በኢትዮጵያ ያሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የለመዱት ምርጫን ማጀብ እንጂ ተወዳድሮ ማሸነፍ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባን ባካሄደበት ወቅት፣ የአሥር ዓመቱን የልማት ዕቅድና ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከአባላቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ነው፡፡
በግንቦት ወር በሚካሄደው ምርጫ ላይ ላለመሳተፍ እያፈገፈጉ ያሉ ፓርቲዎችን አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹የሕወሓትን ምርጫ ሲያጅብ የነበረ ፓርቲ አሁን ዛሬ ምርጫ አልወዳደርም ቢል የአጃቢነት ሱስ ስላለበት እንጂ፣ የዘንድሮ ምርጫ ከአምናው ስለሚያንስ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በምርጫው አንወዳደርም የሚሉ ፓርቲዎችን መንግሥት ከግማሽ መንገድ በላይ አነጋግሯል፣ ለምኗል፣ ደግፏል፣ እንደ ግለሰብም አነጋግሬያቸዋለሁ፣ ሽማግሌም ልከንባቸዋል እንዳይወጡ ለምነናቸዋል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ለአብነት በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ ‹‹ተወዳደሩ፣ እናግዛችሁ ብለን ሽማግሌ ባለበት ጠይቀናቸዋል፤›› በማለት በምሳሌነት አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ የሚፎካከሩ ዕጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ይሁን አንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ አንዳንድ ተፎካካሪዎች ለመወዳደር ፍላጎት እያሳዩና ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የእነዚህን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ እንደሚያስተናግድ ተስፋ እንደሚያደርጉና ማድረግም አለበት ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
‹‹ማንም የፖለቲካ ፓርቲ ለመወዳደር ፍላጎት ካለው ደግፈንና አግዘን እንዲወዳደር ማድረግ አለብን፤›› ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የሆነ ሕግ ጠቅሶ ፓርቲዎችን ከመግፋት ሕጉን ክፍት አድርጎ ማስገባት እንደሚበጅ በመጥቀስ ‹‹እኔም በፅኑ አምናለሁ፣ ምርጫ ቦርድም ይህን ያደርጋል የሚል ተስፋ አለኝ፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ አስመልክተው፣ መንግሥት ዘመቻውን ከመጀመሩ በፊት በርካታ የሽምግልና ጥረቶች እንደተደረጉ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጦርነት ጨዋታችንና ድራማችን ነው እንደተባለው፣ ለማንም አልበጀም ተው ተብለው ቢለመኑ አልሰሙም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዕብሪት የወለደው እንቅስቃሴ አደገኛ እንደሆነና ውድቀትን እንደሚያስከትል በመግለጽ፣ በእንቅስቃሴ ያሉ ፓርቲዎችን ከዕብሪት መጠበቅ አለባችሁ ብለዋቸዋል፡፡
የሕወሓት የጦርነት ፈላጊነት አሳዛኝነት ላለፉት ሃያ ዓመታት ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የትግራይ ሕዝብ በሴፍቲኔት ሲረዳ መቆየቱ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ሁሉም የትግራይ ክልል አመራር ጦርነት ሰባኪ፣ ግጭት ጠማቂ፣ የጦርነት ተንታኝ በመሆንና እኛ ከጠፋን አፍሪካ ቀንድ ትታመሳለች የሚለውን አምነው ፈረንጆቹን አሳምነዋል ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አንበሳ ገዳይ እንጂ ገበሬ ገዳይ ሲባል አልነበረም፣ የሚታወቀው እናም አርሶ አደር እየገደለ እንደ አንበሳ ገዳይ የሚፎክር አካል ነው ያየነው፤›› ብለዋል፡፡
ሕወሓት በትግራይ ክልል በ200 ቦታዎች ጥቃት እንደፈጸመና ከ30,000 በላይ እስረኞችን ፈትቶ እንደለቀቃቸው ገልጸዋል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሕወሓት ተይዘው በእግራቸው እንዲጓዙ ይደረግ እንደነበር፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ሙሉ በሙሉ ከታገቱበት መለቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የተከሰተው ዓይነት ግጭት የተከሰተባቸው አካባቢዎችንና የደረሰውን የንፁኃን ሞት በተመለከተ ሲገልጹ በኢራቅ 60 በመቶ፣ አፍጋኒስታን 25 በመቶ፣ በሶሪያና በየመን ተመሳሳይ ዓይነት የንፁኃን ዜጎች ሞት እንዳጋጠመ በመጥቀስ በትግራይ ክልል የነበረውን እንቅስቃሴ ከሞላ ጎደል በተሳካ ሁኔታ እንደተካሄደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
በግጭት ወቀት በከፍተኛ ሁኔታ ንፁኃን ዜጎች እንደሚጠቁ እየታወቀ ከመጀመሪያው ጥሩ መፍትሔ የነበረው ግን ውጊያ አለመጀመር ነበር በማለት ውጊያ ከተጀመረ በኋላ ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈርና ሌሎች ፕሮፓጋንዳዎች የተለመዱ ናቸው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ መንግሥት በትግራይ ክልል ሲያደርግ የነበረውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ በተመለከተ ሲገልጹ፣ የሚመለከታቸው አካላት በማይካድራ፣ በመተከልና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱት አሰቃቂ ግድያዎችና መፈናቀሎች ላይ ድምፃቸው አለመሰማቱ፣ የሕወሓት ኃይሎች ከአገሪቱ በዘረፉት ሀብት በተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሠሩ ግለሰቦቹን በመደለል በማሳመናቸው ነው ብለዋል፡፡
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕወሓት ማለት ንፋስ ላይ የተበተነ ዱቄት ማለት ነው፣ ከዚህ በኋላ ሰብስበን ዱቄት ልናደርገው አንችልም፤›› ሲሉ ሕወሓት በድርጅታዊ ቁመና ላይ እንደማይገኝ ተናግረዋል፡፡
አሁን ስለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ጥቃትና ችግር እየተናገሩ ያሉ ሰዎች ስለሰሜን ዕዝ እንደሚያነሱ፣ በየመንገዱ ተጨፍጭፈው በመኪና ሲረገጡ ማንም ምንም ያለ አልነበረም ብለዋል፡፡
በሕወሓት ምክንያት ለወደሙ መሠረት ልማቶችና ድጋፍ መንግሥት 40 ቢሊዮን ብር ያህል እንዳወጣ ጠቅላይ ሚኒስተሩ አስታውቀዋል፡፡ ጩኸት ሁሉ አንድ ቦታ የሚሰማበት ምክንት የዓይን መንሸዋረር እንጂ፣ የበደል ልክን አያሳይም በማለት አክለው ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የኤርትራ ወታደሮችን መግባት አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያስረዱ፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር አራትና አምስት ጊዜ ውይይት መደረጉን አስራውቀዋል፡፡
የወታደሮቹን መግባትን አስመልክቶ የኤርትራ መንግሥት እንደ ምክንያት የሚያነሳው ላለፉት ሃያ ዓመታት የሕወሓት ኃይሎች ከፈጸሙት ጥፋት በተጨማሪ፣ አሁንም ወደ ውጊያ እንድንገባ ሮኬት ተኩሰውብናል የሚልና በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አካባቢ ላለፉት ሃያ ዓመታት የኢትዮጵያ ወታደር የነበረበትን ምሽግ ለቃችሁ ወጥታችኋል የሚል ነው፡፡
‹‹በመሆኑም የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ መሀል ከተሞች በመሄዱ ምክንያት እዚያ ስታባርሩት ተገልብጦ ወደ እኛ ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለሆነውም የአገር ደኅንነት ሥጋት አለብን፡፡ ለዚህም ድንበር አካባቢ ያሉትን ቦታዎች ይዘናል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ጦር ዜጎቹን የሚቆጣጠር ከሆነ ለቀን እንወጣለን፤›› ማለታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ዘረፋና አስገድዶ መድፈርን፣ እንዲሁም ሌሎች ጥፋቶችን አስመልክቶ ሁለቱ መንግሥታት በቅርብ ተገናኝተው ውይይት ያደርጉበታል ብለዋል፡፡
‹‹በሌላ በኩል የአማራ ልዩ ኃይል በትግራይ ክልል ተሰማርቷል፣ በመሆኑም ለቆ ይውጣ የሚል ግፊት ከውጭ ኃይሎች የሚሰማው ሐሳብ፣ የኢትዮጵያ ኃላፊነት ከመሆኑም በላይ መንግሥት ከፈለገ የአማራ ልዩ ኃይልን ጅግጅጋ ሊያሰማራ ይችላል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ከህዳሴው ግድብ ጋር በተገናኘ ግድቡ ዘርፈ ብዙ ችግር እንዳለበት፣ ኢትዮጵያ ሱዳንንም ሆነ ግብፅን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት፣ በተመሳሳይም ኢትዮጵያውያንም በጨለማ የመኖር ፍላጎት የላቸውም ብለዋል፡፡
‹‹እኛ የዓባይን ውኃ አልገደብንም፣ ነገር ግን እየተከለከልን ያለው የዝናብ ውኃ እንዳንገድብ ነው፣ እናም ዝናብን አትጠቀሙ ማለት ትንሽ ይከብዳል፤›› በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ምንም ፈታኝ ቢሆንም የግድቡ ሁኔታ በተገባው ቃል መሠረት እንደሚከናወን ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል፡፡
የህዳሴው ግድብ ከታሰበለት ጊዜ በመዘግየቱ ምክንያት ግንባታውን ከሚከናወነው በሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተጠይቆ የነበረውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ኪሳራ፣ መንግሥት ባደረገው ጥረት ወደ 450 ሚሊዮን ዩሮ ዝቅ እንዲል መደረጉን ገልጸዋል፡፡