Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጩኸት በረከተ!

እነሆ መንገድ። ከሳሪስ አቦ ወደ መገናኛ ልንጓዝ ነው። ዙሪያ ገባውን በጨረፍታ ስንቃኘው በአቧራ ሸማ የወየበው ዓይናችን እርስ በርሱ ይጋጫል። ‹‹አቤት ይኼ አቧራ…›› ይላል መንገድ ላይ ተኝቶ በሁለት ጉንጩ ጫት የሚያላምጥ የአዕምሮ ሕመምተኛ። ሠልፉ ረጅም ነው። እንደተሰመረ አልተሰረዘም። የሚሰረዝበትን ጊዜም የሚያውቅ የለም። ሁሉም የሚያውቀው ሠልፉ ከጠዋት አንስቶ እስከ ማታ ድረስ ረዝሞ መዋሉን ነው። ‹‹አቤት አቧራ…›› ደገመው ያ መሀል መንገድ ላይ እንደ ባለጠጋ በጎኑ ተጋድሞ ወጪ ወራጁን ሲታዘብ የሚውል ታማሚ። ‹‹ታዲያ ማን እሱ ላይ ተኛ አለህ፣ አትነሳም?›› ይላል ባለተራው ወያላ። ‹‹ማን ያነሳኛል? ልነሳስ ብልስ ማን ያግዘኛል? እናንተ ሰው በሰው ላይ እየጫናችሁ መንገድ ማጣበብ የለመዳችሁ ብላችሁ፣ ብላችሁ በአቧራዬ መጣችሁ? እኮ በመንገዴ?›› ሲለው ወያላው ትቶት ተሳፋሪ በስህተት ያስተረፋት ክፍት ቦታ እንዳታመልጠው ያብጠረጥር ጀመር። የአዕምሮ ታማሚው ቀጠለ። ድሮስ ሊያቆም ነው እንዴ!

‹‹እኔ እኮ የሚገርመኝ ላያስጨርሱኝ የሚያናግሩኝ ነገር ነው። በገዛ አገሬ በገዛ ገላዬ ቆዳዬን አፈር ባስመሰልኩ፣ ምንድነው ይኼ ሁሉ ጭንቅ? በለው አቧራ… የት አገር እንድረስ አለች ሟቿ ሚስቴ?›› ብሎ ከመንገድ የለቀመውን የተኮሰተረ ሲጋራ ለኮሰ። ሠልፈኛው በመሰልቸት ይሁን በግልምጫ ወይም በሐዘኔታ ተራ በተራ ይገላምጠዋል። ‹‹ዕውን ከእኔ ገላና ከእናንተ የማን ነው ቆሻሻው? ዕውን ከእናንተ ዓይንና ጆሮ የማነው ንቁው? ይኼን ሁሉ አቧራ ለመጠጣት ሥራ አለኝ ብላችሁ፣ ትዳር አለኝ ብላችሁ፣ ተስፋ አለኝ ብላችሁ ከቤት ትወጡ? ወይኔ እናንተን ባደረገኝ?›› ሲል አንዲት ገራገር ወጣት ሳቀች። ‹‹ምን ያስቅሻል?›› ብሎ ተቆጣ። ‹‹አቧራው…›› አለችው በፈገግታ። እንባውን እያዘራ በሳቅ ተንፈራፍሮ፣ ‹‹ለምን አታራግፊውም ታዲያ? እናንተስ ለምን አትተባበሩም? እዚህ መንገድ ላይ ዘመኔን በሙሉ ያየሁት አቧራ ማቡነንና አቧራ ማጨስ እንጂ፣ ማራገፍ የማይችል ብቻ ነው…›› ብሎ ሳቁን ከሲጋራው ጭስ ጋር ሊያዋህድ በረጅሙ አንቦለቦለው። ምን ያድርገው ታዲያ!

ጉዟችን ተጀምሯል። ታክሲያችን እንደ ጤፍ በገፍ ዘግና በየመቀመጫዋና በመሬቷ ላይ ጭምር ዘርታን ትፈተለካለች። ‹‹ያ ሰውዬ አቧራ… አቧራ… እያለ አውርቶ አሁን አፌን ሳይቀር አፈር… አፈር… አለው…›› ትላለች ከሾፌሩ ኋላ የተሰየመች ወይዘሮ። ‹‹ታዲያ አንቺን ማን አጣጥሚው አለሽ? ዝም ብለሽ አትውጭውም? ወይም ጥርስሽን በወይራ ፋቂው…›› አላት ከጎኗ የተሰየመ ጎልማሳ። ‹‹ጣዕምማ ድሮ ቀረ፣ አቤት የድሮ አፈር። አቤት የድሮ አቧራ። ለዛው፣ አኳኋኑ፣ አቦናነኑ፣ አረጋገፉ…›› ስትል ተሳፋሪዎች ፈገግ አሉ። ‹‹እሺ?›› እያለ ይለኩሳታል ጎልማሳው። ‹‹የዛሬን አያድርገውና የእኛ ዘመን አቧራ እንዲሁ ከየትም ተነስቶ የትም አይቦንም ነበር። ረጋ ብሎ መክሮና አማክሮ እንደ ሠፈሩ ሰው ፀባይ፣ እንደ አየር ንብረቱ ይዞት ነው የሚቦነው። ደግሞ ከዘንድሮ ጋር ሊወዳደር? የዘንድሮው እኮ ስሜት ብቻ ነው፣ ዕውቀት የለውም…›› እያለች ስትቀጥል መሀል መቀመጫ አጠገቤ የተሰየመችው ያቺ ገራገር፣ ‹‹ኧረ ቆይ ስለምንድነው የሚወራው?›› ብላ አቋረጠቻት። ‹‹ከገባሽ ይግባሽ፣ ብቻ እኛ እንደ ፈለግነው አቧራችንን ማነፃፀር መብት አለን። ምነው ላሊበላን በሰውኛ ዘይቤ አናግረውት የለም እንዴ? ዓባይን፣ አዋሽን፣ ተከዜን… የአገራችን ጎበዛዝት ባለቅኔዎች አላጫወቱዋቸውም? ምናለበት ታዲያ እኛ ዛሬ አቧራዎቻችን ብንዘክር?›› ስትል ገሚሱ ይስቃል ገሚሱ በግርምት አፉን ይዞ ያዳምጣታል። ‹‹እውነቷን እኮ ነው፣ የአንጀቴን ግድግዳ ገልብጣችሁ ብታዩት የኮቴዎቼ ማኅተም ድርሳን ይነበባችኋል ያለ ደራሲ አለ፤›› ብሎ ደግሞ ጎልማሳው አባባሰው። ወይ አፈርና ሰው!

ሦስተኛው ረድፍ ላይ ደግሞ አንዲት ወጣት በሞባይል ስልክ ታወራለች። ‹‹እስኪ የሚፈርምልኝ ሰው ፈልጊ… የማልነካውን አገር እንዲህ ነው እንዲህ ነው ከምትይኝ ምናለበት ባል ብትፈልጊልኝ?›› ስትል ሁሉም ካቀረቀረበትና በሐሳብ ከተሰደደበት መለስ ብሎ ጆሮውን ጣለባት። ‹‹ምን ሰለቸሽ በይኝ? ያንቺ ወሬ። እንደዚያ አብረን እንዳልበላንና እንዳልጠጣን፣ ስንቱን ችግር አብረን እንዳላሳለፍን፣ ዛሬ ሲደላሽ እኔ ያለሁበትን ረስተሽ ስለራስሽ ድሎት ብቻ ስታወሪኝ ትንሽ አይደብርሽም?›› ስትል፣ ‹‹ተመልከት ኮምፔ…›› ብሎ አንዱ ከመጨረሻ ወንበር ያሽሟጥጣታል። ልጅት ከወዳጇ ጋር ሰው ሰማኝ አልሰማኝ ሳትል መጠዛጠዟን ቀጠለች። ‹‹ዋይፋይ ተገኝቶ ነው ወሬው የደራው?›› ብሎ ጋቢና የተሰየመው ይጠይቃል። ‹‹ኧረ ዋይፋይ የት ተገኝቶ፣ በቀጥታ ደውላላት ነው እንዲህ የምትሞልጫት?›› ሾፌሩ ነገር ያካርራል። ‹‹ዘንድሮ ግጣም ያጣው በዝቷል። አንዳንዱ ይኼው እንደምትሰማው በጂኦግራፊ ያመካኛል። አንዳንዱ በፖለቲካ ይማረራል። ወዲህ ቢሉት ወዲያ ቢወስዱት ዞሮ ዞሮ ግጣም የማጣት ችግር ነው። ባል ጠፋ፣ ሚስት ጠፋች፣ መካሪ ጠፋ፣ አይዞህ ባይ ጠፋ፣ ሽማግሌ ጠፋ፣ ይሉኝታ ጠፋ፣ በየፊናችን እንዳሻን እየሆንን መረን ተለቀቅን…›› የምትለው ወይዘሮዋ ናት። ይጨንቃል!

‹‹ወይ የዘንድሮ ሰው በጆከር አበደ እኮ…›› ከመጨረሻ ወንበር አንዱ ጀመረ። ‹‹የምን ጆከር?›› ጠየቀችው ከጎኑ። ‹‹ጆከር ነዋ፣ ጆከር አታርፊም? ወይስ በሁለት ማንኪያ የሚጎርስ ሲባል ሰምተሽ አታውቂም?›› ሲላት ዓይኑን አፍጥጦ፣ ‹‹ታዲያ እንደ እሱ አትልም? ለምን በገዛ ቋንቋችን ባይተዋር ታደርገናለህ?›› ብላ ተቆናጠረችበት። ይኼኔ ጎልማሳው ቀበል አድርጎ ‹‹ወይ ጆከር ተጫውተንም በሆነልን፣ እኛ የጨዋታው ዓይነት አይደለም የቸገረን። የመሆንና ያለ መሆን ጉዳይ ነው…›› ብሎ ሳይጨርስ አስነጠሰ። ያም ያም ‘የተናገረው እውነት ቢሆን ነው ሳይጨርስ ያስነጠሰው’ ዓይነት አጎብድዶ ‘ይማርህ ይማርህ’ ሲለው ታዘብን። ያውም እኮ ኮሮና ከፍቷል በተባለበት ጊዜ፡፡ ምን ይህ ብቻ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሳይደረግ እኮ ነው ሰው አፍ ለአፍ ገጥሞ የሚተጋተገው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ታክሲያችን ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልታ ተቆጣጣሪ እንኳ የለም፡፡ መመርያ ወጣ ቢባልም አስፈጻሚ ጠፍቶ ሾፌርና ወያላ አፋቸውን ሳይሸፍኑ፣ ታክሲዋን የሰርዲን ጣሳ አስመስለው ጠቅጥቀዋታል፡፡ ወይ ዘንድሮ እንጃልን!

ጉዟችን ቀጥሏል። ተሳፋሪ ይወርዳል፣ በሌላ ተሳፋሪ ይተካል። ወያላው በወረዱት ፋንታ ታክሲዋን ሰው ለመሙላት ይጣራል፣ ሲገኝም በትርፍ ላይ ይደርባል። ‹‹ይቅርታ እዚህ ጋ ጠጋ ትሉላት?›› እያለ ፊት መቀመጫ ያሉትን ጭምር ያስቸግራል። ‹‹ደራርብብን እንጂ ‘ላለው ይጨመርለታል’ አይደል የሚባለው…›› አለው ጎልማሳው። የምትደረበዋ ልጅ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ታዲያስ! እንዲህ ታክሲ ወንበር ላይ ታጭቀን ካልተለማመድነው ኮሮናን እንዴት ልንቋቋመው እንችላለን?›› ብላ ኮስተር ትላለች። ‹‹ጨዋታ ትችያለሽ አይደል? ለእንዳንቺ ዓይነቷስ እንኳን መጠጋት ብነሳም አይቆጨኝም…›› አለ አፍላ ጎረምሳ። ‹‹አመሠግናለሁ…›› ከማለቷ ጎልማሳው ወዲያው ቀጠል አድርጎ፣ ‹‹አሉ እንጂ ወይ ጨዋታ አያውቁ፣ ወይ ጨዋታ አይወዱ፣ ራሳቸው ተሸብረው ሌላውን ማሸበር የሚወዱ… አይደለም እንዴ? አጋጥመውሽ አያውቁም?›› አላት። ምን ዓይነቱ ነው እባካችሁ!

‹‹ፍርድ እንደ ራስ ነው። የአንዳንዱ ሰው የታክሲ ውስጥ ሁኔታ ከአኗኗሩና ከመጣበት አድካሚ መንገድ ጋር ሲገናኝ ታዝቤያለሁ…›› አለችው። ‹‹እሱስ ልክ ነሽ፣ እኛም የሰውን ባህሪ ካመጣጡ ጋር አገናዝበን መቀበል አበዛን መሰለኝ፣ እንዳሻው የመጣለትን የሚዘባርቅ ያልበሰለ ነውጠኛ እናበረታታለን…›› ብሎ ጎልማሳው ነገር ሲጀምር፣ መላው የታክሲ ተሳፋሪዎች እርስ በርስ ተያየን። ‹‹በቀኝ አሳይቶ በግራ ሸጠው ማለትስ አሁን ነው…›› የምትለኝ አጠገቤ የተቀመጠችው ናት። ከጀርባ የተሰየሙ አዛውንት ተሳፋሪዎች አንዱ በበኩላቸው፣ ‹‹ልፉ ብሎን እንጂ ከዘንድሮ ሰው ጋር ለመግባባት እየተቸገርን ነው…›› ሲሉ ይሰማሉ። ጉድ እኮ ነው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ወይ የዘንድሮ ሰው እንዲህ መላ ቅጡ ይጥፋው?›› ይላል አንዱ። ‹‹እንዴት መላ አይጠፋው ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻውን ሰው አያስኮን። መንገዱ መሰናክሉ ብዙ ነው…›› ወይዘሮዋ ናት ይህን የምትለው። ‹‹ምን ማለት ነው ደግሞ? ሰው ሆነው ከተፈጠሩ ወዲያ ሰው ለመሆን መጣር?›› ይላታል ከወጣቶቹ አንዱ። ‹‹በዚህ በዚህ እኮ ነው እኛና እናንተ የተሸዋወድነው። የዘንድሮ ልጆች ስለመሆንና ስላለመሆን ምንም የምታውቁት ነገር የለም። ዝም ብላችሁ መስሎ በማደር የተካናችሁ ብቻ ናችሁ። ዳዊት ሰለሞንን ምን አለው? እንግዲህ ሊሞት እያጣጣረ ሰለሞን በእጁ ደገፍ አድርጎት (ያየች አትመስልም? የሚል አለ) ‘ልጄ ሆይ ሰው ሁን’ አለው። እንግዲህ ሰለሞን የንጉሥ ልጅ ነው። ምን ሰው ሁን የሚያስብል ነገር መጣ? ካለመሆን የሚከለክለው ምን ነገር ነበር? አያችሁ ሰው ሁሌም በተቃርኖ የሥነ ልቦና ጦርነት ይናጣል። በልጅነቱ ከማመንና ካለማመን ጋር፣ በጉርምስናው ከታላቅነትና ከበታችነት ስሜት ጋር፣ እንደ እናንተ በወጣትነቱ ደግሞ ከማንነትና ከሰብዕና ቀውስ ጋር እየዋዠቀ ያልፋል። እነዚህን ተቃርኖዎች በአግባቡና በጊዜው በሰከነ መንፈስ አስታርቆ ሰብዕናውን እየገነባ የማይሄድ ሰው፣ ሰው ከመሆን ጎደለ ማለት ነው። እናም ባጭሩ ሰው መሆን ማለት በሁለት ጣምራ ግጭቶች መሀል ዘወትር እያሸነፉ በመሀል ማለፍ መቻል ማለት ነው…›› ስትል አንዱ ቅልጥ አድርጎ አጨበጨበላት። ወያላው ተናዶ፣ ‹‹አቦ ሁከትና ግርግራችሁን እዚያው የለመዳችሁበት…›› ብሎ ገላመጠንና ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው። ‹‹አሁን በዚህ መንገድ ከወጪ ወራጁ ዕውን ስንቱ ሰው ይሆን ሰው? ኧረ ሰው መሆን ከበደ…›› እያለ አንዱ በለሆሳስ ሲያወራ ሌላው፣ ‹‹ምናለበት ዝም ብትል? ከቻልክ ፀጥ በል፣ ካልቻልክ ምላስህን ዋጠው…›› እያለ ሲለፈልፍ፣ ‹‹አንተን ምን አገባህ በገዛ አፌ ገና እጮህበታለሁ… በአገሩ ሁሉ ጩኸት አይደለም እንዴ የበረከተው…›› ሲለው እኛም ተጋብቶብን ነው መሰል ተባብረን እየጮህን ወደ ጉዳያችን ተፈተለክን፡፡ መልካም ጉዞ!         

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት