Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየሃይማኖት ፖለቲካ ምርኩዝ ያስፈለገው አንካሳ የነገድ ፖለቲካ!

የሃይማኖት ፖለቲካ ምርኩዝ ያስፈለገው አንካሳ የነገድ ፖለቲካ!

ቀን:

በሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

አገራችን ምርት ሳታሳድግ የበዛ አፍ ፈጠረችና ምግብ ካጣ አፍ የሚጎለጎለው በአገራችን ታሪካዊ ጠላቶቿ የግፊት ኃይል የሚስፈነጠረው የሾለ ምላስ አገር እየቀደደ፣ ሕዝብ እየቦጫጨቀ ለእኛው ሁሉ የሕልውናችን አደጋ ሆነብን፡፡ የነገድ ፖለቲከኞች ምላስና መሰሪ ተግባር፡፡ ይህን የነገድ ፖለቲካ ምላስ ሁሉም ወደ አፍ ወናው ተግባብቶ ካልመለሰ ከእንግዲህ ፈጥኖ ምላሱን የሚመልስ ሌላ ማንም ይኖራል ብየ አልገምትም፡፡ አደብ ያደረገ ምላስ የነበራቸውም የበለጠ ምላስ አውጥተዋል፡፡ የፉክክር ደጃፍ ሳይዘጋ አደረ እንዲሉ፡፡

በነገድ ስም በተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእጅጉ ስንቸገር ኖረን፣ አሁን ደግሞ የሃይማኖት ፓርቲዎች የመፈልፈያ ኢንኩቤተር ተፈበረከልን፡፡ ሁኔታው ‹‹የንጉሥ ዝሆን›› ጉዳይ ሆነብን፡፡ ንጉሡ የለቀቋት አንዲት ብርቅየ ዝሆን አዝመራቸውን ያወደመችባቸው ምስኪን አርሶ አደሮች ዝሆኗን ከስሰው ለአቤቱታ ንጉሥ ፊት ቢቀርቡ፣ ሌላ ዝሆን ጨምረው ወደ የቤታቸው ተመለሱ የተባለው ዓይነት ማለት ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የ86 ነገዶች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቆጥረን ለመረከብ ስንጠባበቅ የሃይማኖት ፓርቲዎች ተጨመሩልን፡፡ እነዚህም በየሃይማኖት ዘውጋቸው ስም ተጨማሪ ፓርቲዎችን የሚፈለፍሉ ከሆነ፣ የትየለሌ የሃይማኖት ፓርቲዎች ብቅ ብቅ አሉ ማለት ነው፡፡ ይህ በተፈጸመ ጊዜ ውድ አገራችን ኢትዮጵያ በፓርቲ የበለፀገች አገር ሆና ‹‹በጊኒየስ ቡክ ኦፍ ኢንሳይክሎፔዲያ›› ላይ ስሟ ስለሚሰፍር፣ በዚህ አዲስ ገጽታ ጭምር ትታወቅልናለች፡፡ ለእኛም ተጨማሪ መታወቂያ ይሆነናል ብለን የምናስብ ቅን ዜጎች እንኖር ይሆን? ይህን አላውቅም፡፡

የእኛ አገር የፖለቲካ ልሂቃን በጣም መሰሪና ጥበበኞች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የዋሆችን ሲያስፈልግ በማሳመን አለዚያም በማኮናፈዝ የልብን ማሳካት እንዳሉን ፖለቲከኞች ማለት ነው፡፡ የፖለቲካው ሒደት ግቡ ታች በረንዳ ላይ ለቆሙት የዕለት ዳቦ፤ ጣሪያ ላይ ለተንጠላጠሉት ደግሞ የኑሮ ድሎት የሚያከፋፍል የኪራይ መሰብሰቢያ ጽንፈኛ የቡድን ፖለቲካ እንጂ፣ እነሱ ባደኸዩት ሠፊው ሕዝብ ችግር ላይ የሚያተኩር ፖለቲካ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሕዝብን ውስብስብ ችግር ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡

ለምሳሌ የትግራይ ሕዝብ የጣሳ ውኃ ጠርሮበት በሴፍቲኔት ምፅዋት ዱቄት እየተበተነለት በከፋ ድህነት ውስጥ ሲኖር በትግራይ ሕዝብ ስም ሲምል ሲገዘት፣ ያዙኝ ልቀቁኝ ይል የነበረው የአገራችን የብሔር ፖለቲካ አስተማሪ መሐንዲስ [ጁንታው] በዶላር ውቅያኖስ ውስጥ ሰምጦ ከሚኖርበትና ዓለምን ከጨበጠበት የሞቀ ቤተ መንግሥት የሕዝብ ትግል የከፈተው የጎርፍ ማስተንፈሻ ቦይ ከእነ ዶላሩ ዋሻ ውስጥ ሸርኩቶ እንደቀበረው ዓይተናል፡፡ የማንም ብሔር ፖለቲካ መዳረሻ ይኸው ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ የመጨረሻ ፍርድ እስኪመጣ ድረስ ለምን ይጠበቃል? ለምን እንደ ሰው ማሰብ ተሳነን? ለምን ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ወዘተ. የሚል ፓርቲ ያስፈልገናል? ያሳለፍናቸው 60 የብሔር ትግል ዓመታት እንዴት የሐሳብ ዕድገት በማስገኘት በሐሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ እንደ ሠለጠኑትና በኢኮኖሚ እንዳደጉት የበለፀጉት አገሮች መንገድ መንገድን መያዝ አቃተን? እኛ ለምን እዚያው ላይ ቀንጭረን ቀረን ብለን እንጠይቅ፡፡

የነገድ ፖለቲካ ሁለመናችንን አገለማው፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ የነገድ ፖለቲካ ጣሪያ ላይ ሲደርስ የሃይማኖት ፖለቲካ ምርኩዝ ድጋፍ ያስፈለገው አንካሳ ፖለቲካ መሆኑ ነው፡፡ ግብፅና ሱዳንን ጨምሮ የፖለቲካው ገፊ ኃይሎች የሆኑት የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ሰልችተው፣ ከእንግዲህ ወዲህ የነገድ ፖለቲካ ኢትዮጵያውያን ንሱ በቃችሁ ቢሉን እንኳ የለም አይበቃንም የሚሉ የፖለቲካው ሱስ የሰረጃቸው ዜጎች ከመካከላችን እንደማይታጡ እገምታለሁ፡፡ በነገድ ፖለቲካ የሠለጠኑ የተካኑ ዜጎች በብዛት በማስመረቅ ጎጆ አውጥተውናልና፡፡ ኢሕአዴግ ማብቃት ይል እንደነበረው፡፡ እህህህህ. . .

በአገራችን ነገዶች መኖራቸው የታወቀው ከዛሬ 5,000 ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ከዚያ ሩቅ ዘመን ጀምሮ ነገዶቹ በተለያዩ የእርስ በርስ መስተጋብር ሒደቶች በጦርነት፣ በፍልሰት፣ በሰፈራ፣ በንግድ፣ በወዳጀ ግቢ እየተቀላቀሉ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖትም እየተቀያየሩ እዚህ ስለደረሱ አሁን ያለነው የአገሪቱ ሰዎች ማንኛችንም ብንሆን እኔ የዚህ ነገድ አባል ነኝ፡፡ አሁን የምከተለው ሃይማኖትና የምናገረው ቋንቋ የአያት የቅድመ አያቴ ነበር ለማለት የማንችል ነን፡፡ ለባዕድ ጠላቶች ፍላጎት ማሳኪያና ለፖለቲካ ኪራይ መሰብሰቢያ ስንል ዓይናችንን በጨው ታጥበን በድፍረት ከምንክድ በስተቀር፣ ደማችን/ዘረመላችን ስለተቀላቀለ ሁላችንም የኢትዮጵያዊ ነገድ ሆነናል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ውጪም ሌላ ብሔርተኝነት አለን ለማለት በቂና አስተማማኝ መረጃ የለንም፡፡ ይህ ድንቅ የአገራችን ልዩ ሁኔታ ነው፡፡ መቼም አገራችን ኢትዮጵያ የማትጠቀስበት ድንቅ ነገር የለም፡፡ ለተጨማሪ መረጃ እኔ የጻፍኩትን ‹‹ቋንቋና ብሔርተኝነት›› መጽሐፍ አንብቡ፡፡ ግን ሁላችሁም ሀቁን አታውቁም እንዳልኩ ተደርጎ እንዳይወሰድብኝ፡፡ እባካችሁ በፈጣሪ ከተሳፈርንበት አስቀያሚ ኋላቀር የነገድ ፖለቲካ መኪና ላይ ሁላችንም እንውረድ፡፡ ነገሩ ሁሉ እየተባባሰ ሄደ እኮ! የተከበሩ ሃይማኖቶችንም ለነገድ ፖለቲካ መኪናው ጎማ ታኮ አድርጎ ለመጠቀም የተወጠነው ሴራ ረዥም መንገድ ሳይጓዝ በአጭሩ ይቀጭ፡፡

ከነገድና ከሃይማኖት ፖለቲካ የፀዳው ብዙኃኑ ዜጋ ሁሉ ይህንን የመቃወም መብት ያለው መሆኑን ተረድቶ ወደ ፊት እየወጣ እምቢ በማለት፣ እነዚህ ጥቂት እኩያንን ጥቂት ጥቂት ቅር ማሰኘት ይጀምር፡፡ እነሱንም ጭምር ማዳን ስለሆነ፡፡ ደጃፉ ተዘግቶ ከሚቃጠል ቤት ውስጥ ከቃጠሎው ተርፎ የሚቀር ምንም የቤት ዕቃ አይኖርም፡፡ አገሩ ሲቃጠል ዝም ብሎ የሚመለከት ዜጋ ህሊና የለውም፡፡ በተለይ ሀቀኛ የሆኑ ምሁራን ለመላው ሕዝብ ይህንን ለማስገንዘብ ተደፋፍረው ጥረት ማድረግ ይጀምሩ፡፡ ማነው አገሩ የነገድና የሃይማኖት ሱሰኛ ምንደኛ ፖለቲከኞች ብቻ ነው ያለው? በሐሳብ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካና ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ሃይማኖት በነፃነት የመከተል መብት የለንም እንዴ? ለምን ይፈራል? የአያቶቻችንን የጀግንነት ውርስ ማን ወሰደብን? ኧረ ተው እባካችሁ፡፡

 መፍትሔው ፖለቲካችን የተመሠረተበትን አድሎኛ ሕገ መንግሥት መሻር፣ ሕገ መንግሥቱ የተሠራበትን በጉልቤ የተዋቀረውን ቋንቋን መሠረት ያደረገ ክልላዊ አወቃቀር እንደነበረው መልከዓ ምድርን፣ ለልማት አመቺነትን፣ የጋራ ታሪክን፣ ባህልንና ሥነ ልቦናን ጨምሮ ሌሎችንም ተገቢ መሥፈርቶችን አካቶ በሕዝብ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ እንዲስተካከል ማድረግ፡፡ ባለፊት 30 ዓመታት የብሔር ፖለቲካው የፈጠረውን የተዛቡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች ማረም፣ የምርት ዕድገትንና የሕዝብ ቁጥርን የሚያመጣጥን የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ አውጥቶ ሕዝቡን አስተምሮ መተግበር መጀመር ይመስለኛል፡፡

አገራችን አሁን የምትገኘው በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነው፡፡ መጪው ምርጫ የአገራችን ፈተና ለሆነው ለዚህ የብሔር ፖለቲካ ችግር መፍትሔ የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ወይም ሀቀኛ ኅብረ ብሔራዊነት አስተሳሰብ ያነገቡ ዕጩዎች ዓላማ የሚያሸንፍበት የምርጫ ጊዜ እንዲሆን የማድረግ የዜግነት ኃላፊነታችንን መወጣት የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡  

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው    [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...