ከአገሪቱ ጠቅላላ ተሽከርካሪዎች ከ70 በመቶ በላይ በሚገኙባት አዲስ አበባ ከተማ፣ ከተሽከርካሪዎች በሚወጣው በካይ ጋዝ እየደረሰ ያለው ችግር ከፍተኛ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው ላለፉት ስምንት ወራት በተሽከርካሪዎች ምክንያት የሚደርሰውን የበካይ ጋዝ ተፅዕኖ የተመለከተ ጥናት ሲያከናውን መቆየቱን ገልጾ፣ የጥናቱ ውጤትም በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የከባቢ አየር ብክለት ክትትልና ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አክሊሉ አደፍርስ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በቢሮው በተደረገ ጥናት ከ70 በመቶ በላይ የአገሪቱ ተሽከርካሪዎች በሚገኙባት አዲስ አበባ ዕድሜያቸው ከ15 ዓ.ም. በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡
ከፍተኛ ዕድሜ ያላቸው ተሽከርካሪዎች የካርበን ጭስ የማጣራት ቴክኖሎጂያቸው ኋላቀር እንደሆነ ያስታወቁት ባለሙያው፣ በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ የሆነ በካይ ጋዝ በከተማዋ እንደሚለቀቅ ገልጸዋል፡፡
ከአገሪቱ አቅም ውስንነት አንፃር ለፍጆታ የሚያገለግለው የነዳጅ ጥራት ደረጃ ለበካይ ጋዝ ልቀት አንዱ ምክንያት እንደሆነ ያስታወቁት አቶ አክሊሉ፣ ብዙዎቹ ተሽከርካሪዎች ምርመራ የሚያደርጉት በዓመት አንዴ ብቻ መሆኑ ሌላው በከተማዋ ላይ እየደረሰ ላለው የአየር ብክለት ዋነኛ መንስዔ እንደሆነ አክለዋል፡፡ በአብዛኛው ከመኪና የሚውጡ በካይ ጭሶች በደንብ ሳይቀጣጠሉ የሚወጡ ጋዞች (ኢንኮምፕሊት ካርበን ሪአክሽን) እንደሚባሉ የገለጹት አቶ አክሊሉ፣ የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው እነዚህ ብናኝና ጭሶች ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር ያስከትላሉ ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ በተመረጡ ሆስፒታሎች ከበካይ ጋዝ ልቀት ጋር በተገናኘ ያለውን መረጃ ለመሰብሰብ እንደተሞከረ ከፍተኛ ባለሙያው አስታውቀው፣ በዚህም ከመተንፈስ ችግር ጋር የተገናኙት አብዛኞቹ በሽታዎች ዋነኛ መነሻቸው ከአየር ብክለት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች በካንሰር በሽታ እንደተያዙ ቢነገርም መነሻውን ወደኋላ መልሶ የማየት ልምድ እንደሌለ ያስረዱት አቶ አክሊሉ፣ ሆኖም በጤና ተቋማት ያሉ ባለሙያዎች በጥናቱ ወቅት እንዳረጋገጡት የአየር ብክለት ችግር ዋነኛው የበሽታው መንስዔ ነው ማለታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በጥናቱ ወቅት የተለያዩ ተሽከርካሪዎች እንደ ሥሪት ዘመናቸውና አገልግሎታቸው በመውሰድ የጭስ ማውጫቸው ላይ በመሣሪያ የታገዘ ናሙና መወሰዱን፣ በዚህም ከተሽከርካሪዎቹ የተገኘው ውጤት ለበካይ ጋዝ ልቀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ጥናቱ ከዚህ በበለጠ በስፋት ሊሠራ እንደሚገባ፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የችግሩን ስፋት በትክክል ዓይቶ መፍትሔ ለማስገኘት፣ ‹‹የከባቢ አየር ብክለትና ቁጥጥር ስትራቴጂ›› እያዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የስትራቴጂው መዘጋጀት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ማለትም ትራንስፖርት ቢሮ፣ የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት፣ የአካባቢ ጥበቃና ሌሎች አካላት እንደ ድርሻቸው ሊያከናውኑ የሚገባቸውን ዝርዝር ሥራዎች እንደሚያግዝ ቢሮው አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከ630 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙ በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩ ሲሆን፣ ከአገሪቱ የተሽከርካሪ ሥርጭት ከ70 በመቶ በላይ መሆናቸውን፣ አብዛኞቹም ተሽከርካሪዎች በናፍጣ የሚሠሩ፣ ለአየር ብክለትና ለተያያዥ ችግሮች መንስዔ እንደሆኑ ያመላክታሉ፡፡