብ ደኅንነትና ጥቅምን የሚያስጠብቁ ባለሙያዎች ተገቢውን ክብር እንዲያገኙ፤›› እንደሚሠራም ፓርቲው ይፋ አድርጓል፡፡

በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር አጨቃጫቂ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የሆነውን ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያን በተመለከተ ደግሞ፣ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ድንጋጌዎች በሕዝበ ውሳኔ አማካይነት እንዲለወጡ እንደሚደረግም አስታውቋል፡፡

መንግሥት ከዜጎች ጋር ኢኮኖሚው ውስጥ ወደ ውድድር ፈፅሞ መግባት የለበትም ብሎ እንደሚያምን የገለጸው ኢዜማ፣ ‹‹በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግሥት ሚና ውድድሩ ጤናማ እንዲሆን ሕግ በማውጣትና በመቆጣጠር ያላግባብ የሚበለፅጉ እንዳይኖሩ፤›› እንደሚሠራም በማኒፌስቶው ገልጿል፡፡

ለዘመናት መልስ ያላገኘውን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄን በተመለከተ ደግሞ፣ ‹‹ጉዳዩን በማያዳግም ሁኔታ ለመመለስ መሬት በግል፣ በማኅበረሰብና በመንግሥት ይዞታነት እንዲያዝ ያደርጋል፤›› በማለት ከመሬት ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ትልሙን ይፋ አድርጓል፡፡

ኢዜማ የፖለቲካ እምነቶቹን፣ አገራዊ ራዕዮቹን፣ ተልዕኮዎችንና የማስፈጸሚያ ሥልቶቹን በዝርዝር ያቀረበበት የምርጫ ማኒፌስቶ ስምንት ክፍሎችን ያካተተ ሲሆን፣ በአገሪቱ ጥያቄ ሆነው የዘለቁ የደኅንነት፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የውጭ ጉዳይን የተመለከቱ የፓርቲውን አቋሞች አካቶ በ97 ገጾች ተቀንብቦ ፋ ሆኗል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...