Friday, September 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግርን የመቅረፍ ተስፋ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በአሁኑ ወቅት በገበያ ውስጥ የምግብ ዘይት እጥረት አለ፡፡ በገበያ ላይ ከተገኘም መሸጥ ከሚገባው ዋጋ በላይ እየተሸጠ ነው፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በሸማቾች ማኅበራት በኩል 20 ሌትር የፓልም ዘይት በ770 ብር ለሸማቾች ሲሸጥ የነበረ ቢሆንም፣ ይኼው ዘይት በነጋዴው እጅ ገብቶ መልሶ እስከ 1,600 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

  በሸማቾች ማኅበራት በኩል የተከፋፈለው ይህ ዘይት በአመዛኙ ተጠቃሚዎች ለራሳቸው ፍጆታ ከመጠቀም ይልቅ እዚያው አየር በአየር እየተሸጠ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ለራስ ፍጆታ እንዲጠቀሙበት ከሸማቾች ማኅበራት የወጣው ዘይት በግልጽ ለነጋዴዎች እየተሸጠ ሲሆን፣ ነጋዴዎቹም በዚሁ መልክ ከየሸማች ማኅበራት ደጃፍ የሚገዙትን ዘይት የራሳቸውን ትርፍ አክለው ከፍተኛ የትርፍ ህዳግ ይዘው እየሸጡ መሆኑ የምግብ ዘይት ገበያን የበለጠ እየበረዘው ነው፡፡

  ከዚሁ የዘይት ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከተጠቃሚዎች ያገኘነው መረጃ 20 ሌትሩን የፓልም ዘይት በ770 ብር ከሸማቾች ማኅበር የገዙ ጥቂት የማይባሉ ሸማቾች ለነጋዴዎች እስከ 1,100 ብር ድረስ እየሸጡ ነው፡፡ ከሸማቾች በዚህን ያህል ዋጋ የተሰበሰበ ዘይት ደግሞ ለሆቴልና መሰል አገልግሎት ለሚሰጡ ድርጀቶች እስከ 1,600 ብር እየተሸጠ ነው ተብሏል፡፡

  በአሁኑ ወቅት ያለው የዘይት ገበያ ችግር የሚታይበት ሲሆን፣ ከፓልም ዘይት ውጪ ያሉ የምግብ ዘይቶች በመደብሮች ሼልፍ ላይ እምብዛም አይታዩም፡፡ በርካታ ሱፐር ማርኬቶችም ሼልፋቸው ላይ የሱፍ፣ የበቆሎና የአኩሪ አተር ዘይት እንደቀድሞው ደርድረው አይታይም፡፡ ምርቱ አለባቸው የተባሉ መደብሮች ውስጥም ቢሆን አምስት ሌትር ዘይት እስከ 550 ብር እየተሸጠ መሆኑ ታውቋል፡፡

  በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ያሉ የዘይት ማምረቻዎች በእጃቸው ያለውን በሚሊዮን ሌትር የሚቆጠር ዘይት ይዘው ምርቱ እንዲነሳላቸው እየተጠባበቁ ናቸው፡፡

  መነሳት በሚገባበት ወቅት አለመነሳቱ በፋብሪካዎቹም ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ድሬዳዋ በሚገኘው የሸሙ ዘይት ማምረቻ ተገኝተው ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ምርቱን ለማንሳት መንግሥት አዲስ አሠራር እንደሚከተል አስታውቀዋል፡፡  

  ከሸሙ የዘይት ማምረቻ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አሁን በመጋዘናቸው የተመረተው ፈሳሽ የሸሙ ዘይት መጠን ከሦስት ሚሊዮን ሌትር በላይ ነው፡፡ መንግሥት ባስቀመጠው የዋጋ ተመን መሠረትም ምርቱን ያነሳሉ የተባሉ አከፋፋዮች እየተጠበቁ መሆኑን ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ሰሞኑን እንዳመለከቱት፣ የምግብ ዘይት ምርቱ ቀደም ብሎ ከነበረው አሠራር ውጪ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እንዲነሳ የሚደረግ መሆኑን የሚጠቁም ሲሆን፣ የዘይት አምራቾች በራሳቸው መንገድ ምርቱን እንዲያከፋፍሉ የሚደረግ መሆኑን ነው፡፡

  በማኅበራት በኩል ብቻ ይቀርብ የነበረውን አሠራር በመቀየር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከሁለቱም ፋብሪካዎች ጋር ትስስር እንዲያደርጉ ተደርጎ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የመሥሪያ ካፒታል ችግር ስላለባቸው በወቅቱ ክፍያውን ከፍለው ምርቱን ማንሳት ያለመቻላቸውን አስታውሰዋል፡፡ ከፋብሪካዎቹም ይህ ጥያቄ እየተነሳ ስለሆነ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እነሱ ፕላን አድርገው በሚያቀርቧቸው አከፋፋዮች ሥርጭቱ እንዲፈጸም እንደሚያደርግም አመልክተዋል፡፡   

  ከማከፋፈል ሥራ ባሻገር መንግሥት የምግብ ዘይት እጥረትንና የዋጋ ጭማሪን ለመቀነስ ለሸሙና ፌቤላ ዘይት ፋብሪካዎች 44 ሚሊዮን ዶላር የሚያቀርብ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡ የአገር ውስጥ አምራቾችን ለመደገፍና ምርታቸውን ለመጨመርም ለፋብሪካዎቹ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በልዩ ሁኔታ ማመቻቸቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስተሩ አቶ መላኩ አለበል አስታውቀዋል፡፡ በዚህ በተፈቀደ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ዕቃውን እያስመጡና እያቀነባበሩ ለገበያ እንዲያቀርቡ የሚደረግ ይሆናል፡፡

  እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ከእነዚህ የዘይት አምራቾች በተጨማሪ ከውጭ ማንኛውንም ዓይነት ዘይት የሚያስገቡ አስመጪዎች በአምስት በመቶ ቀረጥ እያስገቡ ሲሆን፣ ይህንን የቀረጥ መጠንም ከዚህም በታች ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  ቀደም ብሎ በነበረው አሠራር ከውጭ የሚገባው ዘይት 58 በመቶ ታክስ ይጣልበት የነበረ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ምርቱን በተመጣጠነ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ቀረጡን ወደ አምስት በመቶ ዝቅ በማድረግ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ አሁንም ቀረጡን በመቀነስ ከውጭ በተመጣጣኝ ዋጋ ዘይት እንዲገባ ይደረጋል ተብሏል፡፡

  የአገሪቱን የምግብ ዘይት ፍላጎት ለማሟላትና ገበያን ለማረጋጋት ይችላሉ የተባሉትና በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ የተፈቀደላቸው ሁለቱ ፋብሪካዎች፣ በጥቅል በቀን ከ2,400 ቶን በላይ የሚያመርቱ ናቸው፡፡

  በቡሬ የሚገኘው ፌቤላ ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ 1,500 ቶን በቀን የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ ድሬዳዋ የሚገኘው ሸሙ ዘይት ፋብሪካ ደግሞ 950 ቶን የማምረት አቅም አለው፡፡ እነዚህ ሁለት ማምረቻዎች በቀን ከ2.4 ሚሊዮን ሌትር በላይ ማምረት የሚችሉ ናቸው፡፡ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ያስፈልጋል ተብሎ ከሚታሰበው የምግብ ዘይት ውስጥ 32 በመቶ የሚሆነውን ሸሙ ለመሸፈን አቅም ያለው መሆኑን ሲገልጽ፣ ፌቤላ ደግሞ 60 በመቶውን ይሸፍናል ተብሎ  የሚጠበቅ ነው፡፡  

  አሁን ለሚታየው የዘይት እጥረትና የዋጋ ንረት የማከፋፈል ሥራው ያሉበት  ችግሮች አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን፣ ይህ እንዲስተካከል የዘይት ማምረቻዎቹ በሚመርጧቸው አከፋፋዮች እንዲያሠራጩ መደረጉ ምናልባት ውጤት ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ተገምቷል፡፡  

  የዘይት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ መንግሥት እንደ አማራጭ ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል ለሸሙና ለፌቤላ የዘይት ማምረቻዎች በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ ማድረግ ሲሆን፣ የሚያመርቱትም የፓልም ዘይት ነው፡፡

  ከጥቂት ወራት በፊት የወጣ መረጃ የፓልም ዘይት የጤና እክል ያስከትላል ብሏል፡፡ እነዚህ ምርቶች ችግር አይኖራቸውም ወይ? በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የሸሙ ዘይት የሥራ ኃላፊዎች፣ በፋብሪካቸው የሚመረተው የዘይት ዓይነት ፈሳሽ የፓልም ዘይት ሲሆን፣ ምርቱም በተገቢው መንገድ የተፈተሸ በጥራቱም ማረጋገጫ ያገኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  በዓለም ላይ ለምግብ ዘይትነት ጥቅም ላይ ከሚለው አብዛኛው እጅ የፓልም ዘይት መሆኑን የተናገሩት የሸሙ ሥራ ኃላፊዎች፣ እነሱ የሚያመርቱት ዘይት ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን በመጥቀስ ለጤና ተስማሚ በሆነ ደረጃ የሚመረት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡  

  ይህ በእንዲህ እንዳለ ሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚያመርተውን የምግብ ዘይት ለመጨመር አለብኝ ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብበት የነበረው ለማስፋፊያ የሚሆን የግንባታ ቦታ የተፈቀደለት መሆኑን ገልጿል፡፡

  የማስፋፊያ የግንባታ ቦታ ጥያቄውን በካቢኔ ደረጃ የተመለከተው የድሬዳዋ አስተዳደር፣ ሸሙ ስድስት የሚሆኑ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርትበት ቦታ እጅግ የተጣበበ መሆኑን በመስክ ጉብኝት በማረጋገጥ፣ ለማስፋፊያ የሚሆነውን ተጨማሪ ቦታ ተፈቅዶለታል፡፡  

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች