ተመዝጋቢዎች 70 በመቶ ወይም መቶ በመቶ የከፈሉ መሆን አለባቸው
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ቢሮ በ2005 ዓ.ም. የ20/80 እና የ40/60 የቤት ፕሮግራሞች ተመዝጋቢ ሆነው ዕጣ ያልወጣላቸው ነዋሪዎች፣ በማኅበር ተደራጅተው የቤት ግንባታ እንዲያከናውኑ የሚያስችል ምዝገባ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ቢሮው ከስምንት ዓመታት በፊት ለሁለት ዓይነት የቤት አማራጮች ተመዝግበው ዕጣ ያልወጣላቸው ተመዝጋቢዎች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበር በማቋቋም በጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለማድረግ ያወጣውን መመርያ አጠቃላይ ሁኔታ በከተማ አስተዳደሩ አዳራሽ ለመገናኛ ብዙኃን ማክሰኞ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ መስከረም ዘውዴ (ዶ/ር) በመግለጫው ወቅት እንደገለጹት፣ የተዘጋጀው መመርያ የቤት ቁጠባ ክፍያቸውን ያላቋረጡ የ2005 ዓ.ም የ40/60 እና 20/80 ተመዝጋቢዎች በማኅበር ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት ለመሥራት እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ አቅሙና ፈቃደኝነቱ ያላቸው ተመዝጋቢዎች ለአማራጩ መመዝገብ እንደሚችሉ፣ የከተማ አስተዳደሩም የቦታና የመሠረተ ልማት አቅርቦት እንደሚያዘጋጅ አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አማራጭ የቤት ልማት አቅርቦት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ ታምራት፣ መንግሥት በቤት ልማት ፕሮግራም ለአሥራ ስድስት ዓመታት ቤት ሲገነባ ቢቆይም፣ የአቅርቦትና ፍላጎት መመጣጠን እንዳልታየ ገልጸው፣ የተለያየ አመራጮችን ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ፣ የቤት ልማት ማኅበራት በራሳቸው ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲገነቡ የቤቶች አስተዳደር ቢሮ አማራጭ መመርያ እንዳዘጋጀ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
አዲሱ መመርያ በ2005 ዓ.ም. ተመዝግበው 70 በመቶ፣ እንዲሁም መቶ በመቶ የከፈሉ የቤት ፈላጊዎችን በማኅበር ተደራጅተው ቤቶች እንዲገነቡ ለማድረግ የተዘጋጀ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት በሚቆይ የበይነ መረብ ምዝገባ ማንኛውም ቤት ፈላጊ በመረጠው የቤት ዓይነት መሠረት፣ ቢሮው በዕጣ በሚደለድለው የጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤት ማኅበር ለመደራጀት የተዘጋጀውን ቅፅ ሞልቶ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡
በአምስት ክፍላተ ከተሞች የመሬት ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ጳውሎስ፣ የርክክብ ሒደቱ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች እንደተጠናቀቀና በየትኞቹ ክፍላተ ከተሞች ግንባታዎቹ እንደሚከናወኑ እንደሚገለጽ አስታውቀዋል፡፡ የበይነ መረብ ምዝገባው እንደተጠናቀቀ ተመዝጋቢዎች በቡድን ተደራጅተው ወደ ማኅበራት ማደራጃ ሄደው ሕጋዊ ሰውነት የሚይዙ ሲሆን፣ የቤት ሥራ ማኅበራት ተብለው ከተዋቀሩ በኋላ የቤት ልማት ቢሮው የፋይናንስ፣ የመሬት ርክክብና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የማደራጀት ሥራና ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አስረድተዋል፡፡
በተያዘው ዓመት አሥር ሺሕ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚዎችን በመቶ ማኅበራት ለማስተናገድ እንደታቀደ ያስተወቁት አቶ ጳውሎስ፣ በገላንና በባሻ ወልዴ ችሎት ለመንግሥት ሠራተኞች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤት የግንባታ አፈጻጸምን መነሻ በማድረግ፣ በዚህኛው አማራጭ የሚገነቡ ቤቶችን እንደ ሕንፃዎቹ ዓይነት በ18 ወራት ለማጠናቀቅ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
ቢሮው ከዲዛይን አማራጭ፣ ከኮንትራክተርና ከአማካሪ ድርጅት ጥቆማ፣ እንዲሁም የግንባታ ክትትልና የፋይናንስ ድጋፎችን ከማመቻቸት ውጪ በግንባታዎቹ ላይ ሚና እንደማይኖረው የተገለጸ ሲሆን፣ ተቋራጭና አማካሪን ድርጅቶችን የመቅጠር፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የማከናወን እንቅስቃሴ በተደራጁት ማኅበራት አማካይነት እንደሚከናውን በመግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡
መመርያው በ2005 ዓ.ም. በቤት ልማት ፕሮግራሞች ተመዝግበው ስማቸው በምዝገባ መረጃ ቋት ውስጥ የሚገኙና በኅብረት ሥራ ማኅበር ተደራጅተው በራሳቸው አቅም ቤት ለመገንባት ፍላጎት ያላቸውና የቁጠባ ሒሳብ ያልዘጉ፣ የቤት ግንባታውን ወጪ 70 በመቶ በኅብረት ሥራ ማኅበሩ ስም በሚከፈት የዝግ ሒሳብ ማስቀመጥ የሚችሉና እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ያወጣቸውን የግንባታ ሕጎች በማክበር በኅብረት ሥራ ማኅበሩ አማካይነት ከአባላቱ ጋር በጋራ ሕንፃ የመኖሪያ ቤት ለመገንባት የተስማሙ የዕድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያስረዳል፡፡
የሚገነቡት ቤቶች የሕንፃ ከፍታ ከባለ አራት እስከ 15 ወለል የሚደርስ ሲሆን፣ ስፋታቸው በአማካይ ለባለ አንድ መኝታ ቤት 60 ካሬ ሜትር፣ ለባለ ሁለት መኝታ 75 ካሬ ሜትርና ለባለ ሦስት መኝታ የውስጥ መተላለለፊያን ጨምሮ 105 ካሬ ሜትር ይሆናል፡፡ በወቅቱ በሚኖረው የገበያ ዋጋ ተለዋዋጭነቱ ታሳቢ ሆኖ የቤቶቹ ግንባታ ግምት የወጣላቸው ሲሆን፣ በዚህም የሕንፃ ከፍታቸው ባለ ዘጠኝ ወለል ላይ ያረፉ ባለ አንድ መኝታ ቤቶች 882,086.75 ብር፣ ባለ ሦስት መኝታ 1,104,025.71 ብር፣ እንዲሁም የቤት ስፋታቸው 105 ካሬ የሆኑ ባለ ሦስት መኝታ ቤቶች 1,547,300.53 ብር ግምታዊ ዋጋ ወጥቶላቸዋል፡፡
በሌላ በኩል 13ኛ ወለል ላይ የሚያርፉ ባለ ሁለት መኝታ ቤቶች 926,023.38 ብር፣ ባለ ስድስት መኝታ ቤቶች 1,157,529.23 ብር፣ እንዲሁም 105 ሜትር ካሬ ላይ ያረፉ ባለ ሁለት መኝታ ቤቶች 1,620,540.92 ብር መሆኑን ከወጣላቸው ግምታዊ ዋጋ መረዳት ተችሏል፡፡