Monday, July 22, 2024

የችግሩን ምንጭ ዘንግቶ ለማያባሩ ግጭቶችና ተደጋጋሚ ጥቃቶች የሚደረገው መፍትሔ ፍለጋ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዓርብ መጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ከ100 በላይ ሰዎች ደግሞ ለጉዳት ዳርጓል፡፡ በተጨማሪም በርካታ ቤቶች በእሳት ጋይተዋል፡፡ የጥቃቱ መነሻ በግለሰቦች መካከል ተፈጥሮ በዕርቅ የተፈታ ግጭት ተከትሎ እንደሆነ የተነገረ ቢሆንም፣ ይኼንን ጉዳይ መርሳት ያልፈለጉና ሊተውት ያልፈቀዱ ‹‹የኦነግ ሸኔ›› እና መሰሎቹ አባላት የፈጸሙት ጥቃት እንደሆነ በጊዜው ተጠቅሷል፡፡

ይሁንና ይኼ ግጭት ራሱን የቻለና የተነጠለ ክስተት ሳይሆን፣ በተደጋጋሚ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱና እየተከሰቱ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች፣ እንዲሁም በተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች ቅጥያ መሆኑ ብዙ የተነገረለት ነው፡፡ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰላማዊ ኑሮ እንዳይኖርና ዜጎች ከቦታ ቦታ እንደ ፍላጎታቸው የመንቀሳቀስ መብታቸውን እንዳያጣጥሙ እያደረጉ ያሉ ክስተቶች አካል መሆኑም ይነገራል፡፡

ከአጣዬ አስቀድሞ በከሚሴ፣ በከማሺና በመተከል ዞኖች፣ የጉሊሶን ጥቃት ጨምሮ የተለያዩ የምዕራብ ወለጋ ጥቃቶች፣ በደቡብ ክልል የጉራፈርዳ ጥቃቶች፣ የአማሮ ልዩ ወረዳ የታጠቁ አካላት ጥቃት፣ ወዘተ. ሰንሰለታማ ቅጥልጥሎሽ ያላቸው የሚመስሉና ተመሳሳይ ምክንያቶች የሚሰጧቸው ክስተቶች እንደሆኑም ይወሳል፡፡

ካሁን ቀደም በተለይ በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍ የነበረውና በኋላም መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚል መጠሪያ የሰጠው ቡድን በቅንጅት የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች እንደሆኑ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሕወሓት በአገር መከላከያ ሠራዊት ካምፖች ላይ ጥቃት መፈጸሙን በመጥቀስ ከተጀመረው ጦርነት ወዲህ ሕወሓት በመሸነፉ እነዚህ ግጭቶች ረግበዋል የሚሉ መግለጫዎች ሲሰጡ ከርመዋል፡፡ ይኼ ንግግር በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ሲስተጋባ ነበር፡፡

ሆኖም ግጭቶቹ እንደተባለው ባለመርገባቸው የዜጎች መፈናቀልና ሞት እንደቀጠለ ሲሆን፣ በርካቶች ነገ ደግሞ እንዴት እንሆን ይሆን? በሚል ሥጋት ውስጥ መኖር ጀምረዋል፡፡

የአማራ ክልል የአጣዬንና የኤፍራታና ግድም ወረዳዎች ግጭቶችን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል በአገራዊ ግዳጅ ላይ ተሰማርቶ ባለበትና ባልታሰበበት ጊዜ አርሶ አደር ሊይዛቸው በማይችሉ ከባድ መሣሪያዎች በመታገዝ ጥቃት የፈጸመው፣ የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ ኃይሎች ናቸው ሲል ኮንኗል፡፡

ኦነግ ሸኔ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወታደራዊ ክንፍ የነበረና የፖለቲካ ኃይሉ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ተስማምቶ ወደ አገር ሲመለስ፣ ከመከላከያ ወይም ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጋር ለመቀላቀል በተወሰነው መሠረት አሻፈረኝ ብሎ ጫካ የቀረው ቡድን በመንግሥት የተሰጠው መጠሪያ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የፖለቲካ ቡድን በዚህ ስም የሚጠራና የሚታወቅ ቡድን የለም በሚል ሲከራከር የቆየ ሲሆን፣ በጫካ ያለው ቡድን እስካሁን ድረስ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጦር ወይም በአፋን ኦሮሞ አጠራር ወራና ቢሊሱማ ኦሮሞ (Waraana Bilisummaa Oromoo-WBO) ሲል ራሱን ይጠራል፡፡

ያም ሆነ ይህ ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች ለሚደርሱ ጥቃቶችና ለሚፈጠሩ ግጭቶች በምክንያትነት መነሳቱ ባይቀርም፣ ይህንን ጉዳይ አይደለም ሲሉ የሚከራከሩ አልጠፉም፡፡ ለአብነትም ይኼንን መከራከሪያ በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ከሚደርሱ ጥቃቶች፣ ግድያዎችና መፈናቀሎች ማየት ይቻላል፡፡

ይኼ ጉዳይ ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ፓርላማ ተገኝተው ከአባላት ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በተገኙበት ወቅት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ነበር፡፡

የፓርላማው አባል የሆኑት አቶ ዘለዓለም ታረቀኝ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጥያቄ፣ ‹‹የተለያዩ የአገራችንን ሰላም የማይፈልጉ በተለይም በዋናነት በኦነግ ሸኔና በትሕነግ የተቀናጀ ሴራ ሰሞኑን በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ በተለይ በሰሜን ሸዋ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች በዋናነትም በአጣዬ፣ በማጀቴ፣ በሸዋሮቢትና አካባቢዎች በዜጎች ላይ የሕይወት መጥፋት፣ የመፈናቀልና የንብረት መውደም ዛሬም ድረስ ሬሳቸው እንዳይነሳ እስከማድረግ የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይኼም የሆነበት ምክንያት የክልላችን መንግሥት እንደ አገር ከመንግሥት ጎን ሆኖ ሕግ የማስከበሩን ሥራ እየተወጣ ባለበት፣ በተዘናጋ መንገድ ዜጎቻችን ለችግር የተዳረጉበት ሁኔታ አለ፡፡ ይኼ ችግር ብሔር ተኮር የሆነና በተለይ በአማራ ብሔር ላይ ተከታታይ የሆነ የሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀል፣ በአገሩ ላይ እንዳይኖር በተከታታይ ጉዳት እያደረሰበት ይገኛል፤›› ሲሉ በመተንተን፣ መንግሥት ጥቃቶቹ ከመድረሳቸው አስቀድሞ ለምን ማወቅና መከላከል አልቻለም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹የአማራ ሰቆቃዎችና መፈናቀል የሚቆሙት መቼ ነው?›› ሲሉም አስረግጠዋል፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ወ/ሮ አሚናት እድሪስ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል፣ ‹‹የሕዝብን ሰላም የሚያረጋግጥ ሥራ ዋነኛ የመንግሥት ተግባር እንደሆነ ቢቀመጥም፣ በተለያየ ጊዜ ሥልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ የሚጥሩ አካላት በአገራችን በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዳይሠራና መንግሥትን እንዲያማርር ለማድረግ የዜጎችን ሰላም አደጋ ላይ የሚጥል ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፤›› በማለት፣ ለአብነትም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮችን የወቀሱ ሲሆን፣ በአፋር ክልልና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች የድንበር አካባቢ የይገባኛል ጥያቄዎች የታጀቡ ቢሆኑም፣ የሥልጣን ጥመኛ የሆኑ ሰዎች ለረዥም ዘመን ተዋዶና ተዋልዶ የኖረውን የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ በማጋጨት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትርፍ ለማግኘት የሚሸርቡት ሴራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በእነዚህ ችግር ፈጣሪዎች ምክንያት የኅብረተሰቡ ሕይወት በየቀኑ የሚረግፍበትና ከፍተኛ ንብረት የሚወድምበት፣ በአርሶ አደሩ መሬት ላይ የመንደር ማሰባሰብ የተሠራበትና በርካታ ነዋሪዎች የተሰደዱበት እንደሆነ በማሳወቅ፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ሕዝብ መኖር የለበትም በማለት ኦሮሞን ካላጠፋን ህልውናችን ያከትማል የሚሉ አካላት በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንን ለማጥፋት እየሠሩ እንደሚገኙ የምክር ቤቱ አባል ወ/ሮ አሚናት ተናግረዋል፡፡ በሕዝቡ ላይ ይኼንን ጥቃት የፈጸመው የአማራ ልዩ ኃይል ነው በማለት፣ ልዩ ኃይሉ ከዞኑ እንዲወጣና የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ መዋቅሩን እንዲመራ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹አማራ ሲሞት ንፁህ፣ ኦሮሞ ሲሞት ኦነግ መባል የለበትም፤›› ሲሉም  ተናግረዋል፡፡

ይህንን የፓርላማ ውሎ የታዘቡ ሰዎች ይኼ የአደባባይ አተካሮ በኦሮሚያና በአማራ የብልፅግና ፓርቲዎች መካከል ያለውን መሳሳብ ወደ ሕዝብ ዓይን ያወጣ ክስተት እንደሆነ የሚያመላክቱ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ወደ መፍትሔ መቅረብ እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሕዝቦች በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ የመወሰን እኩል ዕድል እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ፍጭት ነው በማለት፣ ለአገሪቱ ዕጣ ፈንታ አደጋ የሚደቅን ችግር እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡

እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦችን በሚያጠናክር ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ለፓርላማው በሰጡት ምላሽ፣ የሚከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች ሞትን፣ ማፈናቀልንና ንብረት ማውደምን አስከትለው ለመኖርና ለመሥራት የማይመች ድባብን እንደሚፈጥሩ በማስመር፣ ሰከን ብሎ በማሰብ ለጠላት ሲሳይ ከመሆን ራስን መታደግ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ኦሮሞና አማራን ለማባላት ገንዘብና ጊዜ ሰውተው የሚሠሩ ኃይሎች እንዳሉ እያወቃችሁ በተቀደደ ቦይ ውስጥ የምትገቡ ፖለቲከኞች፣ አመራሮችና ሰዎች ትገርሙኛላችሁ፡፡ ስትፈልጉ በራሳችሁ ጊዜ ብትጣሉ ባልከፋ፡፡ እነሱን ካላባላን በዚህ አገር የምንፈልገውን ነገር አናሳካም ለሚሉ ኃይሎች ዕድል መስጠት ጥሩ አይደለም፡፡ እና ማስተዋል ጥሩ ነው፡፡ ኦሮሞም ይሙት፣ አማራም ይሙት፣ ጉራጌም ይሙት ጉዳቱ ለኢትዮጵያ ነው፡፡ በዚያ መንፈስ እያሰብን የዜጎቻችን መጎዳት፣ መደፈርና መገረፍ እኩል የሚያሳዝነን ካልሆነ የጋራ አገር ልንገነባ አንችልም፡፡ ይኼ ፖለቲካዊ አመራርን ይጨምራል፡፡ እባካችሁ ሰከን ብላችሁ ይኼ አገር የ80 ብሔር ብሔረሰቦች አገር እንደሆነ፣ ሁሉም በእኩል ከኖረ ብቻ ኢትዮጵያ እንደምታድግ እንደዚያ ብናስብ ጥሩ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና ምን እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ቢሉም በፓርቲያቸው ውስጥ ያለው ሽኩቻ እንዲህ ያለ ክፍተት እየፈጠረ እንደሚገኝ አስተያየት ሰጪዎች ቢናገሩም፣ መፍትሔው በቅርብ የማይታይና የአገር ህልውና ሥጋት የሆነ አገራዊ አደጋ እንደተደቀነ የተደበቀ አይደለም የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በተረፈም ብሔራዊ አንድነትንና የጋራ ኢትዮጵያን መሠረት ያደረገ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር አገራዊ ርዕይ ላይ ጥላሸት ማጥላቱ አይቀርም ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -