Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የጅማን ቡና ከሐረር ቡና ጋር ደባልቆ ማቅረብ የቡና ጣዕሙን ያሳጣዋል›› ማስተር ሔኖክ መገርሳ፣ የላቭ ቱ ኔሽንና ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ኢትዮጵያ መሥራችና ሰብሳቢ

ማስተር ሔኖክ መገርሳ ‹‹ላቭ ቱ ኔሽን›› (ፍቅር ለሕዝብ) የተባለውን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ እንዲሁም ‹‹ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ኢትዮጵያ›› መሥራችና ሰብሳቢ ናቸው፡፡ የድርጅቱንና የአሶሲዬሽኑን እንቅስቃሴ በተመለከተ ከሪፖርተር ጋር ያካሄዱትን ቃለ ምልልስና ከሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ለቀረቡላቸው ልዩ ልዩ ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ ታደሰ ገብረማርያም አቀነባብሮ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

ጥያቄ፡- ‹ላቭ ቱ ኔሽን›› የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንዴትና ለምን ተቋቋመ?

ማስተር ሔኖክ፡- ‹ላቭ ቱ ኔሽን›› (ፍቅር ለሕዝብ) በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሰማራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን፣ የተቋቋመውም ነሐሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡ በሥሩም ወደ 10 የሚጠጉ ፕሮጀክቶችን አቅፏል፡፡ ከፕሮጀክቶቹም አንዱና ዋነኛው ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ኢትዮጵያን መመሥረት ነው፡፡ በአሜሪካ በአውሮፓ የነበረውን የቡና ብቃትና ጥራት ደረጃ አሰጣጥ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ለማድረግ የሚያስችል ማሠልጠኛ ተቋም አዲስ አበባ ውስጥ ማቋቋም፣ እንዲሁም መካከለኛው ገቢ ላላቸው ወገኖች የሚውሉ 500,000 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በዚሁ ከተማ መገንባት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ የኤሌክትሪክ መብራትና በፀሐይ ኃይል የሚሠራ ሶላር በማስገባት ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ከተያዙት ፕሮጀክቶች መካከል የተካተቱ ናቸው፡፡   

ጥያቄ፡- ከፕሮጀክቶቹ መካከል ተግባራዊ የሆኑት የትኞቹ ናቸው?

ማስተር ሔኖክ፡- ድርጅቱ ከያዛቸው ፕሮጀክቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት ተግባራዊ የሆነው ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ኢትዮጵያ መመሥረት ሲሆን፣ የማሠልጠኛ ተቋም ሥራ መጀመር፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶችንም ለመገንባት እንዲያስችል ከአንዳንድ የውጭ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ ሥልጠናው ለጊዜው በኪራይ በተገኘ ቤት ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፣ ሠልጣኞቹም የተመለመሉት ለጊዜው ከአዲስ አበባ ብቻ ነው፡፡ ወደፊት ግን የራሳችን ሕንፃ ይኖረናል፡፡ የመቀበል አቅማችንን ደግሞ በአገር አቀፍ፣ ከዚያም ከፍ ሲል በአፍሪካ ቀንድ ደረጃ ከፍ ይላል ብለን እየሠራን ነው፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጡት ከዓለም አቀፍ ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን የሚላኩ ታዋቂ ቡና ቀማሾች ናቸው፡፡ ከተቋሙ ሠልጥነው የሚወጡት ወገኖች በየትኛውም አገር የመቀጠርና ሥራ የማግኘት ዕድል አላቸው፡፡

ጥያቄ፡- ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በቡና ጥራት ላይ ያደረገውን እንቅስቃሴ እንዴት ይገለጻል?

ማስተር ሔኖክ፡- አሶሲዬሽኑ የተመሠረተው በቅርቡ ነው፡፡ ይኼም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ የሚገኙ ወደ 23 የሚጠጉ ቡና አምራቾችና አቅራቢ ድርጅቶች የተሳተፉበትና የቡና ጥራትን ለመለየት የሚያስችል የቡና ቅምሻ አካሄዷል፡፡ ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በተከናወነው በዚሁ የቡና ቅምሻ ላይ የአምስት ድርጅቶች ቡና አገር ነክ፣ ጥራታቸውና ደኅንነታቸው የተጠበቁ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ለእነዚህም ድርጅቶች ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ኢትዮጵያ ያዘጋጃውና በዓለም የቡና ገዥዎች ማኅበር ዘንድ ተቀባይነት ያለው የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በእያንዳንዱም ምስክር ወረቀት ላይ ቡናው ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ መልኩን የሚገልጽ ጽሑፍ ታክሎበታል፡፡ ይህ ዓይነቱን የምስክር ወረቀት ካገኙትም መካከል ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል እና ጉጂ ኃይላንድ የተባሉ ድርጅቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለውድድር የቀረቡትን ቡናዎች በመቅመስ ደረጃ የሰጡት ከዓለም አቀፉ ስፔሳሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ዋና መሥሪያ ቤት የመጡ ታዋቂው ፈረንሣዊ ቡና ቀማሽ ናቸው፡፡

ጥያቄ፡- የዓለም አቀፉ ስፔሻሊቲ ኮፊ ማኅበር አወቃቀርና እንቅስቃሴን እንዲሁም እርሶም ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ኢትዮጵያን ለማቋቋም ያነሳሳዎት ምክንያት ምን እንደሆነ ቢያብራሩልን?

ማስተር ሔኖክ፡- የዓለም አቀፉ አሶሲዬሽን ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘው በአሜሪካ ሲሆን በ170 አገሮች የሚገኙ ቡና ገዥዎችን በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡ ይህም አሶሲዬሽን ለዓለም ቡና ገዥዎች የገበያ ትስስር የፈጠረ የዓለም የቡና ገዥዎች ማኅበር ነው፡፡ ትኩረቱም የቡናን ጣዕምና ደረጃ መጠበቅ ነው፡፡ በተጠቀሱት አገሮችም ውስጥ እንደ ዓለም አቀፉ ተቋም ሥልጣን ያላቸው ተመሳሳይ አሶሲዬሽኖች ተቋቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይህ ዓይነቱ አሶሲዬሽን እስካሁን አልነበራትም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አቋቁማ ወደ ሥራ ለመግባት ችላለች፡፡ በተረፈ ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ኢትዮጵያን ለመመሥረት ያነሳሳኝ ምክንያቶችን ከመግለጼ በፊት የኢትዮጵያን ቡናን በተመለከተ የዓለም ቡና ገዥዎች ማኅበር ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች ለማብራራት እወዳለሁ፡፡ ቡናችንን ወደ ውጭ አገር ገበያ መላክ ላይ ችግር እንዳለበት መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ጣዕሙና ደኅንነቱ የተጠበቀ ባለመሆኑ የተነሳ ነው፡፡ ለዚህም ችግር መንስዔው አንደኛ ደረጃ የሆነው ቡና ከሁለተኛና ከሦስተኛ ደረጃ ቡና ጋር ደባልቆ ማቅረብ፣ ወይም የሐረርን ቡና ከጅማ ቡና ጋር አዋህዶ መላክና የመሳሰሉ ችግሮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ቡናን በተጠቀሰው መልክ መደባለቅ ደግሞ ጣዕሙን እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለው ይኼው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ቡና ገዥዎች ገንዘባቸውን ይከስራሉ፡፡ ቡናውም ወደ መጣበት እንዲመለስ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያም ትወቀሳለች፡፡ በተረፈ ወደ ዋናው ጥያቄ ልመለስና አሶሲዬሽኑን ማቋቋም ያነሳሳኝ አሜሪካ ሎስ አንጀለስ ውስጥ የገጠመኝ አንድ ክስተት ነው፡፡   

ጥያቄ፡- ክስተቱን ምንድነው?

ማስተር ሔኖክ፡- በሎስ አንጀለስ በሚገኝ የኮያ ሠፈር ቡና ለመጠጣት አቀናሁ፡፡ በዚህም የብራዚል፣ የኮሎምቢያ፣ የጃፓን፣ የኮሪያ፣ ወዘተ ቡና በብዛት ይጠጣል፡፡ የቡና መገኛ ከሆነችው ኢትዮጵያ ግን የቀረበ ቡና የለም፡፡ በጠጪዎቹም ዘንድ አትታወቅም፡፡ በተለይ ደግሞ ጃፓንና ኮሪያ መኪና እንጂ ቡና አያመርቱም፡፡ ይህም ሆኖ ግን በዓለም በጣም የታወቁ ናቸው፡፡ ይህ ቁጭት በውስጤ ገባ፡፡ አንድ ቀን ኢትዮጵያ በአገሯ ብቻ ሳይሆን በዓለም የቡና ቀማሽ በመሆን ዕውቅና የምትሰጥበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን አጥብቆ መሥራትና መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን ተገነዘብኩ፡፡ ኢትዮጵያ ይህን አሶሲዬሽን ከተቋቋመና በዓለም የቡና ገበያ ትስስር ውስጥ ብትገባ ኢኮኖሚዋ እንደሚንሠራራ፣ ቡና አምራቾችና ላኪዎች ደህና ገንዘብ እንደሚያገኙ፣ መንግሥትም ከቀረጥ ገቢ እንደሚጠቀም ራዕይ ታየኝ፡፡ ይህንንም ተግባር ላይ ለማዋል እንዲያመቸኝ ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ማቋቋምን ተያያዝኩት፡፡ የማቋቋሙም ሁኔታ ዕውን ሆነ፡፡ በሥሩም ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ አሥር ፕሮጀክቶች እንዲኖሩ አደረግኩ፡፡ ፕሮጀክቶቹም አቅምን ባገናዘበ መልኩ ሥራ ላይ እየዋሉ ናቸው፡፡  

ጥያቄ፡- የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በዓለም አቀፍ ደረጃ በራሱ የሚያካሂደው ውድድር አለ፡፡ ከዚህ አኳያ ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ኢትዮጵያ ከባለሥልጣኑ ጋር ያለው ቅንጅት ምን ይመስላል?

ማስተር ሔኖክ፡- የእኛ አሶሲዬሽን ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ባለሥልጣኑ ቡና አምራች ነው፡፡ እኛ እየሠራን ያለነው ቡና ከሚገዙ የዓለም ቡና ገዥ አሶሲዬሽኖች ጋር ነው፡፡ የዓለም ቡና አሶሲዬሽን ከኢትዮጵያ ቡና አይገዛም፡፡ ምክንያቱም ጥራት የለውም፡፡ የቡና ገዥዎች አሶሲዬሽን ቡና የሚገዛው የዓለም አቀፉ ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ዓርማ ከተቀበሉና አባል ከሆነ አገር ብቻ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ነው ቡና እየተቀመሰ ለዓለም ገበያ የሚቀርበው፡፡ በእርግጥ በስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ያልተቀመሰ ቡና የሚገዙ አገሮች ይኖራሉ፡፡ እነርሱም ቻይናና ህንድ የመሳሰሉ ናቸው፡፡ በተረፈ ከዓለም አቀፉ ታዋቂ ቡና ቀማሽ የተረጋገጠ ሠርተፊኬት የሌለው ቡና አቅራቢ በ170 አገሮች ውስጥ ቡናን ለሽያጭ የሚያቀርብበት መንገድ ሁሉ የተዘጋ ነው፡፡ የብራዚል ቡና ከኢትዮጵያ በልጦ በዓለም ታዋቂ ሊሆን የቻለው ‹‹ስፔሻሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን ብራዚል›› በማቋቋሙና በዚህም አሶሲዬሸን የተቀመሰ ቡና ለዓለም የቡና ገዥዎች በማቅረቡ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ባለሥልጣኑ ስብሰባችን ላይ እንዲገኝ በተደጋጋሚ ጊዜ በደብዳቤ ጠይቀን መልሱ የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቶብናል፡፡ ባለሥልጣኑ በአገር ውስጥ የሚካሄደውን የቡና ግዥ አስመልክቶ ከአርሶ አደሮቹ የቀረበውን ቡና ይቀምስና ለዚህም ዕውቅና ሊሰጥ ይችላል፡፡ እኛ ግን ለ170 አገሮች ቡና ገዥዎች ቡናችን እንደ በፊቱ ጥራቱ የወደቀ ሳይሆን ጥራት ያለው ቡና እያቀረብንና ለዚህም ማስረጃ እየሰጠን ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት...

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባ-ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...