Monday, March 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በአገርና በሕዝብ ህልውና ላይ መቀለድ ይብቃ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከተቋማት ግንባታ ይልቅ ለተክለ ሰብዕና ግንባታ የሚደረገው ትኩረት ከፍተኛ በመሆኑ፣ ለውዳሴም ሆነ ለውግዘት ስማቸው የሚነሳው ግለሰቦች ብቻ ናቸው፡፡ የአገርና የሕዝብ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ተወዝፈው የግለሰቦች ጉዳይ አየሩን ይቆጣጠረዋል፡፡ ከድህነት ውስጥ ለመውጣት መላ ከመምታት ይልቅ፣ የግለሰቦች ውሎና አዳር ለዜና ርዕስነት ተመራጭ ነው፡፡ ቢታረስ መላ አፍሪካን ሊመግብ የሚችል ሰፊ ለም መሬት ፆሙን እያደረ፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው የውኃ ሀብት በከንቱ እየባከነ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለሥራ የደረሱ ወጣቶች ሥራ አጥ ሆነው፣ ምድሪቱ የታቀፈችው ህልቆ መሳፍርት የሌለው የማዕድን ሀብት አፈር ውስጥ ተኝቶ፣ በአፍሪካ ቀርቶ በዓለም ሳይቀር ከፍተኛ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ የቱሪስት መስህቦች ሥራ ፈተው ዛሬም በልቶ ማደር ብርቅ ነው፡፡ ፅዱና ንፁህ የመኖሪያ ቤት ማግኘት ቅዠት ነው፡፡ ሀብት ላይ ተንፈራጠን ቆመን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወገኖቻችን አሁንም የዕለት ደራሽ አስቸኳይ ዕርዳታ ይለመንላቸዋል፡፡ በሥራ አገርን መለወጥ እየተቻለ በከንቱ ጥላቻ በመተናነቅ ተመፅዋች መሆንን የመሰለ ከንቱነት የለም፡፡ የትምህርት ጥቅሙ ሁለገብ ዕውቀት ገብይቶ ተፈጥሮን ለራስ በሚመች መንገድ መግራት ሆኖ ሳለ፣ዚህ በተቃራኒ በዘርና በሃይማኖት በመቧደን በየዕለቱ ችግር መቀፍቀፍ ልማድ ሆኗል፡፡ ተቋማትን በመገንባትና ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎች በማውጣት በሥርዓት መኖር እየተቻለ፣ ለሕገወጥነት መስፋፋት መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችን ችላ ማለት አገር እያጠፋ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና አስተማማኝ የሚሆነው ብሔራዊ ጥቅሟና ደኅንነቷ ሲከበር ነው፡፡ ይሁንና ከዚህ እውነታ በተቃራኒ በርካታ ጉዳቶች እያጋጠሙ ነው፡፡ በሕዝብና በአገር ህልውና ላይ መቀለድ ልማድ ሆኗል፡፡

በጠንካራ የሕግ ማዕቀፎችና በአስተማማኝ ተቋማት የማይመራ አገር፣ እንኳን ሊያድግ ቀርቶ በነበረበት መቆም ይቸግረዋል፡፡ አገርም እንደ ሰው የተለያዩ ህዋሳት ሲኖሩት፣ እነዚህ ህዋሳት በአግባቡ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ጤናማ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አገር መንግሥት የሚባል የገዘፈ አካል ሲኖረው፣ የተለያዩ ተቋማትም ይኖሩታል፡፡ እነዚህ ተቋማት ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ በሚባሉ ሦስት ዋነኛ ህዋሳት እየተመሩ ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ እነዚህ ሦስት ህዋሳት በሚገባ እየተናበቡና አንዱ ሌላውን እየተቆጣጠሩ ሲሠሩ አገረ መንግሥቱ ጤናማ ይሆናል፡፡ ሕግ አውጪው ጥራት ያላቸው ሕጎችን እያወጣ፣ ሕግ ተርጓሚው ሕጎች መከበራቸውን እያረጋገጠ፣ አስፈጻሚው ደግሞ በሥርዓት ሥራውን እያከናወነ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ አገር ሰላም ትሆናለች፡፡ ዜጎች በተረጋጋ ሁኔታ የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት ያጣችው ይህንን የመሰለ የሰከነ አሠራርና አመራር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በድህነት፣ በጉስቁልና፣ በኋላቀርነትና ለመግለጽ በሚያስቸግር ተስፋ ቢስነት ዘመናት ነጉደዋል፡፡ ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው ቢሰበክም ከንድፈ ሐሳብ የዘለለ ተግባር አልነበረም፣ አሁንም የለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ጋር ተናንቀው የአገራቸውን ነፃነት ቢያስከብሩም፣ የእነሱ ነፃነት ግን በጨቋኞችና በአምባገነኖች ተገፎ ለዘመናት መሰቃየታቸው የታወቀ ነው፡፡ ለማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን የተለያዩ ዓይነት ትግሎች ቢደረጉም፣ ተስፋን ከማለምለም ይልቅ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች በመብዛታቸው ከባድ መከራዎች አጋጥመዋል፡፡ በአገርና በሕዝብ ላይ እየተቀለደ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ከመቼውም ጊዜ በላይ የውጭ ተፅዕኖ ተጋርጦባታል፡፡ ከሁለት ወራት በኋላ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ሊጋብዝ የሚችል ምርጫ ታካሂዳለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚ እየተቀዛቀዘ በመሆኑ ግንባር ቀደም ተጠቂ ልትሆን ትችላለች፡፡ በውጭ ዕርዳታና ብድር ላይ የተንጠላጠለው ኢኮኖሚ በበቂ መጠን ሥራ መፍጠር ካልቻለ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ዕጣ ፈንታ ያሳስባል፡፡ በአጠቃላይ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉልህ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ክስተቶች ቢያጋጥሙ በማለት በከፍተኛ ጥንቃቄ መራመድ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ከአጉል ብሽሽቅ፣ ትችትና ከማይመስል የፖለቲካ ነጥብ አስቆጣሪነት ወጥተው በመርህ ቢመሩ ይመረጣል፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር ገጽታውን ቀይሮ አደገኛ ምዕራፍ ውስጥ እንዳይገባ፣ ከችግሩ ውስጥ እንዴት መውጣት እንደሚቻል መፍትሔ ማመላከት የተሻለ አቅም ይገነባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ነገር ከሥልጣንና ከጥቅም የበላይነት ጋር ብቻ እየተቆራኘ የአገር ጉዳይ ሲዘነጋ፣ ለውጭ ተፅዕኖ በቀላሉ መንበርከክ ይከተላል፡፡ በአገርና በሕዝብ ላይ መቆመር አይገባም፡፡

ኢትዮጵያ በሰላምና በዕድገት ወደፊት መራመድ የምትችለው፣ ከራሳቸው በላይ ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ኢትዮጵያውያን ሲበዙ ነው፡፡ አሁን እንደሚታየው ግን የብዙኃኑ ድምፅ ታፎኖ አየሩን የተቆጣጠሩት፣ ከአገር በፊት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያስቀድሙ መሰሪዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የሚባለውን ስም ለመስማት ከሚቀፋቸው ጀምሮ፣ በኢትዮጵያዊነት ስም እስከሚቆምሩት ድረስ ፍላጎታቸው ዥንጉርጉር ነው፡፡ አገርንና ሕዝብን ማዕከል ማድረግ አይፈልጉም፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጣሪያ ሥር ተገድበው ከመፎካከር ይልቅ፣ ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎታቸውን አልፋና ኦሜጋ ማድረግ ይሻሉ፡፡ በሰላማዊ መንገድ መነጋገርና መደራደር ሲችሉ አንዱ ሌላውን ለማስገበር ይራኮታሉ፡፡ ጦሳቸው ለንፁኃን እየተረፈ በርካቶች ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡ ቤተ እምነቶች ድረስ በመዝለቅ የፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ለማድረግ ተግተው ከመሥራታቸውም በላይ፣ የአገር ሽማግሌዎችን ሳይቀር የጥፋት ተላላኪ ያደርጋሉ፡፡ የማኅበረሰቦችን የሥነ ምግባርና የሞራል እሴቶች በመናድ ሕገወጥነትን ያስፋፋሉ፡፡ የሕግ የበላይነትን በመዳፈር ንፁኃን ይገድላሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ያፈናቅላሉ፡፡ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ሴቶችን አስገድደው ይደፍራሉ፣ ያስደፍራሉ፡፡ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ዜጎችን በሰብዓዊ ጋሻነት ያግታሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች ኢትዮጵያን ከማጥፋት የዘለለ ሚና የላቸውም፡፡ በአገርና በሕዝብ ላይ መቀለድ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡

ኢትዮጵያ ከፊቷ ምርጫ እየጠበቃት ነው፡፡ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ መረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትገነባ የሚፈልግ ማንኛውም ወገን ሰላምን መንከባከብ አለበት፡፡ ኢትዮጵያን ‹‹ኖህ መርከብ›› ብንመስላት፣ የተለያዩ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች ያሉዋቸው ወገኖች ተሳፍረውባታል፡፡ የመርከቧን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት መርከቧ ውስጥ የተሳፈሩ ሰዎች በሙሉ መሆን አለበት፡፡ መርከቧ ውስጥ ተሁኖ በገጀራ መፈላለግ ወይም በጠመንጃ መታኮስ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም መርከቧ እንድትሰምጥ በማድረግ ተያይዞ መጥፋት ይከተላልና፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚቻለው የመርከቧን ደኅንነት በመጠበቅ፣ ጤናማ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል መደላድል በመፍጠር ብቻ ነው፡፡ የመናገርና ሐሳብን በማንኛውም መንገድ የመግለጽ ነፃነትን አሽሞኑሙኖ የሚሰጠው ዴሞክራሲ ነው፡፡ ዴሞክራሲን የመጠበቅ ኃላፊነትም የሁሉም ነው፡፡ ሚዲያውም ሆነ ሌሎች አካላት ዴሞክራሲን መጠበቅ ካልቻሉ ባይኖሩ ይመረጣል፡፡ በየሥርቻው መሽገው ውጥረት የሚፈጥሩም ሆነ ግጭት የሚቀሰቅሱ፣ ለአገርና ለሕዝብ ህልውና ጀርባቸውን የሰጡ ናቸው፡፡ 

ለምርጫ እንፎካከራለን የምትሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፈቃደኛ ከሆናችሁ፣ ግጭት የሚጠነስሱትንና የሚያስፈጽሙትን በጋራ ስትታገሉ አሳዩ፡፡ ምርጫው በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ሒደት እንዲታጀብ ቁርጠኛ ከሆናችሁ፣ ፉክክራችሁ በሠለጠነ መንገድ እንዲከናወን ዕገዛ አድርጉ፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ሆናችሁ የጦር መሣሪያ ፍልሚያን በድብቅ አትቀስቅሱ፡፡ ለሕዝብ ይጠቅመዋል የምትሉትን ፖሊሲ በግልጽ ይዛችሁ ቀርባችሁ ለመወዳደር ተዘጋጁ እንጂ፣ በስም አጥፊነትና በጠላትነት ስሜት ውስጥ ሆናችሁ አታሲሩ፡፡ የሕዝብን የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤትነት የምታምኑና በተግባር የምታረጋግጡ መሆናችሁን ሕዝብ በማክበር አረጋግጡ፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዳችሁ የሕዝብን ልጆች በብሔርና በሃይማኖት እየከፋፈላችሁ አታጋድሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከችጋርና ከመከራ ውስጥ እንዴት መውጣት እንደሚችል ፍኖተ ካርታችሁን አቅርቡ፡፡ ኢትዮጵያ ከልመና ለመውጣት እንዴት የተፈጥሮ ሀብቶቿን እንደምትጠቀምና ባለፀጋ እንደምትሆን አመላክቱ፡፡ የዘመናት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዴት መወገድ እንደሚችሉ መፍትሔ ጠቁሙ፡፡ ሌላው በሠራው ላይ አቃቂር ከማውጣት እንዴት አስበልጦ መሥራት እንደሚቻል አሳምኑ፡፡ ደሃ አገር ጀርባ ላይ በአንቀልባ ታዝላችሁ ሥልጣን በአቋራጭ እንዴት እንደሚገኝ ከማለም፣ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዕውን መሆን ታገሉ፡፡ በተለይ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ተሰግስጋችሁ አገር ለማፍረስ የምታደቡ አደብ ግዙ፡፡ በአገርና በሕዝብ ህልውና ላይ መቀለድ አቁሙ፡፡

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...