Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትይህንን ምርጫ በየዓመቱ የሚከበር የሁላችንም ታሪካዊ ሀብት ማድረግ እንችላለን!

ይህንን ምርጫ በየዓመቱ የሚከበር የሁላችንም ታሪካዊ ሀብት ማድረግ እንችላለን!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

የተጣመደ ግንኙነት ካላቸው ወገኖች ዘንድ፣ ከየትኛቸውም በኩል አድሏዊ ያልሆነ፣ ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃ አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ የምዕራብ አገሮች ከሰሜን ኮሪያ፣ ከሩሲያና ከቻይና ጋር ያላቸው ግንኙነት ላይ ላዩን የፈለገውን ያህል የሚሳሳቅና ትከሻ የሚተቃቀፍ ቢሆን፣ ከሳቅና ከትከሻ ትቅቅፉ በታች ያላቸውን ባላጋራነት አይዘነጉትም፡፡ ለሥርዓተ-ማኅበራቸው ወገንተኛ የሆኑ የምዕራብ መገናኛዎችም እንዲሁ የፈለገውን ያህል ሚዛናዊና ነባራዊ መረጃ ሰጪ ነን እያሉ ቢመፃደቁም፣ በባላጋራነት በተጠመዱት አገሮች ላይ የሚሰጡት መረጃ ሚዛን ያጣና በጎ ነገራቸው የተቀናነሰበት፣ ከዚህም አልፎ በግልጽም ሆነ በሰዋራ መንገድ የማጠልሸት ፕሮፓጋንዳን ያዘለ መሆኑ አይቀርም፡፡

ባላጋራነት የሚዛናዊ ጋዜጠኛነት፣ የዕውናዊ ግንዛቤና ውሳኔ ጠላት ነው፡፡ ግንኙነቶች በአንድ አገር ውስጥም ቢሆን የባላጋራነት ፈርጅ እስከያዙ ድረስ፣ በዚያ ፈርጅ ውስጥ የገቡ ሰዎች (በ‹ሕዝብ› እና በግል ሚዲያ ውስጥ የሚሠሩ ጭምር) ባላጋራዬ የሚሉትን ወገን የሚጠቅም (ወገኔ የሚሉትን የሚጎዳ) መረጃና እውነት ከመሸፈጥ አይመለሱም፡፡ በአሜሪካ ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንትነቱ ጊዜ በእሱ አመራር ላይ ይመጣ የነበረውን ትችትና ተቃውሞ ሃሳዊና ጠላታዊ አድርጎ ከመፈረጅ አልፎ፣ ራሱንና ደጋፊዎቹን የአሜሪካ መድኅን፣ ተቀናቃኞቹን ደግሞ የአሜሪካ ጠንቅ አድርጎ ረድፍ አውጥቶላቸው ነበር፡፡ ስም ያላቸው ጋዜጠኞችና ሚዲያዎች ጭምር በረድፎች ውስጥ እየገቡ የጋዜጠኝነት ተግባር ወይ ትራምፕን የማሳጣት አለዚያም የማሞካሸት ነገር መስሎ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ዶናልድ ትራምፕ ጥቅሙን ለማሳካት በማንኛውም ቀጥተኛና ዘዋራ መንገድ ከመገልገል የማይመለስ ሰው ነው፡፡ በመጀመርያው ምርጫ ጊዜ፣ ተፎካካሪውን ሒላሪ ክሊንተንን ባልተጠበቀ አኳኋን ማሸነፉ፣ ሒላሪ ክሊንተን በውጭ ጉዳይ ኃላፊነቷ ጊዜ የተጻጻፈቻቸው ከመንግሥት ጉዳይ ጋር የተያያዙ የ‹‹ኢሜይል›› ግንኙቶቿ በምርጫው መዳረሻ ላይ ለአደባባይ ከመዘርገፋቸው ጋር በቅርብ የተገናኘ ነበር፡፡ በሁለተኛውም ጊዜ ተፎካካሪውን ጆ ባይደንን ለመጣል፣ ጆ ባይደን የነበረውን መንግሥታዊ ሥልጣን ቤተሰባዊ ለሆነ ሕገወጥ ተግባር አውሎታል የሚል ማስረጃ ለማግኘት የራሱን የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ያላግባብ እስከ መጠቀም (የዩክሬይንን መሪ በመያዣ ለማስገደድ እስከ መሞከር) የደፈረ ነውር ሠርቷል፡፡ ያ ቢከሽፍም ስለእሱ የሚነገረው የአመራር እንከንና ጥፋት ሁሉ ሐሰተኛ የጠላትነት ሥራ ተደርጎ እንዲታይ ከመጣር አልቦዘነም፡፡ ከዚያም አልፎ ሁለተኛው ምርጫ ገና ከመጀመሩ በፊት የምርጫ ውድድሩ በሀቅ ከተካሄደ እንደማይሸነፍ፣ ከተሸነፈ ግን ምርጫው ተጭበርብሯል ማለት ነው የሚል ድምዳሜ በደጋፊዎቹ ዘንድ እንዲለመድና እንዲታመን ለማድረግ ያለውን ብልጠት ሁሉ አውሏል፡፡ የዶናልዶ ትራምፕ አመራር ከቀን ወደ ቀን ተቀባይነቱ እያሟሸሸ እንደ መሄዱና ከጆ ባይደን ጋር የነበረው የምርጫ ውድድር ለእሱ እንደማይሆን እንደ መገመቱ፣ የምርጫውን አካሄድና ውጤቱን ኢ-ተዓማኒ ለማስባል የሚችለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

የትራምፕና የደጋፊዎች ውንጀላ በጠንቃቃ የሰነድ አያያዝ፣ በድጋሚ ቆጠራና በፍርድ ቤት ብያኔ ሁሉ ፉርሽ ቢሆንም፣ እነ ትራምፕ ለመቀበል አልፈቀዱም፡፡ ‹ካፒቶል ሂል› የጆ ባይደንን ተመራጭ ፕሬዚዳንትነትን የማወቅ ሥነ ሥርዓት ላይ በነበረበት ሰዓት፣ ትናንትናን ናፋቂና ዘረኞች ሁሉ የተገማሸሩባቸው የትራምፕ ደጋፊዎች በካፒቶል ሂል (በአሜሪካ ምክር ቤታዊ ተቋም) ላይ ዓለምን ያስደነገጠ ጋጠወጥ አመፅ አካሄዱ፡፡ በመገናኛ ብዙኃን በተለቀቁት የምሥል ቅጂዎች ውስጥ ነውጠኞቹ ዴሞክራት እንደራሴዎችን ቢያገኙ ኖሮ ከመጨፍጨፍ የማይመለሱ እንደነበሩ (‹‹እከሊት የት ነው ያለሽው?›› እያሉ ሲያስሱ ሁሉ) ተመልክተናል፡፡ አደገኞቹ ነውጠኞች ገና በቅዋሜ ሲያንዣብቡ የዶናልድ ትራምፕ መንግሥት በቂ የጥበቃ ኃይል በተጠንቀቅ አለማሰማራቱ አጥጋቢ ምላሽ ያላገኘ ክፍተት ነበር፡፡ በቪዲዮ ምሥል ያየነው የመስኮትና የበር ግንጠላ ሁሉ ተራ የሕንፃ መደፈር ሳይሆን፣ የአሜሪካ ዴሞክራሲ ከፍተኛ አምባ መደፈር ነበር፡፡ ይህ በራሱ ታላቅ ቅሌት ነበር፡፡ ረዥም ዕድሜን በጠገበ ዴሞክራሲ ውስጥ የአገሪቱ እንደራሴዎች አስተማማኝ ጥበቃ አጥተው ነፍሳቸውን ለማዳን ሲራወጡ ማየት ሌላ ግዙፍ ቅሌት ነበር፡፡ ‹‹የተባበረችው አሜሪካ›› የሚለው ነባር መጠሪያ በሽሙጥ ‹‹የተከፋፈለችው አሜሪካ›› ወደሚል መቀየሩ፣ በአንድ የምርጫ ዘመን ውስጥ በአሜሪካ ዴሞክራሲ ላይ ምን ያህል መጎሳቆል እንደ ደረሰ የሚገልጽ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ጥፋት ደርሶና እኛ ከርቀት ለመታዘብ እንደቻልነውም ዶናልድ ትራምፕ ለነውጠኞች መነሳሳት የራሱን አስተዋፅኦ ያደረገ ሆኖ ሳለ፣ የዚህ ዓይነቱ ማጋጣ ተግባር እንዳይደገም ትምህርት እንዲሆን ዶናልድ ትራምፕን ዳግመኛ ለፕሬዚዳንትነት እንዳይወዳደር ማገድ ተሞክሮ መክሸፉ ብዙዎችን ሳያበሽቅ አይቀርም፡፡ የዶናልድ ትራምፕን ተጠያቂነት ያለ የሁለት ሦስተኛ የድምፅ ስምምነት በሴኔቱ ምክር ቤት ውስጥ የታጣው፣ ትራምፕን ጥፋተኛ ለማለት የሚያበቃ ማስረጃ ቸግሮ ሳይሆን፣ ባላጋራዊ ወገንተኛነት ሀቅ እስከ መካድ ድረስ ስለወሰደ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከሥልጣን ከተሰናበተ በኋላ የተካሄዱ የመረጃ ፍልፈላዎች ነውጠኞቹ ከፀጥታ አስከባሪዎች ውስጥም የሻጥር አጋዦች እንዳላጡም አጋልጠዋል፡፡ ባላጋራዊ ግንኙነት፣ አሜሪካን በሚያህል ዴሞክራሲ ውስጥ ይህን ያህል ከእውነት ጋር ሲያጣላና የፀጥታ ሙያተኞችን ወደ ፖለቲካ ሲስብ ካየን፣ ኢትዮጵያን በመሰለች ለዴሞክራሲ ባይተዋር ሆና በኖረች አገር ውስጥ ባላጋራነት ስንት ነውር ሊወልድ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ የአሜሪካ ልምድ ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ጆሮ የሚበጥስ ድምፅ ያለው ደወል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ‹‹ፖለቲከኞች›› ሃምሳ ዓመት ሊሞላ ለአመል ለቀረው ጊዜ ያህል ባላጋራነት ባልራቀው ፖለቲካ ውስጥ ኖረዋል ማለት ይቻላል፡፡ የከተማውንም የጫካውንም ትግል ያለፉበት የእርስ በርስ ባላጋራነትን ሳያሸንፉ ነበር፡፡ ለሕዝብ ነፃነት ታግለን ድል መታን ያሉም፣ ለሥልጣን በበቁ ጊዜ የጠላትና ወዳጅ አተያያቸውን በረሃ ትተውት አልመጡም፡፡ ታገልንለት ያሉለት ነፃነትና እኩልነት በሥልጣናቸው ጊዜ  ከቃል ምግብነት አለማለፉ ይሁን ግድ የለም፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕጦት አኳያ ቢያንስም፣ በማንነት መኩራትና በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመሥራት በር መከፈቱ እሰይ የሚያሰኝ ነው፡፡ የእኛ አገር ባላጋራዊ ፖለቲካ ግን ይችን ታህሏን ውጤት የማግኘትንም ነገር፣ ትልቅ ኪሳራ (የሕዝብ ለሕዝብ መሸካከር) ግድ የሚከፈልበት አስመሰለው፡፡ እናም አዲስ መጡ የመብት ስብከትና ‹‹ትግበራ›› አንዱ ማኅበረሰብ ሌላውን ጨቋኙና መዝባሪው አድርጎ እንዲያይ ከሚያደርግ መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ ጋር እንዲለወስ ተደረገ፡፡

ሐረርጌ ውስጥ ያለ ብሔረሰብ ልዩነት የተቸገረ ታዳጊ/ወጣት፣ በጎረቤትና በባልንጀራ ቤት ውስጥ ተናጥቆ እየበላና እየለበሰ የሚያድግበት የመተዛዘን ግንኙነት እንግዳ ነገር አልነበረም፡፡ ጎንደር ውስጥ አማራ፣ የትግራዊ ትግሬና የኤርትራ ትግሬ የሚል መንጓለል ያልነበረበት መዘማመድ ነበር፡፡ ባለቻቸው የኑሮ አቅም የተቸገሩ ልጆችን ለማሳደግ ዓይናቸውን የማያሹ ብዙ እንስፍስፍ እናቶች የሚያበቅል ማኅበራዊ ማኅፀን በኢትዮጵያ እንደነበረን አበበች ጎበናና እሳቸውን የመሰሉ እናቶች ማሳያዎች ናቸው፡፡ አበበች ጎበና መክበሪያ የሚሆነኝ ‹‹ኤንጂኦ›› ልጀምር የሚል ጮካነት የማያውቃችው፣ በኋላም በዚህ ዓይነት ነጋዴነት ያልጎደፉ የኢትዮጵያዊ ደግ እናትነት ተምሳሌት ናቸው፡፡ የደሃ ጓዳቸው ያፈራችውን ጉርስ በፍቅር እየፈተፈቱ የተቸገሩ ልጆችን ያጎረሱና ያሳደጉ፣ የተቸገረ ልጅን ልጄ ለማለትና በፍቅር ለማንቆሻበል/ለማቀማጠል ብሔረሰብ/ጎሳ ወይም ጎጥ የሚባል ነገር እንደማያሻው በኢትዮጵያ ማሾ ሆነው ማብራት የቻሉ ሰው ናቸው፡፡ የእሳቸው ማሾነት በክፍልፋይ ወገናዊነትና ባላጋራነት ውስጥ ለሰመጡና በመስመጣቸውም ለሚኮሩ ‹‹ፖለቲከኞች›› የአስተሳሰብ ማረሚያ ትምህርት ቤት የሚሆን ነው፡፡

አካባቢዎችን ከተወሰነ ብሔረሰባዊ ባለቤትነት ጋር አጣብቀን፣ ሌላውን ማኅበረሰብ ባዕድ እያደረግን ስንቀሰቅስና ይህንኑ አድልኦ ለመብት መዋደቅና መብትን ማስከበር አድርገን ስናባዛው፣ ከዚህም ተሻግረን በዚሁ መመዘኛ ሰዎችን በጭካኔ እየቀጣን ስንገድል፣ ንብረት ስናሳጣና ስናፈናቅል፣ እንደ አበበች ጎበና ያሉ ዕልፍ አዕላፍ የእናት እናቶችን በሚያፈራ ማኅበራዊ ማኅፀናችን ላይ መዝመታችን ነበር፡፡ የማቃጠልና የማረድ ወንጀል የፈጸምነው በዚያ ማኅበራዊ ጉያ ላይ ነበር፡፡ ጥቃቶቻችን ማኅበራዊ ማኅፀንን ከማድማት ክፉኛ ከፍተው፣ ‹‹ሌላው ሁሉ ቀርቶብኝ ነፍሴን ከስለትና ከእሳት ባተረፍኩ፣ ተርፌም በቁራሽ ረሃቤን ባስታገስኩ›› እስከ ማለት ድረስ የሕዝብን ሰቆቃ ልክ አሳጡ፡፡ የፖለቲከኞቻችን ‹‹ለሕዝብ መብትና ሐርነት ታጋይነት›› ሄዶ ሄዶ ይዘቱ ሲፈለቀቅ፣ እዚህ ደረጃ ድረስ ሕዝብን መግቢያ ማሳጣትን ተልዕኮዬና ድሌ እስከ ማለት ድረስ አዘቅት መግባቱ ቁልጭ ብሎ ታየ፡፡ እንዲህ ያለው ፖለቲካ በትክክለኛ ስሙ ሲቀመጥ፣ የግፍ ግፍ መዋልን ጥማቴና ዓላማዬ ያለ ፖለቲካ ሊባል ይችላል፡፡ የእኛ አገር ባላጋራዊ ፖለቲካ እዚህ ድረስ ዘቅጧል፡፡

ለመፀፀት የሚችል ልቦና ተርፎን ከሆነም እስካሁን የፈጸምነው ግፍ ከመትረፍረፉ የተነሳ፣ ሊያስጨንቀን ይገባ የነበረው በዚህ ሁሉ በደል የጎዳነውን ሕዝብ ምን ብናደርግ ልንክስ እንችላለን የሚል ንሰሐ ነበር፡፡ አሳዛኙ ነገር በእኛ የበቀል ፖለቲካ ውስጥ እንኳን ንሰሐ ኃፍረትም ሽው ያለ አይመስልም፡፡ ኦነግ ሸኔ ዛሬም  ስብሰባ ያለበት ሥፍራ ድረስ ሳይቀር እየዘለቀ ከተራ ሰዎች አልፎ የመንግሥት ሰው እስከ መግደል ይዳፈራል፡፡ ማንነት እየለዩ በጭካኔ የመግደል ልማዱም ከመቀነሱ በቀር አላባራም፡፡ ከተራማጅ ነኝ ባይነት እየተንከባለለ ወደ ፋሽስታዊነት የዘቀጠው ሕወሓት፣ በአረመኔያዊ ጥቃት የተሞላ ክህደት በኢትዮጵያ አገሩ ላይ ፈፅሞ ከተመታ በኋላ እንኳ ፀፀት አልዘለቀውም፡፡ በርዝራዦቹ አማካይነት በሰላይ ደርጅቶች ሥልት የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ መንግሥት ፀረ ትግራዊ ጨፍጫፊ አስብሎ ለማስመታት ሃሳዊና እጅግ የተዛቡ ሰነዶችን ማቀናበርና ማናፈስ ቀጥሏል፡፡

ዶናልድ ትራምፕን የተካው የጆ ባይደን መንግሥትም እውነት ከማን ጋር እንዳለች ለማጣራት ሳይጥርና ኢትዮጵያ በአሜሪካ ጥቅም ውስጥ ያላትን ቦታ እንኳ በአግባቡ ሳይመርምር ኢትዮጵያን ለመንከስ እያዛጋ ነው፡፡ ዛሬ እኛን በኢሰብዓዊትና ረሃብን የማጥቂያ መሣሪያ በማድረግ የሚከሱን አሜሪካና የተወሰኑ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ምን ያህል ለሰው ፍጡር ሩኅሩኅ፣ ለሰብዓዊ መብትና ለሰው ልጅ ሰላም አሳቢ እንደሆኑ፣ አምባገነኖችን እየጣሉ ምን ያህል ነፃነትንና ዴሞክራሲን እንደጠቀሙም በእነ ሊቢያና በእነ ኢራቅ በደንብ ተምረናል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያና ግብረ አበሮቿ በየመን ላይ የከፈቱትን ወረራ የዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ያገዘችውና የጦር መሣሪያ የቸበቸበችውም፣ ቆዳና አጥንታቸው በረሃብ ለተጣበቀው የየመን ሕፃናት እንስፍስፍ ስለሆነች እንደሆነ ‹‹እናምናለን››፡፡ ጉልበት ያለው ሲያሰኘው ጅግራን አሞራ ነህ ሊል እንደሚችል ሁሉ፣ አሞራንም ጅግራ ነህ ሊልና ሊያወራርድ ይችላል፡፡ የጉልበተኞች ዓለም ዋና ሕግ ይህ ነው፡፡

ስለሰው ልጆች መቆርቆር ለታላላቆቹ ምዕራብ አገሮች የምር ጉዳያቸው ቢሆን ኖሮ፣ ሳዳም ሁሴንን የመጣል ርብርብ ወደ ሰላም የለሽነትና ወደ ተባባሰ የሰዎች ሲዖል መዝፈቁ፣ በቶሎ አካሄድን ለመቀየር በቂ ልምድ ነበር፡፡ ለመማር ስላልተፈለገ ‹‹በሰብዓዊ መብት፣ በሰው ልጆች ደኅንነትና ሰላም›› የመጫወቱ ተግባር በእነ ሊቢያ፣ በሶሪያ ወዘተ… እየተከታተለ ቀጠለ፡፡ ምዕራብ አፍቃሪ ያልሆኑ ሙስሊም-ዓረብ የሚባሉ አገሮች ላይ ጥፋቱ የተደጋገመው፣ የእነሱ እርስ በርስ የመፋጀት አዙሪት ውስጥ መውደቅ በእስልምና ስም የሚካሄድ ፀረ-ምዕራብ አሸባሪነት እንዲቀንስ ይጠቅማል የሚል ድብቅ ሥሌት ይኖርበት ይሆናል፡፡ የዓረቦች መዳከም በዓረብ-እስራኤል መሀል ያለውን ቅራኔ አቻችሎ አካባቢውን ለመቆጣጠር ይበጃል ባይነትም ሊገመት የሚችል ሌላ የሥሌት ምናልባት ነው፡፡ ከዚህ ጋር የመሣሪያ ንግድ ጥቅምና የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት የመሆን አቅም እንዳይፈጠር የማድረግ ዓላማ ሁሉ አብሮ ይታሰባል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ዓይነት ሥሌት ውስጥ ገብታ ይሆን? ኢትዮጵያ እርስ በርስ የመባላት አዙሪት ውስጥ ብትገባ ጥቅሜ ነው ብሎ የሚያስብ አገረ መንግሥት ሊኖር ቢችልም፣ ከምዕራብ ጌታ አገሮች ጥቅም አኳያ ኢትዮጵያ በዚያ ዓይነት ቋት ውስጥ የምትገባ አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የማጋጨት ሻጥሮች እየተደረጉባት እንኳ የእስልምናና የክርስትና ሃይማኖቶች ተግባብቶ መኖር የበለጠ እየጠነከረ የሄደባት፣ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በሁሉም የአገሪቱ ኑሮ ውስጥ የተማመነና የተሳላ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉባት አገር ነች፡፡ በዚህ የሃይማኖቶች ሰላም ረገድ ለዓለምም ለአካባቢዋም አርዓያ የምትሆን አገር እንጂ፣ ለማንም አደጋ የምትሆን አይደለችም፡፡ የእስራኤልንና የዓረቦችን ግንኙነትና የኃይል ሚዛን በማዛባት ሥጋትም የምትታሰብም አይደለችም፡፡ ከዚያ ቀለበት ውጪ ከመሆኗ ሌላ፣ እየጣረች ያለችው ከመካከለኛው ምሥራቅ የሩቅ ጎቤቶቿ ጋር ጎራ ሳትለይና ሳታበጅ ተስማምታ ለመኖር ነው፡፡ ከኃያላን አገሮችም ጋር ባላት ግንኙነት የምታድምበትና የምታድምለት ጠላትና ወዳጅ አገር የላትም፡፡ ከሁሉም ኃያላንና ኢንዱስትሪያዊ አገር ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ወዳጃዊ ግንኙነት የምትሻና ይህንኑ በተግባር እያሳየች ያለች አገር ነች፡፡

‹‹ተግባብታ ለመኖር ትጣር እንጂ፣ ከዓረብ-እስራኤል የፍትጊያ ቀለበት ውጪ አይደለችም፡፡ በዓባይ ጉዳይ ምክንያት ለዓረብ-እስራኤል ጣጣ ማቻቻያነት ግብፅ የምትሰጠውን ግልጋሎት ልትረብሽ ትችላለች›› ብለው የሚያስቡና ይህ እንዳይሆን የሚሠጉ ይኖራሉ፡፡ በዚህ ሥጋት በኩልም ችግር የሆነችው ኢትዮጵያ ሳትሆን ከሥጋቱ ጀርባ ያለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ዓባይን በተመለከተ ኢትዮጵያ እያለች ያለችው ዓለማችን ምድረ በዳ በመሆን አደጋ ውስጥ ባለችበት በዛሬው ጊዜ በአረንጓዴ ልማቴ ዓባይን ላድን (በአስተማማኝ ሁላችንንም እንዲጠቅም ልሥራ) ነው፡፡ እነ ግብፅ ግን በገዛ ጥቅማቸው እየሻጠሩ ነው፡፡ ግብፅ ማንንም ብትይዝና እኔ ነኝ ያለ ተንኮል ቆፍራ ብታገኝ ከኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ መብት ውስጥ እላፊ ጥቅም አስገድዳ/አንጰርጵራ አታገኝም፡፡ ግብፅ እላፊ አስተያየት ልታገኝ የምትችለው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማትና የዓባይ ህዳሴ ግድብ ጥቅሟ መሆኑን እያወቀች መርዶ ማውራቷን ትታ በጎ መግባባት ውስጥ ስትገባ ብቻ ነው፡፡ ግድቡ ቆሞ ወይ ተቦድሶ ቢቀር እንኳ የታች አገሮች በዓባይ ውኃ የመጠቀማቸው ቀጣይነት አይረጋገጥም፡፡ ይህን ለመገንዘብ ኢትዮጵያ ጣናን ለማትረፍ የምታደርገውን ጥረት ቀረብ ብሎ ማየት ነው፡፡ ጣና ቢደርቅ ኢትዮጵያ አረረም መረረ መኖር አይሳናትም፡፡ ዓባይ ግን ያለ ጣና አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያ ግብፅንና ሱዳንን መጉዳት ብትሻ፣ እጇን አጣምራ አምቦጭ አረም ጣናን ሲበላው ማየት ብቻ ይበቃታል፡፡ ስለዚህ ኃያላኑም እነ ግብፅም ዓይናቸውን ገልጠው፣ የኢትዮጵያን አብሮ የመልማት ጥረት በትክክል ቢረዱትና ቢደግፋት ለሁላችንም ይበጃል፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬ ጠላቴ የምትለው ጎረቤት የላትም፡፡ ሱዳን ጦር የመዘዘችው በጠላቷ ላይ ሳይሆን ባመነቻት ባልንጀራዋ ላይ ነው፡፡ ግብፅም እያሴረች ያለችው በገዛ ጥቅሟ ላይ ነው፡፡ በጎረቤቶቿ ላይ አንዳችም የጠላት ሥራ ያልያዘችውን ኢትዮጵያን ከጎረቤት ጋር አባልቼ የጦር መሣሪያ እነግዳለሁ የሚል ኃያላዊ ዓላማ ይኖር ይሆን? ብሎ ለመጠርጠር መሞከርም ትርጉመ ቢስ ነው፡፡ መሣሪያ ለመሸጥ ከደሃው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ይልቅ የሚያከብረው መካከለኛው ምሥራቅ ሆኖ ሳለ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ለእነ ሳዑዲ ዓረቢያ ታስቦ የነበር የጦር መሣሪያ ሽያጭ አሜሪካ አስተጓጉላ የንግዷን አቅጣጫ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አዞረች ብለን ልናማ ብንሞክር አስቂኝ ምፀት ነው፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ በማዕቀብም ሆነ በሌላ ሌላ ዘዴ ኢትዮጵያን ለማነቅ ዙሪያ መዞሯ ምን ጥቅም ባገኝ ብላ ለሚል ጥያቄ መልስ ማግኘት ይቸግራል፡፡ ኢትዮጵያንና ኤርትራን ወደ ማመስ ብትገባ በቀጥታ በራሷ ጥቅም ላይ ነው የምትዘምተው፡፡ ትልቅ የሕዝብ ቁጥር ያለው የሸቀጥና የመዋዕለ ንዋይ ገበያን መበጥበጥ፣ ኃያላዊ ተሻሚዎች ለመጡባት አሜሪካም ይሁን በኢንዱስትሪ ለለሙት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ጥቅም አይሆናቸውም፡፡ የእስልምናና የክርስትና ተግባብቶ መኖሪያ ሠፈርን ማተራመስም ቀጣናው ጠቅላላ የሃይማኖታዊ አሻባሪነት መፈንጫ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ትርምስ የሚያራባው ሥርዓት አልባነትና የድህነት መክፋትም ሌላ ዓይነት ዋጋ ያስፍላል፡፡ ከቀይ ባህር እስከ ሶማሊያ ዙሪያ የባህር ዘራፊ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተራብቶ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ሰላም ማጣቱና የእነ አሜሪካ የጥበቃ ወጪ መናሩም የማይቀር ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር ደግሞ የስደተኛ ጎርፉ በየአቅጣጫው ይብሳል፡፡ ከተጠቃቀሱት ቀውሶች አንዳቸውም የአሜሪካም ሆነ የምዕራብ አገሮች ጥቅም ናቸው ብሎ ለማለት ይቸግራል፡፡ አሜሪካን እንዲህ የሚያብከነክናት ተጓዳኝ ወይ ዘዋራ ጥቅም ሳይሆን፣ በጆ ባይደን መምጣት ተዓምር ተፈጥሮ ለሰው ልጆች ጥቃትና መብት ያላት የማያወላውል ተቆርቋሪነት ነው ብለን እንዳናስብም የአሜሪካ አስተዳደር ከታዋቂ ሚዲያዎቹ ጭምር የወገኑት ግፍ ለተዋለበት ሳይሆን፣ ተራማጅነትን ተከልሎ ግፍ በመዋል ራሱን ሲያሠለጥን ለኖረና ይህንኑ ችሎታውን ታይቶ በማይታወቅ አኳኋን ኢትዮጵያ ውስጥ ለፈጸመ፣ በድሎ በማልቀስ ብልጣ ብልጥነቱም ዓለምን ‹‹እያደናገረ›› ላለ ቡድን ነው፡፡ የቻይና ግስጋሴ አሜሪካና ምዕራባዊ አገሮች ላይ የፈጠረው የሥጋት ጫና ጥቅማቸውን ፈርጅ በፈርጅ የመንከባከብ አስተውሎታቸውን አቦዘባቸው እንበል? ወይስ የሕወሓት ርዝራዦች የቆርጦ ቅጠላ ዱልዱም ‹‹ብልጠት›› ከእነሱ የሥልጣኔ አቅም በልጦ አጃጃላቸው እንበል?

የዚህ ቡድን የተበዳይነት ቱማታ ለጊዜው ሊያሳስት ይችል ይሆናል፡፡ የሕወሓት አረመኔዎች ሆን ብለው አጥምደው ስለፈጁት የመከላከያ ሠራዊትና በማንነታቸው ተለይተው ጨካኝ ግድያ ስለተፈጸመባቸው ሰዎች እንዳልሰማ መሆን ግን የሚያስተዛዝብ አድልኦ እንጂ፣ በአሳሳች መሳሳት ሊሆን አይችልም፡፡ ሚዲያዎች በጠንቃቃ ጋዜጠኝነት የሕወሓቶችን ውስጣዊ ተፈጥሮ ወደ መረዳት በመሄድ ፈንታ ከቀጣፊ ቱማታቸው ጋር እያሽቃበጡ መቆየት ሊጣፍጣቸውም ችሎ ይሆናል፡፡ አሜሪካን የሚያህል መንግሥታዊ ተቋምና ጆ ባይደንን የሚያህል በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የቆየ ሰው ስለሕወሓት/ ኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት የመረጃ ጎተራ ችግር እንደማይኖርባቸው ግን አያጠራጥርም፡፡ ይህንን ያህል ከባድ ክህደትና ጥቃት ተፈጽሞባት የተረፈች አገር አይዞሽ መባል ቢነፈጋት እንኳ፣ አተራረፏ ብቻውን በጦርነቶች ውስጥ ተዘውትረው በሚታዩት በፍርስራሽ መዋጥ፣ የብዙ ሕዝብ መማቀቅና ዕልቂት ሳይደርስ ፈጥኖ (ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ) መከናወኑ፣ በዚህም ቅልጥፍና፣ ሕዝቧንና የአፍሪካ ቀንድን ከመታመስ ማራቋ ክብር ሊሰጠው በተገባ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ከመቶ ሚሊዮን በላይ የያዘ አገረ መንግሥቷን ለማትረፍ በወሰደችው ዕርምጃ ውስጥ ጥፋት ቢገኝ እንኳ ሚዛናዊ ፍርድ የሚያውቅ፣ ጥፋቷን የሚፈርደው በተሰነዘረባት ከባድ ጥቃትና ከዚያ ለማምለጥ ባካሄደችው ጠንቃቃ ጥረት ውስጥ እንጂ፣ ተገኘ የሚባለውን ጥፋት ራቁቱን በወሰደ ወይም ተጠቂነቷንና ለሕዝቦቿ ያላትን ኃላፊነት እንደሌለ አድርጎ በደመሰሰ ዓይን አይደለም፡፡ ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ ተወላጅ አሜሪካውያን ጆ ባይደንና ዴሞክራቶች እንዲመረጡ ያደረጉት ተጋድሎ፣ ኢትዮጵያን በሚዛናዊ ህሊና በመፍረድ የሚገለጽ አክብሮትን ለማግኘትም የሚያንስ አልነበረም፡፡

የኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን ላይ ኢሕአዴግን መርቆ በ1983 ዓ.ም. በማውጣት ክንዋኔ፣ አሜሪካ ዋናውን ሚና እንደ መጫወቷም ለሕወሓት/ኢሕአዴግ እንግዳ ተፈጥሮ ባይተዋር አትሆንም፡፡ የጥቅምት 2013 ዓ.ም. ከፍተኛ ክህደቱን ከክልል እስከ አዲስ አበባ ያቀናበረውና አረመኔያዊ ፍጅቱን ያካሄደው በዋናነት በትግራዊነት ላይ ነግዶ ነበር፡፡ ይህንን ንግዱን የጀመረውም የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን በተቆጣጠረ ጊዜ፣ ለፍትሕ ቀን ሲታገል የኖረውን ተጋዳላይ ለጠባብ የሥልጣን ስስቱ መሣሪያ ሲያደርግ ነበር፡፡ በሰላይ ድርጅቶች ሥልት የግፍ ሥራዎች እያቀነበረ ሕዝብ በደርግ መንግሥት ጨፍጫፊነት እንዲንገፈገፍና ለሕወሓት የትግል አጀንዳ ማገዶ እንዲሆን ማድረግ የጀመረውም፣ እኛ አልገባንም ነበር እንጂ ገና ከበረሃ ትግል ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም. ግንቦት ሥልጣን ከያዘ በኋላም በዚሁ ሥልት ሕዝብ እንዲደነባበርና ከእሱ ጀርባ እንዲወሸቅ ለማድረግ፣ እንዲሁም ሌሎች ቡድኖችን በሽብርተኛነት ሕዝብን የሚፈጁ አድርጎ ለመወንጀል ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ገዥ ለመሆን እየተጣደፈ በነበረበት ጊዜና ሥልጣን ከያዘም በኋላ እንደ ውጭ ወራሪ ምርኮ የመሰብሰብና የማሸሽ ባህርይው ኃፍረት አልነበረውም፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሕወሓት የከፈተው የትም ያልታየ የገዛ አገርን ከውስጥ የመውረር የጉድ ሥራ ጎልምሶ የወጣውም፣ በ1980ዎች ከበረሃ ወደ መንበረ ኢትዮጵያ እየገሰገሰ ሲመጣ ሕዝብ አጀብ እያለ ከታዘበው የምርኮ ሰብሳቢነቱ ባህርይ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እየገዛ፣ ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት የሆኑ ንብረቶችን ‹‹የማረኳቸው/የተወጋሁባቸው ናቸውና አምጡ! ለጊዜው አበደርኳችሁ እንጂ የራሴ ናቸው›› እያለ መተሳሰቡ ለማመን የቸገረ የጉድ ጉድ ነበር፡፡ ፖለቲካ ይገባናል ከምንል ልሂቃን ውስጥ አድራጎቱን ከበረሃ ትግልና ከብሔርተኛነት ባህርይ የመጣ አድርገን ቆጥረን በሒደት ይታረማል የሚል ተስፋ ነበረን፡፡ የአገሪቱን መከላከያና ደኅንነት ሁሉ በሕወሓታዊ ዕዝና ክምችት መያዙም በሴራ የመገልበጥ አደጋ እንዳይደርስበት ዘዴ ያለው እንጂ፣ አገሪቱ ራሷ እንደ ምርኮ መያዟ አልመሰለንም ነበር፡፡ ያን ያህል አገዛዙን አክፍተን አለማሰባችንም ተገቢ ነበር፡፡ እንዲዚያ ያለ የጉድ ሥራ ከኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ላይ ይፈጸማል ብለን ማሰብ የጤና አይደለምና ያንን ያህል ለምን ጤና ቢስ አልሆንም ብለንም አንቆጭም፡፡ እንኳን ከሕወሓት ውጪ የነበርነው፣ ብዙ የሕወሓት አባላትም ሕወሓት ተራማጅ ነው ብለው የሚያምኑ ነበሩ፡፡ ፍትሕንና እኩልነትን ያመጣል የሚል ተስፋም ነበራቸው፡፡ እስከ ላይ ፖሊት ቢሮ ድረስ የነበሩት የድርጅቱ አመራሮችም ቢሆኑ በዓላማ ሥሌት አንድ ዓይነት አልነበሩም፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነትና በኋላም በጦርነቱ አያያዝ ተፈጥሮ የነበረው የአንጃ ልዩነት ለዚህ አንድ ምስክር ነው፡፡

የሕወሓት ገዥዎቻችን ልማት የሚባል ዳስ ተከልለው ሀብት እንዳሸሹ ሁሉ፣ የአገሪቱን ዋና ሜካናይዝድ የመከላከያ አቅም ማዕከል ወደ ትግራይ ለማዞር የኢትዮ-ኤርትራን የ1990ዎችን ጦርነት ተጠቅመውበታል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራን መጠማመድ ማብቂያ የለሽ አድርገውም የሰሜኑ የኃይል ክምችት እዚያው እየደለበ እንዲቆይ አድርገዋል (የአየር ኃይልን የአብራሪ ክምችት ጭምር ሕወሓታዊ ከማድረግ አልፈው፣ የአየር ኃይሉንም ዋና አቅም ወደዚያ ለማዛወር ሞክረው እንደነበርም ይታማሉ)፡፡ ገብረ ኪዳን ደስታን (‹‹…የትምክህተኞች ሴራ›› ደራሲን) በመሳሰሉ ‹‹አወቅን›› ባይ የሕወሓት አባላት አካባቢ ትግራይን የብዙ ነገር ማዕከል የማድረግ ወገናዊነት የተስፋፋ ቢሆንም፣ የኤርትራን ‹‹ጠላትነት›› ለመመከት በትግራይ ጦር ማጠናከርን ተገቢ አድርጎ ከማየት ባሻገር፣ የአገሪቱን ቁልፍ የጦር ኃይል የማሸሹን ስትራቴጂካዊ ሥሌት ሁሉም ሕወሓቶች ያውቁ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ በኋላ መቀሌ እየተሰባሰቡ ዕብሪት በዕብሪት ሲሆኑም እኛ አልተገለጠልንም እንጂ፣ እንደ ምርኮ ሀብት ያሸሹትንና በከባድ መሣሪያ አደርጅተው በሕወሓታዊ ዕዝ ቁጥጥር ውስጥ ያቆዩትን የሰሜን ዕዝ ተማምነው (ያለ ሰሜን ዕዝ አገሪቱ የባዶ ያህል መሆኗን ያውቁ ስለነበር) ኖሯል፡፡ ገና በሦስተኛው ሺሕ ዓመት መባቻ አካባቢም ኢሕአዴግ በሥልጣን ካልቆየ አገሪቱ አርማጌዲዮን ትሆናለች እያሉ ሲያስፈራሩም አለመጠርጠራችን እንጂ፣ የሁሉንም ነገር ቁልፎች በመዳፋቸው ውስጥ አድርገው ኖሯል፡፡

ኢትዮጵያን ሥልጣናቸው እስኪያከትም ድረስ የሚቆዩባት መክበሪያ ቤት አድርገው ያደቡት ጥቂት ሕወሓታዊ የምርኮ ጌቶች፣ ኢትዮጵያን ከመበታተን በማዳን ሽፋን የመውጫ በራቸውን (አንቀጽ 39) አዘጋጅተው ከግማሽ ምዕት ዓመት ላላነሰ ጊዜ የመግዛት ሐሳብ የነበራቸው ቢሆንም፣ እስከ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ድረስ ያሳለፉት ጊዜ በመደናበር የተሞላና በአገር አስቦጥቧጭነት የተጠመዱበት ምዕራፍ ነበር፡፡ በውጤቱም በድርጅቱ ውስጥ ከነበሩ አገር ወዳዶች መሀል ከተወሰኑት ጋር ተሻኩተውና ተቆራርጠው መለያየት ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ የመሰንጠቁ አደጋ ከተወገደ በኋላ ከልማት ከበሮ ጋር ለረዥም ጊዜ የመግዛቱ ዕቅድ ቢሞቅም የልማት ድለቃው በ2008 ዓ.ም. አርጅቶ እስከ 2010 ዓ.ም. የነበራቸው ቆይታ የተንገሸገሸ ቅዋሜ ያልተላቀቀው ነበር፡፡ ከ2010 ዓ.ም. መጋቢት የለውጥ ጅምር አንስቶ እስከ ጥቅምት 2013 ዓ.ም. የነበረው ቆይታቸው ደግሞ ደግነው ያቆዩዋቸውን አማራጮች የሞከሩበት ነው (ለቡደሳ ቀላል ነው ብለው ባሰቡት አቅጣጫ በኩል አገር ፍርከሳን ማስጀመር፣ ለሕገ መንግሥት ታማኝ በመሰለ ማሞኛ ፌዴሬሽኑን ወደ ኮንፌዴሬሽን መቀየር፣ በመጨረሻ ደግሞ ውስጣዊ ወረራ ማካሄድ)፡፡

ለጦርነት ሲዘጋጁ በቆዩበት ጊዜ ብዙ የክልሉን በጀትና የሕዝቡን ጥሪት ከመሻማታቸው በላይ፣  የአያሌ ታዳጊ ወጣቶችን ህሊና በፕሮፓጋንዳ አጥበው የጦርነት ማገዶ ለማድረግ አልሳሱም፡፡ ጨካኙን የውስጥ ወረራ ከከፈቱ በኋላም፣ ከአካባቢ መንግሥትነት ወደ ዘርፎ በልነትና ወደ መሠረተ ልማት አውዳሚነት ባህርይ ለመውረድ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ ስንትና ስንት ልጆቹን ገብሮ ለፍትሕና ለእኩልነት የተዋደቀው የትግራይ ሕዝብ እንደ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ የረባ የኑሮ ለውጥ እንኳ አለማግኘቱ ሳያንስ፣ የግፍ ጦርነት ከፍተው የፀጥታ ደኅንነት እንኳ በተወደደበት የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ከወሮበሎች ጋር ተናጥቆ በመኖር ውስጥና በተስፋፋ ዕርዳታ ጠባቂነት ውስጥ እንዲወድቅ ዳረጉት፡፡ ለትግራይ ሕዝብ የሚታገሉ የሚያስመስሉት ዱርዬዎች ሕዝብ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ሕመማቸው ሆኖ ለነፍስህ እንድረስ እንኳ አላሉትም፡፡ ጦርነት ከእንግዲህ በቃህ አላሉትም፡፡ አሁንም ከከተማ እስከ ገጠር ድረስ በግድያዎች፣ በዘረፋዎች፣ በኢኮኖሚና በልማት ሻጥሮች ለተሞላ የሽምቅ ውጊያ አውድማ እንዲሆንና ልጆቹን እንዲገብር ለማቄል እየፋጨሩ ነው፡፡    

ቀጣፊዎች ሺሕ ጊዜ ቢፋጭሩም፣ ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ የኢትዮጵያ ኅረብተሰብ በዚህ ዓይነቱ ፖለቲካ ነኝ ባይ የግፍ ሥራ ሳይጠቃና ሳይበረግግ የመኖር አስተማማኝ ሁኔታ ውስጥ መግባት አይበዛበትም፡፡ ይህንን ዕውን የማድረጉ ትግልም የሁላችንም የትግግዝ ኃላፊነት ነው፡፡ ‹‹6ኛ›› የሚባለው የዚህ ዓመት ምርጫ ይህንን የሕዝብን የመኖር ዋስትና አጠናክሮ የሚያስቀጥል ውጤት ማስገኘት አለበት፡፡ በሰላምና በመተሳሰብ ሠርቶ መኖርን ከማጠናከር ጋር፣ ኢትዮጵያ በውስጥ ቀውሷ ጊዜ የደረሰባትን የጎረቤት ጥቃት በብልኅነት መፍታት ይጠበቅባታል፡፡ የኢትዮጵያን ወጣቶች በድንበር ጦርነት መማገድን ፖለቲካ ብለው የሚያራግቡ ቡድኖች ፋታ ያሳጣቸው አገር ወዳድነት ከሆነ፣ ፖለቲካውን ትተው ውትድርና ቢቀጠሩ ይሻላቸዋል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ህላዌ ሦስት ውስብስብ ጉዳዮች አሉት፡፡ የኢትዮጵያ የውስጥ ሰላም፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጣጣ አፈታትና ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘው ድርድር መራመድ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዳሴ፡፡ እነዚህ ሦስት ጉዳዮች አንዳቸው ሌላውን ኪሳራቸው ሳያደርጉ መስተናበርና ውጤታማ መሆን አለባቸው፡፡ ጥንቃቄና ብልህነት የሚያሻው ለዚህ ነው፡፡ ለአንዳንድ የፖለቲካ እንጭጮችና ለአገር ማሰብ ላልፈጠረባቸው በቀለኞች ብልፅግና ፓርቲን በምን ነገር ከሕዝብ ጋር ላፋጥጠው ከሚል ፍላጎት በቀር ልባቸውን የሚያምስ ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ፖለቲካ የጎዱት የዚህ ዓይነት በድንክ ዓላማ የሰከሩ (ሕዝብን ለበቀላቸው ማገዶ ከማድረግ በቀር ሌላ ትርታ የሌላቸው) ሰዎችና ቡድኖች ናቸው፡፡

እንዲህ ያሉት ከአፍንጫቸው የማይርቁ ‹‹ፖለቲከኞች›› በዚህ ምርጫ ላይም፣ ለዳር ድንበርና ለሕዝብ ዕንባ እንስፍስፍ መስለው ማቅራራታቸው አይቀርምና የኢትዮጵያ ሕዝብ በስሜት ኩርኮራቸው ሳይታወር ልብ ሊላቸው ይገባል፡፡ ለእነሱ ሮጦ ወደ ጦርነት መግባት ሌላ ቀውስ ይጎትት አይጎትት ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ስለትግራይ የሚያወሩት ሲዖል፣ ትናንትና እየገዙ የከበሩባትን አገር ጥቅም ሲቀርባቸው ‹‹ጠላት አገር›› ያሉና የእነሱን ዓላማ የሚቃረን ትግራዊን ‹‹ባንዳ›› እያሉ የሚገድሉ ግፈኞችን ይጥቀም አይጥቀም ጉዳያቸው አይደለም፡፡ የእነሱ ‹‹ትልቅ›› ጉዳይ የጠመዱትን ወይም ጠምዶናል ያሉትን ፓርቲ ያለ የሌለ ኃጢያት እያተቱ መበቀል ነው፡፡ አንዳንድ ስሜታዊ መራጮችም ‹‹እንዲህ ከደረሰብንማ! እንዲህ ከተደረገማ! ምርጫዬን ቀይሬያለሁ!…›› እያሉ የድምፅ ካርዳቸውን ከግል ብሶትና ከስሜት መለዋወጥ ጋር ያያይዙታል፡፡ ከእነዚህ ይበልጥ የሚደንቀው ደግሞ፣ በብዙ ሁኔታዎች የሚታገዘውና ከማንም በላይ ዝሆን የሆነው የብልፅግና ፓርቲ ባለው ቲፎዞነት ውስጥ፣ የተፎካካሪ ፓርቲን ዕጩዎችን ለማመናመን ከዚህ ቀደም ሕወሓት/ኢሕአዴግ ይሠራባቸው በነበሩ የማስደንበሪያ ዘዴዎች የመጠቀም አዝማሚያ መከሰቱና ፓርቲው እንዲህ ያለው እርምጥምጥነት ለራሱም ለለውጡም ጉዳት መሆኑን አስተውሎ በይፋ ለማረም ሲፈጥን አለማየታችን ነው፡፡ የአምፖሉ ተምሳሌትነት ይህንን ዓይነቱን ኃላፊነትስ አይጨምር ይሆን? ለውጥ ለዘለቀው ሰውና ቡድን፣ የአሁኑ ምርጫ ያለው ዋጋ ከስሜታዊነትና በቀልን ከማወራረድ፣ እንዲሁም ለብቻ ሥልጣን ከመስቆንቆን እጅግ የላቀና ውድ ነው፡፡ የምርጫ ሒደቱን አልኮስኩሶ ማጉደፍ ኢትዮጵያን ለማነቅ ምክንያት የሚፈልጉ ኃያላንን ከማገዝ አይለይም፡፡ እናም የትኛችንም ብንሆን ተወዳዳሪ ፓርቲዎችንም ሆነ ዕጩዎቻቸውን ለማሽመድመድ የሚካሄድ አፈናን በማስረጃ ከማጋለጥ መቦዘን የለብንም፡፡ ምርጫ ቦርድም አፈናን የመከላከልና ለተፈጸሙ ግድፈቶችና ማስተጓጎያዎች ፈጣን ማቃኛ ለመስጠት ሁሌ ንቁ መሆን ይኖርበታል፡፡

የዚህ አጭር ጽሑፍ ደራሲም በኢትዮጵያ የ‹ምርጫ› ታሪክ ውስጥ አድርጎ የማያውቀውን ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ምርጫ ጣቢያ የሚሄደው፣ የምርጫው ስኬት የአገራችንን ህልውናና ህዳሴ ከማስቀደም ጋር የተጣበቀ ስለሆነ ነው፡፡ ካሉ የፓርቲ አማራጮች ውስጥ ይኼኛው ይሻለኛል ብሎ ድምፁን የሚሰጠውም ጮቤ እየረገጠ ሳይሆን፣ አሉኝ ከሚላቸው ቅሬታዎች ይልቅ የኢትዮጵያን ህልውናና ህዳሴ አብልጦ ነው፡፡

የአሁኑ የምርጫ ምዕራፍ ለዚህ ጽሑፍ ደራሲ ሆኖ የሚታየው በአንድ ቅፅበት ውድድርና ኅብረት ሆኖ ነው፡፡ አጠቃላይ አሸናፊነቱ ወዴት አቅጣጫ እንደሚያመለክት መገመትም አስቸጋሪ አይሆን ይሆናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ምርጫው ወደ ባላጋራዊ ግብግብ ተንሸራትቶ ሰላማዊነቱ፣ ዴሞክራሲያዊነቱና ተዓማኒነቱ መተረቻ እንዳይሆን አድርጎ መንከባከብ ነው፡፡ ፖለቲከኞች በቀልና ጥላቻ እየተፋን የምርጫውን ተዓማኒነትና ዴሞክራሲያዊነት መንግሥት እንዲወጣልን ከጠበቅን የጠበቅነውን አናገኝም፡፡ ትልቁ ዓላማችን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን መገንባት ከሆነ፣ የዛሬ የኢትዮጵያ ህልውናና ለውጥ የሁላችንም የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑ የምር ገብቶን ከሆነም፣ ከምርጫው በኋላም በሚቀጥል የአርበኝት ኅብረት ቀለበት ውስጥ ሆነን ምርጫው መጠማመድ አልባ ሆኖ እንዲዋጣ ሁላችንም መረባረብ አለብን፡፡ ምርጫው የፀብ ደጋሾች መጫወቻ እንዳይሆን በመጠበቁ ቀለበት ውስጥ መንግሥት፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ ዜጎች፣ የፀጥታ ኃይሎችና ፍርድ ቤቶች ሁሉ አሉበት፡፡ ይህ ጽሑፍም ሐሳቦችን የሚሰነዝረው ይህንን የኃላፊነት ማዕዘን ተደግፎ ነው፡፡

ባላጋራዊ መጠማመድንና መስቆንቆንን እስካልራቅነው ድረስ በወገንተኛነትና በሕገወጥነት መበጥበጥን አንርቀውም፡፡ ይህንን ምርጫ መሞላፈጫ ብናደርገው መሳቂያ የምንሆነው ሁላችንም ነን፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ልምድ እንማር! የ200 ዓመት የዴሞክራሲ ልምድ ባላት አሜሪካ ውስጥ መጠማመድ ካደረሰው ጉዳት በእጅጉ እንማር!! ትምህርት የሚገባን ከሆነ፣ ይህችን ምርጫ በየዓመቱ የምትከበር የሁላችንም ታሪካዊ ሀብት ማድረግ እንችላለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...