Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበውዝግብ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ

በውዝግብ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ

ቀን:

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፖርቱ ዓለም የሚታየው እንቅስቃሴ የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ቢሆንም፣ የመንግሥትንና የፀጥታ አካላት ጣልቃ ገብነትም ያስከተለበት ጊዜ በርካታ ነው፡፡ በተለይ የአመራር ምርጫን የተመለከቱ ውዝግቦች ከስፖርታዊ አንድምታ የዘለለ መገለጫ ያላቸው ሲሆኑ፣ በመራጭ፣ አስመራጭና ተመራጭ ፍላጎቶች እንዲሁም በውጪ ባሉ ፍላጎቶች የሚዘወሩ ለመሆናቸው የተለያዩ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በቅርቡ የተደረገው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ያስከተለው ውዝግብ፣ እሰጣ ገባና ንትርክ ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ታኅሣሥ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐዋሳ ባካሄደው  ዓመታዊ ጉባዔ የአገልግሎት ጊዜው የተጠናቀቀው የሥራ አመራር ቦርድ እስከ ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ማግሥት ድረስ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን ለአራት ዓመታት የሚመራውን ሥራ አመራር ቦርድ ለማስመረጥና የምርጫውን ሒደት በሚመለከት የካቲት 19 ቀን2013 ዓ.ም. በቢሾፍቱ አዱላላ ሆቴል አስቸኳይ ጉባዔ ጠርቶ የምርጫ ማስፈጸሚያ መመርያ በማፅደቅ ሦስት አባላት ያለው የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰይሟል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አስመራጭ ኮሚቴው በበኩሉ ለኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አመራር ቦርድ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው የሚቀርቡ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች እንዲሁም ያለ መሥፈርት ለውድድር የሚቀርቡ ሁለት ኦሊምፒያኖች (አትሌቶች) ከኦሊምፒክ ስፖርት ውጪ ያሉ የስፖርት ተቋማትንና ክልሎችን ጨምሮ ማስረጃዎቻቸውን አጣርቶ በአጠቃላይ 21 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለምርጫ መቅረብ እንደሚችሉ ማጣራቱንና ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ የሚደረግበትን ቀንና ቦታ እንዲያሳውቅ መግለጹ ይታወቃል፡፡

ኦሊምፒክ ኮሚቴው በበኩሉ መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም በሐዋሳ ኃይሌ ሪዞርት ምርጫ እንደሚያደርግ፣ ለዚህም በዋዜማው የጉባዔ አባላትና መገናኛ ብዙኃን በሐዋሳ እንዲገኙ ጥሪ አድርጓል፡፡ ይሁንና ምርጫው በሚደረግበት ዕለት የታጠቁ የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይሎችና ፖሊሶች በሆቴሉ ተገኝተው ጉባዔው እንዳይካሄድ ከልክለዋል፡፡ በዕለቱ ቀድመው በስብሰባ አዳራሹ የተገኙ የጉባዔ አባላት ለደቂቃዎች ያህል በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርገው ተለቀዋል፡፡ “ጉባዔው በሐዋሳ እንደሚካሄድ የሲዳማ ክልል ቀድሞ እንዲያውቀው አልተደረገም” የሚል መከራከሪያ ሲቀርብ ተደምጧል፡፡ 

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ የደቡብ ክልል ፈቃድ ሰጥቶት እያለ ጉባዔው መከልከሉ ትክክል እንዳልሆነ ተናግሯል፡፡ ድርጊቱንም “አገርን ለዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቅጣት የሚያደርግ ነው” ብሎታል፡፡

በዕለቱ በሐዋሳ እንዳይካሄድ የተከለከለው ጉባዔ በማግሥቱ ሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የስብሰባ አዳራሽ ሊደረግ መሆኑ እንደተሰማ፣ በአካባቢው የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ደረሱ፡፡ የፌዴራልና የፖሊስ አባላቱ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ገባዔው ተጀምሮ ምርጫው ተደረገ፡፡

ይሁንና ምርጫው ከመደረጉ በፊት የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ ‹‹ለጉባዔው የምሰጠው አስተያየት አለኝ ብለው››፣ ‹‹በሐዋሳ የተደረገው ስህተት ነው፣ ቢሆን ይህ ጉባዔ ጉዳዩን በሆደ ሰፊነት ተመልክቶ ከምርጫው በፊት የጉባዔው አባላት ጊዜ ወስደን፣ ከየክልሎቻችን ኃላፊዎች ጋር መክረንበት ከሁለትና ሦስት ቀን በኋላ ቢደረግ›› ቢሉም፣ የጉባዔው አባላት ምልዓተ ጉባዔው እስከተሟላ ድረስ ምርጫው መደረግ እንዳለበት በአንድ ድምፅ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፡፡ ጉባዔው በአጠቃላይ 69 ድምፅ ሲኖረው በዕለቱ ምርጫ ድምፅ የሰጡ የጉባዔ አባላት ደግሞ 45 መሆናቸው አስመራጭ ኮሚቴው አሳውቋል፡፡              

በምርጫው ውጤት መሠረት ከኦሊምፒክ ስፖርት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ፕሬዚዳንት፣ ከኦሊምፒያኖች (አትሌቶች) ብርሃኔ አደሬ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ተነገረ፡፡

አቶ ዳዊት አስፋው ከኦሊምፒክ ስፖርት የኦሊምፒክ ኮሚቴው ዋና ጸሐፊ፣ ወ/ሮ ኤደን አሸናፊ ከኦሊምፒክ ስፖርት ዓቃቤ ነዋይ፣ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን ከኦሊምፒክ ስፖርት፣ ፍትሕ ወልደሰንበት (ዶ/ር) ከኦሊምፒክ ስፖርት፣ አቶ ጥላሁን ታደሰ ከኦሊምፒክ ስፖርት፣ አቶ ሲሳይ ዮሐንስ ከኦሊምፒክ ስፖርት፣ ኢትዮጵያ በዴቻ ከኦሊምፒክ ስፖርት፣ አቶ ምኒልክ ሀብቱ የኦሊምፒክ ስፖርቶች ካልሆኑ፣ አቶ ባዘዘው ጫኔና አቶ ናስር ሁሴን ከክልል የኦሊምፒክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ እንዲሁም ወ/ሮ ዓለም ገብሬ ከፓራሊምፒክ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ በነበሩበት እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡

የምርጫው ውጤት ከታወቀ በኋላ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገዛኸኝ አበራና የኦሮሚያ ስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ፍሥሐ ገብረሚካኤል የኦሊምፒክ ኮሚቴን ቅጥር ግቢ በር በመኪና ጥሰው በመግባታቸው፣ በግቢው ውስጥ አለመግባባትና ጩኸት ሲፈጠር በአካባቢው የነበሩ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊሶች ወደ ሥፍራው በመግባት ጉዳዩን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡

ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በግቢው ውስጥ ከነበረችውና በምርጫው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆና ከተመረጠችው አትሌት ብርሃኔ አደሬ ጋር ከቃላት ልውውጥ አልፈው ለድብድብ ሲጋበዙ ታይተዋል፡፡ ግርግሩ ቀጥሎ ሳለ በአንድ ኮስትር መኪና አሠልጣኞች፣ አንዳንድ የቀድሞ አትሌቶችና የፌዴሬሽን አመራሮች ‹‹ምርጫው ሕገወጥ ነው›› የሚሉ መፈክሮችን ይዘው በኦሊምፒክ ኮሚቴ ቅጥር ግቢ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል፡፡

በሥፍራው የነበሩ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ሁለቱ አካላት ማለትም ኮማንደር ደራርቱ ቱሉና አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ተቀራርበው እንዲነጋገሩ ጥረት ቢያደርጉም፣ ችግሩ መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በምርጫው የተሳተፉ የጉባዔ አባላትን ጨምሮ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች፣ በኦሊምፒክ ኮሚቴው የስብሰባ አዳራሽ እንዲቀመጡ ተደርጎ፣ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኃላፊዎች ደጋግመው ወደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት በመግባት ከፕሬዚዳንቱ ጋር ሲወያዩ ታይተዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን በቅጥር ግቢው ተቃውሟቸውን የቀጠሉት የቀድሞ አትሌቶች፣ አሠልጣኞች፣ የፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አመራሮችና ሌሎችም፣ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተካሄደው ምርጫ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ የሚመለከተው አካል በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡

አለመግባባቱ ቀጥሎ ሳለ ወደ አመሻሹ ላይ የተወሰኑ የፀጥታ አካላት ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ጋር ከሰዓታት በላይ ከተነጋገሩ በኋላ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርገው ተያይዘው ከቅጥር ግቢው ሲወጡ ታይተዋል፡፡

በጸጥታ አካላት ከተወሰዱት መካክል አሸብር(ዶ/ር)ን ሪፖርተር አነጋግሯቸው፣ በነበሩት ሁኔታዎች ላይ ከተነጋገሩ በኋላ ተግባብተው በሰላም መለያየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የነበሩ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በቅጥር ግቢው ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ሰዎች ተቃውሟቸውን አቁመው በመጡበት አግባብ እንዲመለሱ አድርገው፣ የጉባዔተኛውን ዝርዝር ከወሰዱ በኋላ ከቅጥር ግቢው እንዲወጡ አድርገዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በተለይ የፌዴሬሽኑ ጋዜጣዊ መግለጫ ይዘት ተጠቃሎ ሲታይ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የሚመሩበት መመርያ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ዋና ዋና የሕግ ምሰሶዎችን በመውሰድ በዋናነት በአገሪቱ መንግሥት በተወከለ የስፖርት ኮሚሽን በሚያወጣቸው የስፖርት ማኅበራት መመርያን የተከተለ መሆን ቢገባውም፣ ስፖርት ኮሚሽንም ሆነ መንግሥት እንደማያገባቸውና ዓለም አቀፍ መመርያንም የሚቃረኑ የሕግ አንቀጾችን በመጨመር፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴው ያካሄደው ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡   

የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር በተመሳሳይ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እየተካሄደ ያለው አትሌቲክሱን የሚጎዳ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስምና ክብር የሚቀንስ ነው ሲል የምርጫውን ሒደትና አካሄድ አውግዟል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ታኅሣሥ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐዋሳ ባካሄደው ጉባዔ፣ ምርጫው ከቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በኋላ እንዲሆን መወሰኑን ከገለጸ በኋላ፣ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም በኦሊምፒክ ኮሚቴው ቅጥር ግቢ በድንኳን ያካሄደው ምርጫ ሕገወጥ እንደሆነ ማኅበሩ በመግለጫው አካቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ፣ ከዓለም አቀፉም ሆነ ከአገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ደንብና መመርያ አንፃር ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የአሠራር ክፍተት አለ ብሎ የሚያምን ተቋም ካለ፣ ሕግና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ቃለ ጉባዔ በማስያዝና ክስ በማቅረብ መነጋገር ሲቻል፣ በአትሌቶች ስም መፈክሮችን በመያዝ የሚደረገው ሕገወጥ ተቃውሞና ግርግር ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ ለኢትዮጵያ አትሌቶች ክብር የሚመጥን አይደለም ሲል መግለጫውን አጣጥሎታል፡፡

ታኅሣሥ 25 በሐዋሳ በተደረገው ጉባኤ ምርጫን በሚመለከት የተነሳ ምንም ነገር እንዳልነበረ ያከለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ጉባዔው በወቅቱ አንስቶት የነበረው ጉዳይ የአገልግሎት ጊዜውን ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አመራር ቦርድ እስከ ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ማግሥት ድረስ የጀመራቸውን ሥራዎች ያስቀጥል የሚል ስለመሆኑ ጭምር ተናግሯል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...