Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከሰው ሠራሽ የኑሮ ውድነት መንግሥት ይታደገን!

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ስለኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ብልሹነት ብዙ ብለናል፡፡ ለራስ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለኅብረተሰቡና አገርን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ቢበራከቱ ዛሬ የት በደረስን ነበር፡፡ በአገር ውስጥ በቀላሉ የምናመርታቸውንና ልንሠራ የምንችለውን ከውጭ ከምናስመጣ እዚሁ ብናመርት ራስንም አገርንም መጥቀም በቻልን ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ዛሬውኑ የምናተርፍበት ካልሆነ ንግድ አይደለም የሚሉ መብዛታቸው ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡

 ነገሩ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ከውጭ የምናመጣውም ቢሆን በአግባቡና በትርፍ ህዳግ ቢሆን ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ የተጋነነ የትርፍ ህዳግ በመያዝ ሕዝብንና አገርን ማተራመስ የተለመደ ሆኗል፡፡ የአገራችን የግብይት ሥርዓት መበላሸት፣ ሥነ ምግባር ማጠተና ያላግባብ ትርፍ ለማሰባሰብ መጣር መገለጫው ሆኖ መቀጠሉ ይዞብን የሚመጣው ጣጣ እጅግ ሊያሳስበን ይገባል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሸማቹን እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነት አብሰዋል ተብለው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ይኸው ብልሹ የሆነ የግብይት ሥርዓትና ሥነ ምግባር አልባ የሆነው የአነጋገድ ልማዳችን ነው፡፡

በአግባቡ ከማትረፍ ይልቅ ዘረፋ እስኪመስል ድረስ የትርፍ ህዳግን ለጥጦ ገበያውን ማጋል፣ ምርት በመሸሸግ እጥረት እንደተፈጠረ አድርጎ ገበያውን በማተራመስ በጓሮ በስንጥቅ ትርፍ መቸብቸብ እንደ ጀብዱ የሚታይበት አገር ሆኗል፡፡ በትላልቅ የገበያ ቦታዎች በሕጋዊ የግብይት ደረሰኝ ከመገበያየት ይልቅ ያለ ደረሰኝ በመሸጥ የሚፈጸም ሸፍጥ የግብይት ሥርዓቱ ሌላው መገለጫ ነው፡፡

ሌሎች እጅግ በርካታ በሥውር የሚፈጸሙ ይቅር የማይባሉ ድርጊቶች በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ውስጥ የሚታይ ሲሆን፣ በአብዛኛው የራስን ኪስ ከማደለብ ባለፈ ዓላማ የሌላቸው ነጋዴዎች መብዛታቸው የአገራች ከባድ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በጥቅል ሲታይ ዛሬ ከየአቅጣጫቸው የሚሰማው የሸማች እሮሮ በአመዛኙ እንዲብስ ያደረገው ይሉኝታ የሌላቸው ነጋዴዎች በግልና በቡድን የሚፈጥሩት ትርምስ ነው፡፡ ሌላው አደገኛ ነገር ደግሞ ረዣዥም እጅ ያላቸው ደላሎች የገበያ ሥርዓቱ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ እነዚህ ያለንግድ ፈቃድ ገበያ ውስጥ ነግሠው የሚታዩት ደላሎች እንዳሻቸው እንዲፈነጩበት ሜዳው የተለቀቀላቸው በመሆኑ በአግባቡ ከመነገድ ይልቅ ሕገወጥ ተግባራት ጎልተው እንዲታዩ እየሆነ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሲሚንቶ ምርት ላይ ገበያው እያየለ ግልብጥብጥ ያለበት አንዱ ምክንያትም ከዚሁ ቅጥ ካጣው የግብይት ሥርዓታችን ጋር ይያያዛል፡፡ የደላሎች የረዛዘሙ እጆች ማሳያም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሕገወጦች ገበያውን ለመያዝ ፋብሪካው ውስጥ ካሉ መሰሎቻቸው ጋር ተመሳጥረው በአገር የለም የተባለ ሲሚንቶ በጥቁር ገበያ ሲቸበቸብ የምናይበት ምክንያቱም ጨዋነት የጎደለው አሠራራችን የወለደው ጭምር መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡

ባለፈው ሳምንት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሲሚንቶ ዋጋን ለመቆጣጠር ከተሰጠው ማሳሰቢያ በኋላ በጥቁር ገበያ ከ700 እስከ 800 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ቢበዛ 450 ብር መሸጥ መጀመሩን ስንሰማ የአገራችን የግብይት ሥርዓት መቃወስ ሆን ተብሎ በሚፈጸም ደባ መሆኑን እንረዳለን፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን በጥቁር ገበያ ያለ ደረሰኝ ሲቸበቸብ የነበረው ሲሚንቶ አሁን ላይ 450 ብር እንዲሸጥ ሲደረግ ደረሰኝ መቆረጥም ግድ ነው ተብሎ ይህም መተግበር ጀምሯል፡፡ እዚህ ላይ ግን መገንዘብ ያለብን የሲሚንቶ እጥረት ተፈጠረ በተባለበትና አንድ ኩንታል ሲሚንቶ 700 እና 800 ብር ሲሸጥ፣ ኮንትራክተሮች ውለታ የገቡለትን ሥራ ለመጨረስ በተባለው ዋጋ መግዛት ግድ ስለሆነባቸውና ባልተገባ ዋጋ ለገዙት ሲሚንቶ ደረሰኝ እንኳን ባለማግኘታቸው ሒሳባቸውን ለማወራረድ ያልቻሉበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ጉዳዩ አንድ ቦታ የሚቆም ካለመሆኑም በላይ እንደ አገር ብዙ ያሳጣናል፡፡

እንዲህ በውንብድና የተተበተበው የገበያ ሥርዓት ጠንከር ያለ ዕርምት የማይደረግበትና እንደተለመደው የእሳት ማጥፋት ዓይነት ከሆነ ዜጎች በጠራራ ፀሐይ እንዲዘረፉ እንደመፍቀድ የሚቆጠር ነው፡፡

ከሰሞኑ የሲሚንቶ ዋጋን በተመለከተ የታየው አንፃራዊ ለውጥ የሚነግረንም በእያንዳንዱ መሠረታዊ ፍጆታ ምርቶች ላይ የሚፈጸም ያልተገባ ተግባር ከዚሁ ያልተለየ መሆኑን ነው፡፡

ዛሬ በየትኛውም ምርት ላይ የተጫነው የዋጋ ጭማሪ የብር ምንዛሪ ዋጋ ወይም ነዳጅ ስለጨመረ ብቻ አይደለም፡፡ ያልተመጣጠነና ከእጥፍ በላይ የትርፍ ህዳግ መቆለልና ሸማቹንም መንግሥትንም መበዝበዝ ስለተለመደ ነው፡፡

በነፃ ገበያ መመራት ተገቢነት ያለው ቢሆንም ሁሉም እየተነሳ እንዳሻው ዋጋ ሲቆልል ቆንጣጭ ከታጣ ነገም ከአሁኑ የባሰ ያልተገባ የዋጋ ግሽበት መከሰቱ አይቀርም፡፡

አንድ ምርት ከውጭ መጥቶ ሸማቹ እጅ እስኪገባ የሚፈጀው ዋጋ እየታወቀ ይህንን በመሸሸግ ሁሉም የመሰለውን ዋጋ እያወጣ ነግድ ከተባለ ነገም ከዛሬ የባሰ የኑሮ ውድነት ይጠብቀናል፡፡

ስለዚህ የትርፍ ህዳግ ይበጅ፣ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ዋጋቸው ይለይ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን ሁሉንም ያማከለ የገበያ መረጃ ለሕዝብ ይፋ የሚደረግበትን አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ የቁጥጥር ሥርዓታችንን አንዴ የምንጀምረው ሌላ ጊዜ የምንተወው መሆንም የለበትም፡፡

የሕዝብ ምሬት ከዚህም ከመባሱ በፊት መንግሥት ባልተገባ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ይቆንጥጥ፣ መስመር ያስይዝ፣ እያዩ እንዳላዩ የሚሆኑት ላይ ዕርምጃ ይውሰድ፡፡ ሰሞኑን ያየሁትን ትዝብቴን በመወርወር ላብቃ፡፡ 

ከሰሞኑ በገበያ ውስጥ ያየሁትና አፌን በእጄ ያስጫነኝ ነገር ነው፡፡ ብርቱካን ገበያ ውስጥ አልነበረምና የአንድ ኪሎ ብርቱካን ዋጋ እስከ 100 ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ አራት ፍሬ የያዘና በላስቲክ የታሸገ ብርቱካን ሲሸጥ አየሁ፡፡ ከውጭ የመጣ ነው የተባለው ብርቱን አራቱን ፍሬ በ125 ብር ይቸበቸባል፡፡

ያስገረመኝ ይህ ብቻ ሳይሆን የመጣው ከግብፅ ነው መባሉ ነው፡፡ መቼም ብርቱካን ከግብፅ ድረስ ማምጣታችን እንደ ኢትዮጵያውያን ልናፍርበት ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡ በብርቱካን እጥረት ስለተንገላታ ዶላር አውጥቶ ከግብፅ ድረስ ያስመጣው ድርጅትም ቢሆን ድፍረቱ በግሌ አስገርሞኛል፡፡

ወደ ውስጥ ስንገባ በዚህ ጉዳይ ብዙ ነገሮችን መምዘዝ የምንችል ቢሆንም ግብፆች በራሳችን የከበረ ውኃ ያመረቱትን ብርካቱን ሲሸጡልን እንደማየት ከባድ ነገር የለም፡፡ በብዙ እጅ ከግብፅ የተሻለ መልከዓ ምድርና የምርት ግብዓት ያላት ኢትዮጵያ ከራሷ ውኃ የተመረተ የግብፅ ብርቱካን ልጣ እየበላች ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እዚህ ብርቱካን የሚያመርት ጎበዝ አጥታ የግብፅን ብርቱካን አራቱን በ125 ብር እንድንገዛና የትርፍ ትርፍ የሚለቅም ነጋዴ እንዲበራከት ያደረገውን ያልተገባ አሠራር ማረም ይገባል፡፡

የግብይት ባህላችን ችግር አለበት የምንለውም ተፈጥሮ የቸረው መልክዓ ምድር እያለን ከውጭ ማስመጣት እንጂ ማምረትን ያለመምረጣችን ነው፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች