Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትየብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችን ለተቃውሞ የጋበዘው ምክንያት ምንድነው?

  የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችን ለተቃውሞ የጋበዘው ምክንያት ምንድነው?

  ቀን:

  በጃፓን ቶኪዮ ከተማ ሊከናወን ወራት የቀሩት የዘንድሮ ኦሊምፒክ ጨዋታ በርካታ ውዝግቦችን እንዳስተናገደ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

  በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መደረግ አለመደረጉ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻም እንዲደረግ ከተወሰነ በኋላ ጃፓን ሽር ጉድ ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ ከሐምሌ 16 እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚከናወነው የኦሊምፒክ ጨዋታ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ በብስክሌትና በቴኳንዶ ተወክላለች፡፡

  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በተለያዩ ርቀቶች ላይ ለሚሳተፉ አትሌቶችና ኢትዮጵያውያን አሠልጣኞች ጥሪ አድርጎ ዝግጅት ከተጀመረ አራት ወራት አልፏል፡፡

  ለስምንት ወራት ዝግጅት ያደርጋሉ ተብሎ ማረፊያቸውን በሦስት ሆቴሎች በማድረግ ዝግጅታቸውን ማድረግ ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ የብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን አትሌቶች፣ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ኦሊምፒክ ኮሚቴ በገቡት እሰጣ ገባ ምክንያት የዝግጅት ሒደታቸው ላይ እክል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ስለተፈጠረው አለመግባባት መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ጉዳይ ከአቅሜ በላይ ሆኗል ብሏል፡፡

  መግለጫውን ተከትሎ እየተካረረ የመጣው የሁለቱ ተቋማት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡ የኮማንድር ደራርቱ ቱሉን የዕውቅና መርሐ ግብርና በሐዋሳ ሊደረግ የነበረው ጠቅላላ ጉባዔ በተመሳሳይ ቀን መዋሉ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡

   ከትናንት በስቲያ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ከሆቴላቸው ወጥተው ወሎ ሠፈር በሚገኘው የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት የተቃውሞ ሠልፍ አድርገዋል፡፡  ሠልፉን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉም ተቀላቅላው ነበር፡፡

  በወቅቱም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተወሰኑ የጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊዎችን በማሳተፍ በጽሕፈት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔውን አከናውኖ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን ለአራት ዓመታት የሚመሩ አመራሮችን መምረጡን ይፋ አድርጓል፡፡

  የውዝግቡ መነሻ

  ተቋማቱ የራሳቸውን አቋም፣ በጋዜጣው መግለጫ ከመግለጽ በስተቀር አጥጋቢ ምላሽ ባይሰጡም፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ሊያደርገው ያሰበው ጠቅላላ ጉባዔና የኦሊምፒክ ቡድኑን በአግባቡ እያስተናገደ አይደለም የሚሉት ክሶች ሲቀርቡበት ተስተውሏል፡፡

  አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አንደኛው ጉዳይ ብሎ የሚያነሳው ታኅሣሥ 25 ቀን 2013 ዓ.ም በሐዋሳ በተካሄደው 45ኛው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ጠቅላላ ጉባዔ ስለቀጣዩ ጠቅላላ ጉባዔ ሐሳብ የተሰጠበት ሲሆን፣ ምርጫው ከቶኪዮ ኦሊምፒክ 2020 በኋላ እንዲሆንና ያለው ሥራ አስፈጻሚ እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም. ድረስ እንዲቀጥል በሙሉ ድምፅ መወሰኑን ያትታል፡፡

  ይኼን ውሳኔ ተከትሎም የኦሮሚያ ክልል ስፖርት ኮሚሽን፣ ቦክስ ፌዴሬሽን፣ ውኃ ዋና፣ ቴኒስ፣ ባድሜንተን፣ ጂምናስቲክ፣ የጎልፍ፣ቼዝና የዳርት ፌዴሬሽኖች በጋራ መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያደረገውን ምርጫ በመቃወም በማግስቱ መጋቢት 21 ቀን ለዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ደብዳቤ ማስገባታቸውን አስታውቀዋል፡፡

  ከዚህ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአትሌቶች ማኅበር ጋር በጋራ በመሆን ሰባት የአቋም መግለጫ ሲያወጣ፣ የአትሌቶች ማኅበሩ ደግሞ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያከናወነው ምርጫ ሕገወጥ ነው ሲል በጋዜጣዊ መግለጫው አብራርቷል፡፡

  ከዚህ ቀደም ዘጠኝ የስፖርት ፌዴሬሽኖች የኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ መደረግ የለበትም የሚል የቅሬታ ደብዳቤ ለዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ማስገባታቸው ቢገለጽም፣ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ እንደሚችል የሚገልጽ ከዓለም አቀፍ ኮሚቴው ደብዳቤ ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡

  ምርጫው ከተከናወነ በኋላ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ደ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስና በጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኙ አመራሮች በፖሊስ መወሰዳቸውና ወዲያውኑ መመለሳቸው ተደምጧል፡፡

  በተቃውሞ ላይ የተገኙ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ምን ይላሉ?

  በሁለቱ ተቋማት አመራሮች እንካ ሰላንቲያ የተሞላው ውዝግቡ፣ የጉዳዩ ዋና ተዋንያን የሆኑትን አትሌቶችና አሠልጣኞች ፍላጎት እንዲሁም እያደረጉት ስላለው ዝግጅት ከግምት ውስጥ ያስገባ አካል ያለመኖሩ ጉዳዩን አወሳስቦታል፡፡

  ከዚህም በላይ ለተፈጠረው ውዝግብ ሀይ ባይ መጥፋቱና በዚህ ምክንያት ስፖርቱ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ ማስገባት የቻለ አንድም አካል የለም የሚሉ አሉ፡፡

  ቆይታቸውን በሆቴል ካደረጉ አሠልጣኞች በርካቶች በሰኞ ዕለት ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

  የብሔራዊ ቡድን የመካከለኛ ርቀት አሠልጣኙ አቶ ብርሃኑ መኮንን በሰጠው አስተያየት አትሌቶች ሆቴል ገብተው ሥልጠና ማድረግ ከጀመሩ አራት ወራት እንዳለፋቸውና በእነዚህም ወራት ውስጥ ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ይናገራል፡፡ ‹‹ምንም ሳይከፈለን ለአራት ወራት ቆይተናል፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቃል ከመግባት ባሻገር ምንም ያደረግልን ነገር ባለመኖሩ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከራሱ ካዝና ነው የከፈለን፤›› በማለት አቶ ብርሃኑ ለሪፖርተር አስተያየቱን ይሰነዝራል፡፡

  እንደ ብርሃኑ አስተያየት ከሆነ የኦሊምፒክ ጨዋታው ተቃርቦ እያለ ለብሔራዊ ቡድኑ የሚያስፈልገውን ነገር ከማድረግ ባሻገር ቃል የተገባ ነገር እንኳ አለመተግበሩን ያስረዳል፡፡

  ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ድረስ ቅሬታቸውን ለማሰማት ሰላማዊ ሠልፍ የወጡበት ዋነኛ ምክንያት አቶ ብርሃኑ የገለጸው፣ ኮሚቴው ‹‹የማዳረስ ሥራ ከመሥራት ባሻገር አንዱንም የአሠልጣኝ ጥያቄ መመለስ አልቻለም፤›› በማለት ነው፡፡

  በተጨማሪም በተመሳሳይ ርቀት ላይ በአሠልጣኝነት እየሠራ ያለው አቶ ካሳሁን ስንታየሁ፣ ከተለያዩ ክለቦችና ክልሎች እንዲሁም ከተማ አስተዳደሮች ተመርጠው ቆይታቸውን በሆቴል ያደረጉ አትሌቶች መቀነሳቸው በግልጽ ሳይነገራቸው ከሆቴል እንዲወጡ መደረጋቸውን ገልጿል፡፡

  ‹‹ከቡድን ውስጥ እንዲቀነሱ የተደረጉት አትሌቶች ከሆቴል እንዲወጡ በመዳረጋቸው ለትራንስፖርት ችግር ተጋልጠዋል›› በማለት ስለነበረው ሒደት አቶ ስንታየሁ ለሪፖርተር ጠቅሷል፡፡

  የትራንስፖርት እጥረት፣ ክፍያ በአግባቡ አለመክፈል፣ በቂ የላብ መተኪያ አለመስጠትና በቂ አትሌቶች በቡድን ውስጥ ማካተት አለመቻሉ የአሠልጣኞች አንኳር ችግር መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡

  ይኼን በተመለከተም ኦሊምፒክ ኮሚቴው ያለው በጀት ከተቀመጠው ኮታ በላይ ማስተናገድ እንደማይቻል ማስረዳቱ ይታወሳል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...