በኢትዮጵያ ያለው የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህም በበሽታው የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና ሕይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን ቁጥር ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባወጣው መረጃ፣ መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ለኮቪድ-19 ናሙና የሰጡ 7,659 ግለሰቦች የተመረመሩ ሲሆን፣ 1,981 ሰዎች ማለትም ከተመረመሩት ከ100 ግለሰቦች 26 ያህሉ (26%) ኮቪድ-19 ቫይረስ እንዳለባቸው ተረጋግጧል፡፡ በኢንስቲትዩቱ አገላለጽ፣ ይህም የሚያሳየው ‹‹አብረውን ካሉ ሦስት ግለሰቦች አንዱ ኮቪድ-19 ቫይረስ ሊኖርበት ይችላል›› ማለት ነው፡፡
ወቅታዊው መረጃ እንደሚያሳየው፣ እስከ ተጠቀሰው ዕለት 752 ግለሰቦች በፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በአዲስ አበባ 514፣ በኦሮሚያ ክልል 102፣ በሲዳማ ክልል 76 ግለሰቦች ወደ ፅኑ ሕሙማን መርጃ ክፍል ገብተው ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉ ናቸው፡፡ በተለይ 94 ግለሰቦች በሰው ሠራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ እየተነፈሱ የሚገኙ ናቸው፡፡
ኢንስቲትዩቱ በሰጠው ጥብቅ ማሳሰቢያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን ማስክን በሚገባ ማድረግ፣ ሁልጊዜ የእጆችን ንጽሕና መጠበቅ፣ ከሰዎች ጋር ያለውን ርቀት መጠበቅና ሊፈጠሩ ከሚችሉ የሰዎች መሰባሰብ ራስን መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡
በራስና በቤተሰብ፣ በጎረቤትና በማኅበረሰብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ሞት፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቡናዊ ቀውስ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች ለመከላከል የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ በመተግበርና በማስተግበር የወረርሽኙን የሥርጭት መጠን እንዲገታም ኢንስቲትዩቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
አራቱ የ‹‹መ›› ሕጎች
- መራራቅ፡ አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣
- መታጠብ፡ እጅን በተደጋጋሚ በውኃና በሳሙና መታጠብ፣
- መቆየት፡ አስገዳጅ ካልሆነ ቤት ውስጥ መቆየት፣
- መሸፈን፡ ከቤታችን ወጥተን ስንንቀሳቀስ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) መጠቀም፡፡