በ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል ከወለድ ነፃ የሆነ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ለማቋቋም ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን፣ ቢላል ማይክሮ ፋይናንስ አክስዮን ማኅበር አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ ይህንን የገለጸው ዓርብ መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን፣ በወቅቱም በገንዘብ ዕጦት ምክንያት ወደ ሥራ መግባት ላልቻሉ የሥራ ፈጣሪዎችና በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች ወደ ተለያዩ ሥራዎች እንዲሰማሩ ብድር ለማመቻቸት አልሞ የሚንቀሳቀስ ነው ተብሏል፡፡
የቢላል ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማኅበር ሰብሳቢ ከማል አብዱልሞሀብ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ማኅበረሰቡ የፋይናንስ አጠቃቀምን አውቆና የቁጠባ ባህልን አዳብሮ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግ ማኅበሩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
ማኅበሩ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አክሲዮን ለመሸጥ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ ለመግባት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ከማል (ዶ/ር) በስድስት ወራት የጊዜ ገደብ ውስጥ የአክሲዮን ሽያጭ በማከናወን ማኅበሩ ለምሥረታ እንደሚበቃ ተናግረዋል፡፡
በአነስተኛ በጀት ወደ ሥራ ከተሰማሩና መሰማራት ከሚፈልጉ ወጣቶች፣ በተለይም ከሴቶች ጋር በጋራ ለመሥራት በሚደረገው ርብርብ ማኅበሩ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አክለዋል፡፡
በአጠቃላይ ለሽያጭ የቀረበው አክሲዮን 100 ሺሕ ሲሆን፣ የአንድ አክሲዮን ዋጋ 1,000 ብር መሆኑን፣ ከፍተኛ አክሲዮን ለመግዛት እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር እንደሚፈቀድ አቶ ከማል ገልጸዋል፡፡
የአክሲዮን ሽያጩንም በተለያዩ ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ የሆነ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ፣ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማኅበረሰቡ አክሲዮን በመግዛት ሥራ ፈጣሪዎችን በማሳደግ በአገሪቱ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በተወሰነ ደረጃ መቀነስ ያስፈልጋል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የአገልግሎት ቅድመ ክፈያው ሰባት በመቶ ሲሆን፣ የአክሲዮን ሽያጩም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በዳሸን ባንክ፣ በአዋሽ ባንክ፣ በአቢሲኒያ ባንክና በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የሚካሄድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡