Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አዲስ የተጣለው የኮቮድ-19 ገደብ ለምርጫ ዝግጅታችን ሥጋት ጥሎብናል አሉ

የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አዲስ የተጣለው የኮቮድ-19 ገደብ ለምርጫ ዝግጅታችን ሥጋት ጥሎብናል አሉ

ቀን:

ከሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ ተግራዊ እንዲሆን የተደነገገው፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን መመርያ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ዝግጅት በእጅጉ እንደሚያውክ የተለያዩ ፓርቲዎች ተወካዮች ገለጹ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን ቅዳሜ መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ መመርያውን ተግባራዊ አድርገው ባልተገኙ አካላት ላይ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ሌሎች ቅጣቶችን እንደሚያስቀጣ አስታውቀዋል፡፡

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚገናኘውና በዋነኝነትም የምርጫ ሥራን እንደሚያውክባቸውና ሥራቸውን እንደሚያስተጓጉል የተጠቀሰው መመርያ፣ ስብሰባን በተመለከተ ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 50 ሰዎች ብቻ እንዲሆኑ የሚወስን ነው፡፡

ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ሪፖርተር በምርጫ እንቅስቃሴቸው ላይ ‹‹ምን ዓይነት ተፅዕኖ ይፈጥራል?›› በማለት ጥያቄ ያቀረበላቸው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ፣ ‹‹ምንም እንኳን እንደ አገር የበሽታው ሥርጭት አሳሳቢ ቢሆንም፣ መመርያው መውጣት የነበረበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት ወስደው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማረጋገጥ የምርጫ ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ ተብሎ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

አቶ በለጠ አክለውም፣ ‹‹በኢትዮጵያ የአኗኗር ዘይቤ 50 ሰዎች የሚለው ጉዳይ አይደለም በምርጫ ወቅት፣ ማኅበራዊ ሕይወታችንም ላይ ትልቅ የሆነ ተፅዕኖ የሚፈጠር ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ሊቀመንበሩ የወጣው መመርያ በተለይም በምርጫ አስፈላጊና ወሳኝ የሆኑ እንደ ቁሳቁስ፣ ሥልጠናና ውይይት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና እንደሚፈጥርባቸው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ከ50 ሰዎች በላይ ተብሎ መመርያ መውጣቱ፣ እንዲያውም ‹‹ከ50 ሰዎች በላይ ተገኝተዋልና ጥፋተኛ ናቸው›› በሚል ሰበብ ፕሮግራም እንዲስተጓጎል ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የብሔራዊ ጤና ኮሚቴ አስተባባሪ ሙሉዓለም ተገኘወርቅ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አሁን ከወጣው ከ50 ሰዎች በላይ ይልቅ የአዳራሾችን አቅም 50 በመቶ ተብሎ ቢወጣ የተሻለ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ኢዜማ ቅስቀሳ እንዳልጨረሰና ለቀጣዩ ቅስቀሳ የኮቪድ-19 መመርያን መሠረት በማድረግ እየሠራ ቢሆንም፣ ከ50 ሰዎች በላይ ተብሎ መከልከሉ ግን ውስብሰብ ችግር ያለው ነው ብለዋል፡፡

ሙሉ ዓለም (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ ኢዜማ ከምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ አክለው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ገደቡ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ ‹‹አይደለም የምርጫ ቅስቀሳ ዕጩዎችን በአንድ ላይ አሰባስቦ ለማወያየትም አዳጋች ይሆንብናል፤››  ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሰይፈ ሥላሴ አያሌው (ዶ/ር) የኢዜማን ዓይነት ሥጋት እንዳላቸው ገልጸው፣ በተለይ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግና ከአባላት ጋር መወያየት ቀርቶ፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በአንድ ላይ አሰባስቦ ለመነጋገርም አስቸጋሪ እንደሚሆን ያስረዳሉ፡፡

የበሽታው ሁኔታ አስከፊነቱ ቢታወቅም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ለምርጫ ቅስቀሳ፣ ለውይይትና በሌሎች መሰል ጉዳዮች 50 ሰዎች በየፈረቃ ሰብስቦ ወደ ምርጫ ለመሄድ እንኳን የጊዜና የገንዘብ ውስንነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

እናት ፓርቲ በጉዳዩ ላይ በሥራ አስፈጻሚው ደረጃ እንደሚነጋገርና በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለበት እንደሚወስን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ወረርሽኙ ያመጣውና ያንዣበበውን አደጋ እንደሚያሳስባቸው አክለው ተናግረዋል፡፡

የኅብር ኢትዮጵያ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)፣  በኮቪድ-19 ምክንያት ከ50 ሰዎች በላይ እንዳይሰበስቡ መመርያ መውጣቱን በተመለከተ፣ ብልፅግና ፓርቲ ደግፉኝ እያለ ሕዝቡን ለሠልፍ እያስወጣ በሽታውን በከፍተኛ ሁኔታ ካስፋፋ በኋላ፣ አሁን አዲስ ገደብ ማውጣት መንግሥት በደመነፍስ እንደሚንቀሳቀስ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ብልፅግና በአደባባይ ለመንግሥት ድጋፍ በሚል ሲያስወጣና የበሽታውን መስፋፋት ከግምት ሳያስገባ ወረርሽኙ የአገር ዕዳ ከሆነ በኋላ፣ እንደገና ገደብ ማውጣት እሱ ቅስቀሳውን ከሠራ በኋላ አሁን ፓርቲዎች ቅስቀሳ የለም ብለው ከምርጫው እንዲያፈገፍጉ ይመስላል ሲል ተናግሯል፡፡

ሪፖርተር ለብልፅግና ፓርቲ አዲሱ መመርያ በምርጫ እንቅስቃሴያቸው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጫና አስመልክቶና መሰል ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ቢሞክርም፣ የፓርቲው ተወካዮች ስለ ክልከላውና ገደቡ በቂ ውይይት ስላልተደረገበት ለመናገር እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የምርጫ እንቅስቃሴውንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ዝግጅት አስመልክቶ የተጣለው ከ50 ሰዎች በላይ ያለመሰብሰብ ገደብ ሊያመጣ የሚችለውንና ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት ይንቀሳቀሱ? የሚለውን ጉዳይ ለማጣራት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ቀርቦ፣ የምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ዮሴፍ መርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር ፈጠረብን ብለው እስካልመጡ ድረስ ቦርዱ የሚለው ጉዳይ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመቀነስ የወጣው መመርያ ቁጥር 9/2013 ከ50 ሰዎች በላይ የሚሳተፉባቸው ስብሰባዎችና ቅስቀሳዎች፣ የመራጮች ትምህርት፣ ሥልጠናዎችንና የምርጫ ቅስቀሳ እንቅስቃሴዎችን የሚያዘጋጁ አካላት ቢያንስ 48 ሰዓት አስቀድመው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና መሥሪያ ቤት ወይም አግባብነት ላለው የክልል የምርጫ ጽሕፈት ቤት ማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...