የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ እሑድ መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ እንደሚያከናውን ገለጸ፡፡
የኦሊምፒክ ኮሚቴው መተዳደሪያ ደንብ በየአራት ዓመት አንድ ጊዜ ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ምርጫ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይሁንና ከአንድ ዓመት በፊት የቻይና ግዛት በሆነችው ውሃን ከተማ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን ጨምሮ በርካታ ፕሮግራሞች እንዲሸጋሸጉ ተደርገው ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ ፕሮግራሞች መካከል ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ይጠቀሳል፡፡
የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው፣ ለቀጣዩ አራት ዓመታት ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ለመምራት ለፕሬዚዳንትነትና ለሥራ አስፈጻሚነት ዕጩ ሆነው የቀረቡ 21 ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችንና አሶሴሽኖችን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ኦሊምፒክ ኮሚቴው የካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በቢሾፍቱ አዱላላ ሆቴል ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ፣ የምርጫ ማስፈጸሚያ መመርያና ሦስት ኮሚቴ ያለው የምርጫ አስፈጻሚ አባላትን መሰየሙ ይታወሳል፡፡