Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልኢትዮጵያ ብሔራዊ የሥነ ግጥም ቀን የሚኖራት መቼ ነው?

  ኢትዮጵያ ብሔራዊ የሥነ ግጥም ቀን የሚኖራት መቼ ነው?

  ቀን:

  ዓለም በየዓመቱ ማርች 21 (መጋቢት 12) የዓለም የሥነ ግጥም/ የቅኔ ቀን በማለት ያከብራል፡፡ ቅኔም ሆነ ግጥም የአገላለጽ፣ የሥነ ልሳን እና የባህል ማንነት መገለጫ ናቸው፡፡ ከጥንት ጊዜያት ጀምሮ ሁሉም አህጉራት፣ ከተለያዩ ባህሎቻቸው ጋርግጥሞቻቸውም ሆነ ቅኔያቸው የታወቁ ናቸው፡፡ 

  የዓለም የግጥም ቀን እንዲከበር ሐሳቡ የተነሳው የፍልስጤም የባህል ፌስቲቫል በግንቦት 1989 ዓ.ም. በተከበረበት ጊዜ ሲሆን፣ በወቅቱ ለዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ለግጥም ልዩ ቀን ይኑረው የሚል አስተያየት የሰጡት የአገሬው ባለቅኔዎች ማህሙድ ዳርዊሽ፣ ኢዝዲን ዲን አል ማንሻራ እና ፋድዋ ቶካን መሆናቸው ይወሳል፡፡

  በተከታይም በ1990ዎቹም ጥቂት የማይባሉ የአውሮፓ ምሁራንም እንዲሁ ዩኔስኮን ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄውን ተከትሎና የግጥምን ልዕልና በማሰብ የተባበሩት መንግሥታት የባህልና ትምህርት ክንፍ ዩኔስኮ ... 1999 በፓሪስ ባካሄደው 13ኛ ስብሰባው የዓለም የሥነ ግጥም ቀን ማርች 21 ቀን (መጋቢት 12 ቀን) እንዲከበርመወሰኑ በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡

  ይህ በዓለም የሚከበረው የሥነ ግጥም ቀን የዩኔስኮን ልዩ በዓላት እንደ የዓለም ቱሪዝም ቀን የመሳሰሉትን የምታከብረው ኢትዮጵያ፣ የዳበረ የቅኔና የግጥም ባህል እንዳላት መጠን ትኩረት ለምን አይሰጠውም የሚሉ አሉ፡፡

  የዓለም ሥነ ግጥም ቀን የመከበሩን ፋይዳ ዩኔስኮ የሚገልጸው ግጥምን የማንበብ፣ የመጻፍ፣ የማሳተምና የማስተማር ተግባርን በዓለም ለማትጋት በማለት ነው፡፡ ለብሔራዊ፣ ለአካባቢያዊና ለዓለም አቀፍ የግጥም እንቅስቃሴዎች ዕውቅናና ብርታትን ለመስጠትም አጋጣሚው መሠረት ይሆናል፡፡

  ኢትዮጵያ ብሔራዊ የሥነ ግጥም ቀን የሚኖራት መቼ ነው?

   

  የግጥምን ልዕልና በማሰብ ዩኔስኮ የዓለም የሥነ ግጥም ቀን እንዲከበር የተወሰነበት በጎርጎሳዊው ቀመር ማርች 21 ቀን (መጋቢት 12 ቀን) ቀን በአውሮፓና በእስያ የመፀው እኩሌ (Spring Equinox) ተብሎ ከሚከበርበት ጋር የተገጣጠመ ነው፡፡ የግጥም ቀኑ የፋርስ ቋንቋን በሚናገረው ዓለምም ‹‹ኖውሩዝ›› ተብሎ ከሚጠራው የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ጋር መግጠሙም ተምሳሌታዊ አድርጎታል፡፡

  የዓለም የሥነ ግጥም ቀን ክብረ በዓል በየዓመቱ መጋቢት 12 ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር ለማድረግ ከትምህርትና ከባህል ጋር የተያያዙት ሚኒስቴሮች፣ ከሥነ ጽሑፍ ጋር የተዛመዱት የሙያ ማኅበራት የሚያስቡበት ቀን ይመጣ ይሆን?

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቅኔ/ የሥነ ግጥም ቀንን መሥርቶ በክረምታችን መውጫ በአበባ ወቅት (መፀው) ዋዜማ  ቀንና ሌሊቱ እኩል 12፣ 12 ሰዓት በሚሆንበት በኛው የመፀው እኩሌ መስከረም 25 እንዲከበር ምኞት አለን፡፡ መስከረም 25 የ‹‹ተቀጸል ጽጌ›› በዓል ነውና- አበባን ተቀዳጅ- በርሱ አንጻር ‹‹ተቀጸል ቅኔ››- ቅኔን ተቀዳጅ የሚለውነም ብሂል ማምጣት ይቻላል፡፡

  በዓሉ በየዓመቱ ሲከበር በቅኔዎቻቸውና በግጥሞቻቸው ላቅ በሚሉት በሕይወት ባሉም ሆነ በሌሉ ገጣሚያን መታሰቢያ ለማድረግ መድረክ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እስከዚያው ግን የመጋቢቱን የዓለም ሥነ ግጥም ቀን ከአገራዊው ትውፊት በመቅዳት በመጣጥፍ እንዘክረዋለን፡፡

  ቅኔ በኢትዮጵያ

  የቅኔ ሥነ ጥበብ በኢትዮጵያ በሚለው ሐተታቸው መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ እንደሚተረጉሙት ቅኔ ካሉት ፍቺዎች አንዱ ቀነየ ገዛ የሚለው ነው፡፡ ለዚህም ነው የውስጥና የውጭ ህዋሳትን ለህሊና አስገዝቶ በሰከነ መንፈስና በተመስጦ፣ በተወሰነ ወይም ቁርጥ ባለ ሐሳብ ላይ የሚታሰብ ስለሆነ ቅኔ የሚለውን ስያሜ ሊያገኝ ችሏል ብለው የሚገልጹት፡፡

  በሌላ አተረጓጎም ቅኔ ማለት (ቀነየ) ተቀኜ፣ ሙሾ አወጣ፣ ግጥም ገጠመ፣ አራቆ ተናገረ፣ አዜመ፣ አንጎራጎረ፣ መራ ተብሎ ከሚተረጎመው ግስ የተገኘ ጥሬ ዘር እንደሆነ የቅኔ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡

  የታሪክ ምሁሩ ሥርግው ሀብለ ሥላሴ (/) Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270 በተሰኘው መጽሐፋቸው ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ባህል ዕድገት ውስጥ ያለውን ሁለገብ አስተዋጽኦ ከትምህርት፣ ከሥነ ጽሑፍ፣ ከሙዚቃና ከመሣሪያዎች አኳያ ይዘረዝራሉ፡፡ እርሱን የቅኔ ጀማሪና የባህላዊ ትምህርት መሥራች ይሉታል፡፡ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ የተጀመረው በቅኔ መልክ ሆኖ በመቀጠልም ወደ ዝርው መሻገሩ ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ ማሳያ የያሬድን ድጓ የቅኔና የዝርው ስብጥር መሆኑ ይገለጻል፡፡

  በሥነ ጽሑፍ ረገድ ከአክሱም ዘመን ጀምሮ ልዩ ቦታ እንዳለው የሚያሳየው አንዱ ድጓው ኤፒክ ቅርፅ ያለው መሆኑ ያም በመላእክት፣ ቅዱሳንና ሰማዕታት ትግልና ገድል አጉልቶ በቅኔያዊ ቋንቋው ያሳያል፤ ይገልጻል፡፡

  እንደ ሥርግው (ዶ/ር) አገላለጽ፣ በድጓ ውስጥ የፍልስፍና መነሻዎች ወይም ኖኅያት (ኢሌመንትስ) እናገኛለን፡፡ ሰው ማወቅ፣ መርመር እንደሚገባው የሚያስገነዝብበት መልክ አለው፡፡ ትክክለኛውን የሕይወት መንገድ መከተል መጻሕፍትን መመርመር አስፈላጊነቱን ይጠቁማል፡፡ ያሬድ ለጥበብ ልዩ ቦታ ይሰጣታል፡፡

  ጥበብ በዋጋ የማትተመን የሰው ልጅ ስጦታ መሆኗን ለዚህች ዓለም ከጥበብ ጋር የማይወዳደር አንዳች ነገር አለመኖሯን ያመለክታል፡፡ ሀብትን ከመሰብሰብ ይልቅ ጥበብን መጠየቅ እንደሚሻል፤ ከወርቅ፣ ብር፣ ዕንቁ ወይም ማንኛውም የከበረ ድንጊያ ከጥበብ ጋራ ሊተካከሉ፣ ዕሪና ሊሆኑ እንደማይችሉ ያመሠጥራል፡፡

  የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ አባትና የቅኔ ጀማሪው ቅዱስ ያሬድ ሥራን በተመለከተ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ፣ በአንድ ወቅት ‹‹ነገረ አእምሮ፡ምን፣ እንዴት እንወቅ?›› በማለት በመጽሐፈ ድጓ ላይ የተመሠረተውን ጥናታቸውን አቅርበው ነበር፡፡

  መንደርደሪያው፣ ‹‹አንተስ፣ አንተ ግን፣ አንተንኳ፣ አንተንማ ለማወቅ ብትሻ የምድርን (አፈር÷ ጠፊ የኾነውን) ሐሳብ ተው፡፡ ከዋክብትን ተሻገራቸው፡፡ የሕብረታቸውንየአኳኋናቸውን ውበት ተመልከት፡፡ ከዚኽ ኹሉ እይታኽ ተነስተኽ በልቡናኽ የማይጨፈለቅ ሥሉስን ዐስብ›› የሚል ነው፡፡

  አንድ ከባድ፣ የሚቻል የማይመስል ኃላፊነት ነው ሊቁ የጣለብኽ፡፡ ‹‹ከዋክብትን ተሻገራቸው፣ ዙራቸው፣ አገላብጠኽ እያቸው›› ነው ቃል በቃል ያለኽ፡፡ ይኽ እንዴት ነው እሚቻል? ሌላም ሥራ ጥሎብኻል፡ ‹‹ከዚኽ ተነስተኽ ዐስብ››፡፡ ኹለት ታላላቅ የነገረ አእምሮ ሐሳቦች ናቸው በዚኽች የድጓ ንባብ የተነገሩ፡፡

  ሰው አንድን ነገር ከማወቅ ተነስቶ ሌላን ነገር ሊያውቅ ይችላል፡፡ የአእምሮየዕውቀት ተሸጋጋሪነትን ነው ይኽ የሚያስረዳን፡፡ ‹‹የከዋክብትን ሥን፣ ስንኝ፣ ሕብረት ተመልክተኽ ዐስብ›› ይላል፡፡ ማየት፣ መመልከት ለሐሳብ መነሻነት እንዲውል እንጂ ቆሞ እንዳይቀር ዐደራ ሰጠ፡፡

  በዚኽች ድጓ የተነገረ ሌላው ቊም ነገር ‹‹አንተ ግን ለማወቅ ብትሻ›› በምትለው ሐረግ የተሰጠው ሐሳብ ነው፡፡ የትሕትና ውጤት ነው፡፡ በጥበብ፣ በከፍተኛ ሐሳቦች የታሸ ሊቅ ደረቅ ትእዛዛትን ከማውረድ ይልቅ ማስፈቀድ፣ ማስወደድ ይቀናዋል፡፡ ውስጡ ‹‹እባክኽ ማወቅን ውደድ›› የሚል አባታዊ ምክር አለ፡፡ እርሱን ተከትሎም የአስተዋወቅን ስልት የተለመው ‹‹በልቡናኽ ዐስብ፤ ከዋከብትን አልፈኽ ዙር፤ ይኸንም ለማድረግ ተራ ዐሳብን ተው›› የሚለው ትምህርት ተሰጠን፡፡

  ሥነ ፍጥረትን ማወቅ እንዲቻል ከያሬድ በላይ የሰበከልን፣ ያሳየን ወገን የለንም፡፡ ከዝናብ ኮቴ እስከ ዕፀዋት ዝማሬ በያሬድ የተብራራ ሥነ ፍጥረት ነው፡፡

  ንጉሡን እያዩ ያላዩት ባለ ቅኔ

  በተመስጦ ቅኔ በመቁጠር ላይ ያለና በቅኔ ምሥጢር ልቡ የተሰወረ ሰው ቅኔ በሚቆጥርበት ወይም በሚያስብበት ጊዜ በአጠገቡ ወይም በፊቱ የሚደርሰውን ወይም የሚደረገውን ነገር እያየ አያይም፣ አይሰማም፣ አይሰማም፡፡ ለዚህ ማሳያ በታሪክ ከተሰነደ የተገኘው እነሆ፡-

  . . . በጎንደር ዘመነ መንግሥት ጊዜ የጎንደር ደብረ ቁስቋም አለቃ በእልፍኛቸው ውስጥ ምንጣፋቸውን አስነጥፈው፣ መጻሕፍታቸውን በፊታቸው ደርድረው፣ ለበዓለ ቁስቋም የሚቀኙትን ቅኔ ሲያስቡና ሲቆጥሩ፣ ሲያወጡና ሲያወርዱ ንጉሡ ዘው ብለው ሲገቡ ልባቸው ተመስጦ ሊያዩዋቸው ባለመቻላቸው ቀና ብለው ሳያዩዋቸው ቁጭ እንዳሉ ቀሩ፡፡ ንጉሡም ገርሟቸውና ደንቋቸው በእሳቸው አጠገብ አልፈው ከአልጋ ላይ ተቀምጠው ፍፃሜውን ለማየት ሁኔታቸውን ይመለከቱ ጀመር፡፡ በዚህ ረገድ ንጉሡ ብዙ ጊዜ ካጠፉ በኋላ፣ የደብረ ቁስቋሙ አለቃ አዕምሯቸውን ሲመለስ ንጉሡ ተቀምጠው ቢያዩ ደንግጠው በመነሳት ንጉሡን እጅ ነሱ፣ ንጉሡም፣ ‹‹ምነው? ምን ሆነህ ነው? ብለው ቢጠይቋቸው ‹‹ጃንሆይ ቁስቋምን ያህል ደብር አምነው ሹመውኛል፣ ለበዓል የተሰበሰበው ሰው አለቃው ምን ይናገር ይሆን እያለ ዓይን ዓይኔን ሲያየኝ ያልሆነ ነገር ቢሰማ ደብሩን አዋርዳለሁ፣ ጃንሆይን አሳማለሁ፣ እኔም አፍራለሁ ብዬ ቅኔ እቆጥር ነበር፤›› አሉ ይባላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img