Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ የልማት ዕቅድ ፕሮጀክቶች ሳይጠኑ በጀት የሚፈቀድበትን አሠራር እንደሚያስቀር ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ፣ ከዚህ በፊት ፕሮጀክቶች በደንብ ሳይጠኑ በጀት የሚፈቀድበትን አሠራር የሚያስቀር እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የፕላንና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የፀደቀው የልማት ዕቅድ ከዚህ በፊት ከቀረቡት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች በተለየ መንገድ የክትትልና የግምገማ ሒደቶች አሉት፡፡ ስለዚህም የትኞቹም የልማት ፕሮጀክቶች ከልማት ዕቅዱ ጋር በመናበብ ስለዚህም የጠቀሜታቸውና የአዋጭነታቸው ጥናታቸው ከተከናወነ በኋላ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ይመራሉ ብለዋል፡፡

የልማት ዕቅዱ ግምገማ በእያንዳንዱ የዕቅድ ዘመን መርሐ ግብር ለማሟላት ብቻ የሚደረግ እንደማይሆን ያስረዱት ነመራ (ዶ/ር)፣ የሚጠበቁና የማይጠበቁ ክስተቶችን እየለየ በሩብ፣ በግማሽና በሙሉ ዓመት የሚከለስና የሚገመገም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሚመለከታቸው በርካታ ባለድርሻዎችን አሳትፈው ዕቅዱን እንዲያዘጋጁ እንደሚደረግ ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ሆኖም በአተገባበሩ ወቅት የልማት ሥራዎቹ የሚከናወኑት በክልሎችና ከዚያም በታች እስከ ወረዳዎች ባለው መዋቅር በመሆኑ፣ ኮሚሽኑ በእነዚህ አካባቢዎች የልማት እንቅስቃሴና ፕሮጀክቶችን የተመለከቱ ሥራዎችን ለማከናወን እንዳቀደ አስታውቀዋል፡፡

ነመራ (ዶ/ር) እንዳስረዱት፣ የፀደቀው ዕቅድ የአሥር ዓመት እንደ መሆኑ መጠን በመሀል ላይ የሚከሰቱ በርካታ ተፅዕኖዎች ይኖራሉ፡፡ ስለሆነም እነዚህን ተፅዕኖዎች በደንብ ገምግሞ ዕቅዱን እየከለሱ መሄድ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ዕቅዱን የሚያስተገብሩ ተቋማት መጠናከር ያለባቸው በፌዴራል ደረጃ ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በክልልና በወረዳዎች ያሉትን ተቋማት በማጠናከርና የዕቅዱን ተፈጻሚነት ግምገማ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ውይይት እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

‹‹ልማት የፖለቲካ ሥራ አይደለም፤›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ይህም የአሥር ዓመት ዕቅድ አገራዊ መሆኑን፣ የአንድ ፓርቲ ዕቅድ እንዳልሆነ፣ ተቋማትን በማጠናከርና  በተከታታይ በሚሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ማረጋገጥ እንደሚገባ አክለዋል፡፡

በልማት ዕቅዱ ዝግጅት ወቅት የልማት አጋሮች ድጋፍ ትልቅ እንደነበረ ያስታወሱት ነመራ (ዶ/ር)፣ በቀጣይም ዕቅዱን ለማስፈጸም ከአጋሮቹ ጋር የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ ሰነዱ ላይ እንደተገለጸው፣ የልማት ዕቅዱ የክትትል ሥርዓት በዋናነት ሁለት የመረጃ ምንጮችን ይጠቀማል፡፡ እነዚህም በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሚመነጩ የናሙና ጥናትና የቆጠራ መረጃዎች፣ እንዲሁም በዘርፍ አስፈጻሚ ተቋማት የሚመነጩ የአስተዳደር መረጃዎች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች