Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በምርት ብክነት ቅነሳ ቴክኖሎጂ ላይ የሚሠሩ ተቋማትን እንደሚደግፍ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን አገራዊ የእህል ምርት ብክነት ለመቀነስ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚሠሩ ተቋማትን እንደሚደግፍ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ረቡዕ መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ፉድ ዘ ፊውቸር ቫሊዩ ቼይን አክቲቪቲ (FTF-VCA) የተሰኘው ፕሮጀክት፣ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የገንዘብ ድጋፍ፣ በአራት ክልሎች የእህል ምርት ብክነት ለመቀነስ ከአገር በቀል ድርጅቶች ጋር የሠራቸውን ተግባራት አስተዋውቋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ግብርና ሚኒስቴርን በመወከል የተገኙት በሚኒስቴሩ የግብዓትና የምርት የግብይት ዘርፍ አማካሪ አቶ ደረጀ አሳምነው፣ ‹‹ጥናቶች እንደሚያሳዩት እስከ 30 በመቶ የሚደርሰው የአርሶ አደሩ ምርት በድኅረ ምርት መሰብሰብ ወቅት የሚበላሽ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ሦስት መሠረታዊ ትልሞችን ለማሳካት እየሠራ እንደሆነ ያስታወቁት አማካሪው፣ በዚህም ዜጎች በቂ የግብርና ምርት የሚያገኙበትና በምግብ እህል ራስን የሚችሉበትን ዘዴ፣ ኤክስፖርትን መሠረት ያደረገ የግብርና ቴክኖሎጂ መፍጠርና በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለተቋቁሙ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጉ ግብይቶችን የማቅረብ ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ ምርትን ከሰበሰበ በኋላ ለማከማቸት የሚጠቀምባቸው ግብዓቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸው፣ የምርቱ አቀማመጥ ኃላቀር በመሆኑ በነቀዝ፣ በተባይና በሻጋታ የአርሶ አደሩን የምግብ እህልና ዘር ይጎዱ እንደነበር አቶ ደረጃ አስታውቀዋል፡፡

በፉድ ዘ ፊውቸር ቫሊዩ ቼይን አክቲቪቲና በሦስት አገር በቀል ተቋማት የቀረበው ከኬሚካል ነፃ የሆነ አየር የሚያስገባ ማዳበሪያ ከረጢት ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩ የሚያመርተውን ምርት ከእርጥበት፣ ከነቀዝና ከተባዮች በማፅዳት በተፈጥሮ አየር በመስጠት ዘዴ ብቻ በመጠቀም ምርቱን እንዲያከማች የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በፉድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ የሰብል እሴት ሰንሰለት አማካሪ አቶ ሀብታሙ ፀጋዬ ፕሮጀክቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች አየር የሚያስገባ የግብርና ከረጢት ቴክኖሎጂን ሐይቴክ ትሬዲንግ፣ ሻያሾኔና ኤጋ ከተባሉ የግብር ምርት አቅራቢ ድርቶች ጋር ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ የድኅረ ምርት ብክነት ለመቀነስ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂን ማግኘት እንደሚገባው የገለጹት አቶ ሀብታሙ፣ ሦስቱ አገር በቀል ተቋማት አየር የሚያስገባ ከኬሚካልነ ነፃ የሆነ ምርት ማከማቻ ከረጢት የማስተዋወቅና የማዳረስ አቅማቸው ውስን በመሆኑ ፉድ ዘ ፊውቸር ከሥርጭትና ማስተዋወቅ አንፃር ያለውን ክፍተት ለመሙላት እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የሻያሾኔ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ሰርፀ እንደሚያስረዱት፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደ 300 ሚሊዮን ኩንታል እህል የምታመርት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ወደ 36 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው በነቀዝና በተባዮች ይበላል፡፡

ያለ ምንም ኬሚካል የተዘጋጁ ባለሦስት ድርብርብ የእህል ማከማቻ ከረጢትን ድርጅታቸው በአራቱ ክልሎች በሚገኙ 1,000 የሚደርሱ ገበያዎች፣ 11,000 በሚደርሱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ከኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር ለአርሶ አደሩ መቅረቡን የገለጹት አቶ ያሬድ፣ ከቀረቡ ከረጢቶች ሁለቱ ድርብርብ ፕላስቲክ በመሆናቸው አየር ስለማያስገቡ ተባይ ገብቶ መራባትም ሆነ ምርትን ማበላሸት እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር በተለይ ግብርናን መርጠው ለሚሠሩ የግል ባለሀብቶችም ሆነ ተቋማትን ቀርቦ በማነጋገር ረገድ ትልቅ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ የገለጹት የግብርና ሚኒስቴር አማካሪው አቶ ደረጀ፣ የምርት ብክነት የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች