- የውጭ አጋሮቻችን ያለብንን ዕዳ ለመክፈል መንግሥት ያሳየውን ቁርጠኝነት ያደንቃሉ፡፡ ነገር ግን ተግባር መቅደም አለበት እያሉ ነው።
- መከፈሉ ላይቀር ለምንድን ነው እንደዚህ የተጨነቁት?
- እንደሚመስለኝ መከፈሉ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ዕዳ በመሸከማችን ተስፋ ቆርጠውብናል።
- እንዴት ?
- ኢትዮጵያ ዕዳዋን ሳትከፍል ተጨማሪ ብድር ማግኘት ስለማትችል በአጭር ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያገኙት ፕሮጀክት እንደማይኖር ገምተዋል።
- የኢትዮጵያ አቅም አልገባቸውም ማለት ነው?
- እንዴት?
- ፈጽሞ ተሳስተዋል።
- ምንድን ነው የተሳሳቱት?
- የዕዳ ጫና የሚባለው ነገር አልገባቸውም።
- እንዴት?
- ኢትዮጵያ የዕዳ ጫና አለባት የሚባለው እኮ ጫና በዝቶባት አይደለም።
- ታዲያ ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
- የዕዳ ጫናው በዝቷል የሚሉት ከጂዲፒያችን ጋር አነፃፅረው እንጂ እኛ ከበደን አላልንም።
- ታዲያ ከምን ጋር ሊነጻጸር ይችላል?
- መክፈላችንን ለማረጋገጥ ጂዲፒ መተማመኛ ይሆናል ብለህ ነው? ለስሙ አማካሪ ተብለህ ደመወዝ ትበላለህ።
- ከጂዲፒያችን ውጪ አልመጣልኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ወንድሜ ዋናው መተማመን ነው።
- መተማመን ሲሉ?
- እንከፍላቸዋለና … መጀመሪያ ይመኑን። ምን ሆነህ ነው ዛሬ አንተ? ኢትዮጵያ እኮ እምቅ ሀብት ያላት ሀገር ናት?
- እሱስ እውነት ነው … ይከፈላቸዋል።
- አዎ። እንኳን የእነሱን ዕዳ የማይቻለውን ማድረግ መጀመራችንን አልሰማህም እና ነው።
- ምን ማድረግ ጀመርን?
- ደመና ማዝነብ፡፡
- እንዴት?
- አልሰማህም አዲሱን ፕሮጀክት?
- አልሰማሁም ክቡር ሚኒስትር።
- በኢትዮጵያ በየትም ቦታ የሚገኝ ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ፓይለት ፕሮጀክት ሰሞኑን ተጀምሯል።
- እንዴት ያለ ቴክኖሎጂ ነው የምንጠቀመው?
- ጨው ነው።
- ምን አሉኝ?
- ከደመናው በላይ ጨው መነስነስ ብቻ ነው ብዙ አይፈጅም።
- ተጓዳኝ ችግር ግን አያመጣም ከቡር ሚኒስትር?
- የምን ተጓዳኝ ችግር?
- ደም ብዛት አያመጣም?
- ምን ይላል ይኼ … ውጣልኝ!
[የክቡር ሚኒስትሩ ስልክ እየጠራ ነው። የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የሆነው አብሮ አደግና የልብ ወዳጃቸው ነው የደወለው]
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- አለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዛሬ የምትወረውረው ምን አገኘህ?
- ዛሬ እንኳን እናንተ ናችሁ ያገኛችሁት።
- እኛ ምን አገኘን?
- ዛሬ ራሳችሁን አገኛችሁ።
- እንዴት?
- ምን እንዴት አለው ክቡር ሚኒስትር ዛሬ እውነቱ እውነቱ ወጣ።
- የምን እውነት?
- የተደበቀው ነዋ።
- ምን የተደበቀ አለ?
- ድንበር ጥሰው መግባታቸው።
- አይ እሱን እንኳ ተደብቆ አይደለም።
- እሱ ብቻ አይደለም …
- ሌላ ምን ወጣ?
- ከውጭ የምንወርሰው የፖለቲካ አይዶሎጂ የለም ስትሉ አልነበረም? ይኸው ዛሬ ሳያስቡት እውነቱን አወጡት።
- ምን አሉ?
- ፕራግማቲክ ገበያ መር ኢኮኖሚ እንከተላለን አሉ።
- ይህ እኮ የራሳችን ነው።
- እንዴት?
- የራሳችን ነው ስልህ?
- ገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዴት ሆኖ የእናንተ ይሆናል? ዓለም አቀፍ ሞዴል አይለም እንዴ?
- የእኛ ገበያ መር ብቻ አይደለም፡፡
- ብቻውን አይደለም ሲሉ ?
- ከፊቱ ፕራግማቲክ አለው።
- ክቡር ሚኒስትር ድሮም ቢሆን ቀልድህን እኮ እወደዋለው።