ኢትዮጵያ በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆኗን አረጋገጠች፡፡
በምድብ 11 ከአይቮሪኮስት፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ማክሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ከአይቮሪኮስት ጋር በአቢጃን አድርጋ ውጤት ባይቀናትም፣ ተፎካካሪዋ ማዳጋስካር ከኒጀር ጋር አቻ በመውጣቷ አስቀድማ በሰበሰበችው ዘጠኝ ነጥብ ለአኅጉራዊው ውድድር ከስምንት ዓመታት በኋላ ለመብቃት ችላለች፡፡
በትናንትናው ጨዋታዋ በአይቮሪኮስት 3 ለ1 እየተመራች 80ኛው ደቂቃ ላይ ጋናዊው ዳኛ በሕመም ምክንያት በመውደቃቸው ጨዋታው ተቋርጧል፡፡ ጨዋታውን አይቮሪኮስታዊው አራተኛ ዳኛ እንዲዳኙ የቀረበውን ጥያቄ ኢትዮጵያ ባለመቀበሏ ሳይቀጥል ቀርቷል፡፡ የታመሙት ዳኛ ቻርልስ ቡሉ ወደ ሆስፒታል ከመወሰዳቸው በፊት፣ በብሔራዊ ስታዲየሙ የጤና ማዕከል ሕክምና ማግኘታቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዝሆኖቹ ዊሊ ቦሊ ባስቆጠራት ቀዳሚ ጎልና ፍራንክ ኬሲ በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ግብ ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ ጌታነህ ከበደ ብቸኛዋን ግብ 74ኛው ደቂቃ ላይ ካስቆጠረ በኋላ፣ አይቮሪኮስት ሦስተኛውን ግብ በዢያን ኩሲ አማካይነት ወዲያው አስቆጥራለች፡፡
ዋሊያዎቹ ከዝሆኖቹ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በቋሚ አሠላለፍ የተሠለፉት ተክለ ማርያም ሻንቆ፣ አስራት ቱንጆ፣ ያሬድ ባዬህ፣ አስቻለው ታመነ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ሽመልስ በቀለ፣ አማኑኤል ገብረ ሚካኤል፣ አቡበከር ናስርና ጌታነህ ከበደ ናቸው፡፡
ሃቻምና በአፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ላይ ደርሳ የነበረችው ማዳጋስካር ከኒጀር ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይታለች፡፡
የተቋረጠውን ጨዋታ አስመልክቶ ካፍ የሚያሳልፈው ውሳኔ ይጠበቃል፡፡ በመጪው ዓመት በ24 ቡድኖች መካከል በካሜሩን አምስት ከተሞች ለሚካሄደው 33ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ከሚሳተፉት 24 ቡድኖች ኢትዮጵያን ጨምሮ 21 ቡድኖች ማለፋቸው ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት ቆይታ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ የተገኘችው ደቡብ አፍሪካ በ2005 ዓ.ም. ባዘጋጀችው ውድድር ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡