Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበመማር ማስተማሩ ከወላጆች አብዝቶ የሚጠበቀው ኃላፊነት

በመማር ማስተማሩ ከወላጆች አብዝቶ የሚጠበቀው ኃላፊነት

ቀን:

ትምህርት ለዕረፍትም ሆነ በሌላ ምክንያት ተቋርጦ ሲከፈት የተማሪዎች ትምህርትን በቶሎ የመቀበል አቅም መቀነሱ ዕሙን ነው፡፡ ይህ እንደየተማሪዎቹ ትምህርትን የመቀበልና ውጤታማ የመሆን ችሎታ ቢለያይም፣ በተለይ ትምህርትን በቶሎና በቀላሉ በለማይቀበሉ ልጆች ችግሩ ይጎላል፡፡

ኮቪድ-19 በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከስድስት ወራት ላላነሰ ጊዜ በተቋረጠው የገጽ ለገጽ ትምህርት ወደ 1.6 ቢሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ተለይተው ከርመዋል፡፡ ይህ ደግሞ ትምህርት ዳግም ሲከፈት አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር በተለያዩ ጥናቶች ተመላክቷል፡፡

የተቋረጠውን ትምህርት አካክሶ ቀጣዩን ክፍል ማስቀጠል የትምህርት መቋረጡ በተማሪዎች ላይ ያሳደረውን ዘርፈ ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ ያስችላል በሚልም በዓለም አብዛኛው አገሮች ትምህርትን አስቀጥለዋል፡፡

ይህም በተለይ በደሃ አገሮችና ቤተሰቦች ሥር ለሚገኙ ተማሪዎች በጥቃት ውስጥ ለወደቁትና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ካሉበት ሆነው ለመማር ላልቻሉት ዕፎይታን ሰጥቷል፡፡

ኢትዮጵያም መደበኛ ትምህርት የሚዘጋበትን ሐምሌና ነሐሴን ሳይጨምር ለስድስት ወራት ተቋርጦ የነበረውን የገጽ ለገጽ ትምህርት ካስጀመረች አምስት ወራት ተቆጥረዋል፡፡

ትምህርቱ በሒደት ከላይ ጀምሮ ወደታች የወረደ ሲሆን፣ በፈረቃና አንድ ቀን እየዘለለ እንዲሆን እንዲሁም በአንድ ክፍል ከ21 ያልበለጡ ተማሪዎች እንዲማሩ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በሌላ አማራጮች ትምህርት እንዲደርስ ተደርጎ ከተጀመረ ከወራት በኋላ አንዳንድ ወላጆችና ትምህርት ቤቶች በተማሪዎች የትምህርት ቅበላ ላይ ክፍተት እየታየ ስለመምጣቱ እየገለጹ ነው፡፡

የግሎሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ እንደነገሩን፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትና ትምህርት ሙሉ ለሙሉ መዘጋት በኋላም መከፈት በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ጥናቶች እንደሚያሳዩ ገልጸው፣ ትምህርት ከተከፈተ ወዲህ ባሉት አምስት ወራትም በተማሪዎቻቸው የትምህርት አቀባበልና ውጤት ላይ የመቀነስ ሁኔታ መታየቱን አክለዋል፡፡

ተማሪዎቹ እቤት ከመቀመጥ ይልቅ ትምህርት ቤት እየመጡ መማራቸው፣ በቀሪዎቹ ቀናት ደግሞ ከቤታቸው ሆነው በቴሌግራምና ከክፍል የሚሰጣቸውን ትምህርት እንዲያጠኑና እንዲሠሩ የተዘረጋው አሠራር መልካም መሆኑን፣ ነገር ግን ተማሪዎች ላይ አጥጋቢ ውጤት አለመታየቱን አመልክተዋል፡፡

ሦስት ቀናት ትምህርት ቤት አሳልፈው በቀሪዎቹ ቀናት እንዲሠሩ የሚታዘዙትን ፈጽመው የሚመጡ ተማሪዎች ጥቂት መሆናቸውን፣ ከዚህ ቀደም የክፍል ሥራ ሲሰጥ መምህሩ ተከታትሎና አርሞ የሚሄድበት አሠራር በመቀየሩ የተማሪዎች የክፍል ሥራ ለመሥራት ዳተኛ መሆንና የመምህሩን መልስ መጠበቅ፣ ቤት ሲሄዱ የራስ ተነሳሽነትም ሆነ የወላጆች ክትትል በቂ ባለመሆኑ ተማሪዎች  ውጤታቸው አመርቂ እንዳይሆን ካደረጉ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡

በመደበኛው እስካሁን ሦስት እንዲሁም በየመምህራን ክፍል ውስጥ ተጨማሪ ፈተናዎች መሰጠታቸውን በመጠቆም፣ አጥጋቢ ውጤት አለመታየቱን ይህ መካከለኛ በሚባሉ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ጎበዝ ተማሪ በነበሩት ላይ መታየቱንም ተናግረዋል፡፡

‹‹ወላጅ ልጆቹን በደንብ እየተከታተለ አይመስለኝም›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ተማሪዎቹ ሦስት ቀን ከሚማሩት በተጨማሪ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ቢያግዟቸው ጎበዞች ናቸው፣ ውጤታማም ይሆናሉ ብለዋል፡፡ ከራሳቸውም ልምድ ተማሪዎች ከወላጅ ወይም ካሳዳጊ ድጋፍ ካገኙ በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ጎበዝ ሆነው መውጣት እንደሚችሉ መታዘገባቸውን ተናግረዋል፡፡

ትምህርቱን ለመጨረስ ሲባል በፍጥነት መስጠት፣ ተማሪዎች ቤታቸው ሲሆኑ ለትምህርታቸው የሚሰጡት ጊዜ አናሳ መሆንና በቴሌግራም የሚላኩላቸውን ትምህርቶች ሰበብ አድርገው በማኅበራዊ ገጾችና በሌሎች ጉዳዮች መጠመዳቸው ትምህርታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡

ይህን ችግር ግን ከወላጆቻቸው ጋር በመሆን መፍታት እንደሚቻል፣ በየጊዜውም ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲከታተሉ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ፣ ከትምህርቱ መስመር የወጡ ልጆች ወላጆችን ደግሞ እንደሚያናግሩ ጠቁመዋል፡፡

የማጂክ ካርፔት ትምህርት ቤት ባለቤትና የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ጣሰው መንግሥት፣ ተማሪዎች፣ ወላጆችና ትምህርት ቤቶች ፈቅደውና ፈልገውት ሳይሆን በኮቪድ-19 ምክንያት ተገደው የገቡበት በአሁኑ መማር ማስተማር ሒደት፣ እንደ ጊዜው ሁኔታ ተማሪዎቹን ማብቃት ላይ ሊሠራ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

ትምህርት በኮቪድ-19 ምክንያት ዘግይቶ ዳግም ሲከፈት በሳምንት ሦስት ቀናት መሆኑ፣ በአንድ ክፍል እስከ 46 ሆነው ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ከ25 በታች መደረጋቸውና ተማሪዎቹ ትምህርቱን ናፍቀው መምጣታቸው መልካም ዕድል ፈጥሯል፡፡ ለአስተማሪዎቹም የሚያስተምሩዋቸው ተማሪዎች ቁጥር ማነስ ዕፎይታ ነው፡፡ የክፍል ሥራቸውንም ሆነ የቤት ሥራቸውን ስለመሥራታቸው ለመከታተል፣ የተማሪዎችን ችግር ለመየት ዕድል ሰጥቷልም ብለዋል፡፡

‹‹አሁን ያለው አካሄድ ካለው ችግር አንፃር ብዙ ጉዳት ያደርሳል ብለን አናስብም›› ያሉት አቶ አበራ፣ የቤት ሥራ ሳይሠሩ መምጣትና ውጤት መቀነስ አልፎ አልፎ ቢያጋጥምም አብዛኛው ተማሪዎች ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሆኑ አክለዋል፡፡ ባለው ሁኔታ አቻችሎ መቀጠል ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

አየር ጤና አካባቢ በሚገኝ የመንግሥት ትምህርት ቤት እንደሚያስተምሩ የነገሩን መምህርት፣ መምህሩ እንደ ልቡ ተማሪዎችን ተጠግቶና ደብተራቸውን አገላብጦ የማየት ዕድል አለመኖሩ፣ ቤተሰብ የዕለት ኑሮን ለመግፋት ሩጫ ላይ በመሆኑ ልጆቹን አለመከታተሉ ተማሪዎች ትምህርት ቅበላ ላይ ችግር ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ከታች ክፍል ያሉት ከፊደል አጣጣልና መለየት ጀምሮ ወደ ኋላ የተመለሱበትን በግል መታዘባቸውን፣ በተማሪዎች የማንበብና የመጻፍ ክህሎት ላይ ክፍተት ማየታቸውን ይህ ግን በጊዜ ሒደት እየተስተካከለ እንደሚሄድ እምነታቸውን ነግረውናል፡፡ ነገር ግን ወላጆች ትልቁን ሚና ወስደው ልጆቻቸው ቤት በሚሆኑበት ሰዓት እንዲከታተሉና እንዲያግዟቸው መክረዋል፡፡

በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ሁለት ወላጆች እንዳሉን፣ ትምህርት ቤቱ በቴሌግራም የላከውን ትምህርት አትመው ለልጆቻቸው ቢሰጡም፣ ልጆቻቸው ትምህርት በሌለበት ቀንና ወላጆች ሥራ ሲሆኑ ቴሌቪዥን ላይ ማሳለፍ፣ ዋይፋይ ካለ ደግሞ በሌሎች ሥራዎች መጠመድ ካስተዋሏቸው ችግሮች ናቸው፡፡

የመምህሩን የቅርብ ዕርዳታ የሚፈልጉ ተማሪዎች በተለይ አሁን ባለው የትምህርት አሰጣጥ ይበልጥ እንደሚጎዱ፣ ይህንን በተመለከተ መንግሥት እንደየተማሪዎቹ የመቀበል ችሎታ ተማሪዎች ተከፋፍለው የሚማሩበትን ሥርዓት ቢነድፉ መልካም እንደሆነ መክረዋል፡፡

እንደ ወላጅ የተቻላቸውን ጥረት ቢያደርጉም እንደ መምህር እንደማይሆኑ፣ ሁሉም ወላጆች ልጆቻቸውን የማስረዳት አቅም እንደሌላቸው፣ የቤት ውስጥ አስጠኚ መቅጠር ደግሞ አሁን ላይ እንደማይሞከርና ይህ በልጆቻቸው ትምህርት ላይ ክፍተት መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎች በብዛት ቤት ማለትም ከሰባት ቀናት ሦስት ቀናት በትምህርት ቤት አራት ቀናት በቤት ያሳልፋሉ፡፡ ይህ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት የነበረውን የተማሪዎች ቤት የመቀመጥ ዕድል በሳምንት በሁለት ቀናት ጨምሮታል፡፡

ኮሮና አሁንም ሥጋት ነው፡፡ ተማሪዎች ትምህርታቸው እንዳይቋረጥ፣ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸውና ከሕይወታቸው የሚበልጥ ነገር ስለሌለ መንግሥት በዚህ መልኩ እንዲማሩ አድርጓል፡፡ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ኅትመት ዳይሬክተር ሩቂያ ሐሰን (ዶ/ር) ይህንን ከሁለት አስቸጋሪ ሁኔታዎች መለስ ያለ ችግርን መርጦ የመሄድ ሁኔታ ነው ይሉታል፡፡

ትምህርት ቤት ጨርሶ አለመሄድ መጥፎ ነው፣ ባሉት ቀናት ወይም እንደበፊቱ አምስቱን ቀናት ማስተማርም የራሱ አደጋ አለው፣ በመሆኑም መንግሥት ከተለያዩ ጥናቶች ተነስቶ በአዲስ አበባ አንድ ቀን ተምረው አንድ ቀን እንዲያርፉ  በአብዛኛው ክልሎች ደግሞ አምስቱን ቀን ሆኖ በፈረቃ እንዲማሩ አድርጓልም ብለዋል፡፡

ይህ የመማር ችሎታቸውን እንደሚቀንስ ቢታመንም፣ መምህራን በተደራራቢ ችግር ውስጥ ሆነው ኪሚያስተምሩት በተጨማሪ የመማር ችሎታቸውም ሆነ ውጤታቸው እንዳይቀንስ የወላጅ ወይም ቤት ውስጥ ተማሪዎችን ሊከታተል የሚችል ሰው ሚና ከፍተኛ በመሆኑም ወላጆች ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መልኩ ልጆቻቸውን እንዲከታተሉና ስለ ትምህርታቸው መረጃ እንዲጠይቁ ይመከራልም ብለዋል፡፡

ክፍተቱን መሙላት፣ ቤት ውስጥ በሚያሳልፉበት ጊዜ በተቻለ መጠን ጊዜያቱን በትምህርትና ትምህርታዊ በሆነ ነገር መሙላት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ ልጆች ያላቸውን ትርፍ ጊዜ በተለይ በከተማ ስማርት ፎን ላይ ያሳልፋሉ፡፡ የማይጠቅማቸውንና የሚጎዱዋቸውን ነገሮች ወደ አዕምሮአቸው ለማስገባት በርካታ ጊዜ እንዲያገኙም አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ወላጆች ከበፊቱ በተጨማሪ ልጆቻቸው ላይ በትኩት መሥራት እንዳለባቸው ያስገነዝባል ብለዋል፡፡

እንደ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቤት ሲቀመጡ ትምህርትን በፈረቃ ወይም አንድ ቀን ዘሎ አንድ ቀን ሲማሩ ሊገጥማቸው የሚችል የትምህርት ክፍተትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቅድመ ጥናት እየተሠራና እየተሰበሰበ ቢሆንም፣ ስላልተጠናቀቀ በተማሪዎች የመማር ችሎታ ላይ ስላደረሰው ተፅዕኖ አሁን ላይ ለመግለጽ ባይቻልም፣ ክፍተት ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ትምህርት በሚዘጋባቸው ጊዜያት ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚደርስና አካላዊ ጥቃት እንደሚገጥማቸው ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ትምህርት ሲዘጋ በተለይ በከተማ ያሉና ዕድሉ ያላቸው ተማሪዎች እንዲያነቡና ትምህርታዊ በሆኑ የቴሌቪዥንም ሆነ ሌሎች ቻናሎችን እንዲከታተሉ ይመከራል፡፡ ነገር ግን ይህንን በቤት ውስጥ የሚከታተል ወላጅ ወይም አሳዳጊ ሊኖር ይገባል፡፡

በደሃ አገሮች የሚኖሩ የአርሶ አደር ልጆች  ትምህርት ሲዘጋ በአብዛኛው ቤተሰብ በማገልገል የሚያሳልፉ ቢሆንም፣ ሴቶች ያለአቻና ለግዴታ ጋብቻ የሚጋለጡበት ሁኔታም አለ፡፡

ዶ/ር ሩቂያ እንደ መምህርት ራሳቸው የታዘቡትን አስመልክተው እንዳሉት፣ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ እንደገባና ተማሪዎችም ሙሉ ለሙሉ ከትምህርት ሳይርቁ በፊት በበይነ መረብ የሚሠሩት የቤት ሥራ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ትምህርት ተከፍቶ ያለፈው ያላለቀ ትምህርት በአንድ ወር እንዲጠናቀቅ መሥራት ሲጀመር ግን፣ ተማሪዎች ያለፈውን ትምህርት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ረስተውት መጥተዋል፡፡ በበይነ መረብ የተሰጣቸውን የቤት ሥራም ሆነ ጥናት ረስተውትም ነበር፡፡

አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ካሉ ተማሪዎች በዕድሜም ሆነ በማገናዘብ ደረጃ የተሻሉ ናቸው በሚባሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ይህ ከታየ ከፍተኛ ክትትልና የትምህርት ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው የታችኛው ደረጃ ተማሪዎች ላይ ደግሞ ችግሩ ይጎላል፡፡ ይህም ቤተሰብ ትልቁን ኃላፊነት ወስዶ እንዳልሠራ ያሳያል፣ ተማሪዎች ብዙ ነገር ረስተዋል፣ የመማር አቅማቸውም ይቀንሳል ብለዋል፡፡

በቤተሰብም ሲታይ ትምህርት ቤቶች ወላጆች ለልጆቻቸው ድጋፍ አድርጉ፣ ከትምህርት ቤት የሚቀሩበትን ክፍተት ወላጆችና አሳዳጊዎች በተቻለ መጠን ሙሉ እያሉ መልዕክት የሚልኩት በተማሪዎቻቸው የትምህርት ቅበላና የፈተና ውጤት ላይ መቀነስ በማየታቸው እንደሆነም ያክላሉ፡፡

ተማሪዎችን ቀርቦና ጠጋ ብሎ መርዳት አለመቻል፣ የሁሉም ተማሪዎች የመማር አቅም እኩል አለመሆን፣ የመማር ማስተማሩ ቀናት መቀነስ፣ ከመምህራንና ከወላጆች የቅርብ ክትትል የሚፈልጉ ተማሪዎች መኖራቸውና ቀድሞውንም በቤት ውስጥ በአስጠኚ የሚታገዙ አሁን እየቀረ መምጣቱ የራሱ ችግር ቢፈጥርም ይህንን ተቋቁሞ ማስተማሩ ተመራጭ ይሆናል ብለዋል ዶ/ር ሩቂያ፡፡

መንግሥት ከሚያወጣው የመማር ማስተማር ሒደት፣ በአጠቃላይ ከትምህርቱ ዘርፍ ተዋናዮች በአሁኑ ሰዓት የወላጆች ሚና ከፍተኛ ነውና ወላጆች በቻሉት አቅም ሁሉ ልጆቻቸውን እንዲያግዙና እንዲከታተሉ፣ ስለልጆቻው ከመምህራን ጋር እንዲመካከሩ፣ ልጆቻቸውን በአዎንታዊ መንገድ እንዲያበረታቱ፣ ዝቅተኛ ውጤት ቢያስመዘግቡ ሊያሻሽሉ የሚችሉበት መንገድ ስለመኖሩ እንዲጠቁሙ፣ ለሚፈጠሩ ክፍተቶች ሁሉ የመፍትሔ አካል እንዲሆኑም ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...