የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባካሄደው ግምገማ ቀደም ሲል የነበረውን ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ መበተኑንና በምትኩ አዲስ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ማዋቀሩን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በስሩ ከሚያዋቅራቸው ዲፓርትመንቶች መካከል በአብዛኛው በሙያተኞች እንደሚመራ የሚታመነው ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ፣ ለመበተኑ ዋነኛው ምክንያት ተብሎ በግምገማው የቀረበው ሪፖርት፣ ከዳኝነትና ከጨዋታ ታዛቢ ዳኝነት ምደባ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የአሠራር ክፍተት እንዳለበት በመታመኑ ነው፡፡
እንደ ፌዴሬሽኑ መግለጫ ከሆነ፣ ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው ግምገማ በፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኢብራሂም መሐመድ ከሚመራው ከነባሩ የዳኞች ኮሚቴ አባላት መካከል አቶ ኃይለ መላክ ነጋሽ ብቻ በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ሲደረግ፣ አቶ መኮንን አስረስ፣ ሻለቃ በልሁ ኃይለ ማርያም፣ አቶ ፈቃዱ ጥላሁንና አቶ ቸርነት አሰፋ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል፡፡
በምትካቸው የካፍ ኮሚሽነር ልዑል ሰገድ በጋሻው፣ ኢንስትራክተር ግዛቴ ዓለሙ፣ ኮሚሽነር አዲሱ ነጋሽና ኮሚሽነር ስንታየሁ እጅጉ አዲሶቹ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ አባላት ሆነው ተመድበዋል፡፡
ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፌዴሬሽን ሙያተኞች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ነባሩ የዳኞች ኮሚቴ እንዲበተን የተደረገው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በየደረጃው በሚያከናውናቸው ውድድሮች በተለይም ከዳኝነት ጋር ተያይዞ ስህተቶችን በሚሠሩ ዳኞችና ረዳቶቻቸው ትክክለኛ ውሳኔ አለመሰጠቱ ነው፡፡
የዳኝነትና የጨዋታ ታዛቢ ዳኝነት ምደባ የሚደረገው አቅምና ችሎታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ባለመሆኑና ለዚህም ተደጋጋሚ ጥቆማዎችና ቅሬታዎች መቅረባቸው፣ ከሙያው ሰብዕና ውጪ ለግል ጥቅማ ጥቅም መቆምም ይጠቀሳሉ፡፡
ውድድሮችን እኩል አለማየት፣ በውድድሮች ላይ የሚፈጸሙ ግድፈቶች ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች የገለልተኝነት ችግር ያለባቸው መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡