‹‹አሁንም ልባችንን እንጂ እጃችንን ለሰላምታ አንዘርጋ››
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
በኢትዮጵያ በተለይም በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በኮቪድ-19 በሽታ የሚያዙት ሰዎችም ሆነ ሕይወታቸውን የሚያጡት ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ አገራዊው አኃዝ እንደሚያሳየው በቫይረሱ የተያዙት ከ200 ሺሕ በላይ አሻቅቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ በቴሌቪዥን የታዩና ሕክምናቸውን በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ውስጥ በሚገኘው የኮቪድ ሕክምና ማዕከል እየተከታተሉ የሚገኙ አንዲት እናት፣ ‹‹[ኮቪድ] ቀላል በሽታ አይደለም፣ ከባድ ነው፡፡ እባካችሁ ጥንቃቄ ውሰዱ ይገድላል፤›› ሲሉ ተሰምተዋል፣ ታይተዋል፡፡ በኦክሲጅን ታግዞ የሚተነፍስ አንድ ወጣትም፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ሊያዝ ይችላል፣ ስለዚህ መዘናጋት አያስፈልግም፤›› ሲል የተናገረው እያሳለ ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በአዲስ አበባ ግዙፉ የኮቪድ ሕክምና መስጫ በሆነው ሚሌኒየም ማዕከል የጽኑ ሕሙማን ቁጥርና ፍሰት በሦስት እጥፍ ጨምሯል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው ወቅታዊ መረጃ፣የኮቪድ-19 ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከታወቀ በአንድ ዓመት ውስጥ ለ2,340,575 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፣ 202,545ቱ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። እስካሁን 154,323 ከኮቪድ-19 ቫይረስ አገግመዋል።
መጋቢት 20 ብቻ 7,840 ግለሰቦች የኮቪድ-19 ምርመራ አድርገው 1,982ቱ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ናሙና ከሰጡ 100 ግለሰቦች 25ቱ (25%) ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ነው፡፡ 795 ግለሰቦች ደግሞ በፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ እየታከሙ ሲገኙ 24 ሰዎች በዕለቱ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ኮቪድ በኢትዮጵያ ባጠቃላይ ለ2,825 ግለሰቦች ሕይወት ኅልፈትና ለብዙዎች ደግሞ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ቀውሶችን ማስከተሉን ያስታወሰው ኢንስቲትዩቱ፣ ኅብረተሰቡ ከዚህም የከፋ ችግር እንዳይገጥመው ማስክን በአግባቡ በማድረግ የእጅን ንፅህና እንዲሁም ርቀትን በመጠበቅ ወገኑን እንዲታደግ ጥሪ አቅርቧል፡፡ አያይዞም ‹‹አሁንም ልባችንን እንጂ እጃችንን ለሰላምታ አንዘርጋ!›› ብሏል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማስጠንቀቂያ
የኮቪድ-19 ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል የወጣው መመርያ ቁጥር 30/2013 የተቀመጡ የክልከላ ዕርምጃዎች በማይተገብሩ አካላት ላይ እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲሁም ሌሎች ቅጣቶች እንደሚያስቀጣ ሰሞኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡
ከጤና ሚኒስቴር ጋር መግለጫ የሰጠው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ አሳሳቢ የሆነውንና በፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘውን የኮቪድ-19 ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያግዝ በቁጥር 30/2013 መመርያ ቢወጣም አተገባበሩ ላይ ግን ከፍተኛ ክፍተት ታይቷል ብሏል።
በመሆኑም በመመርያው የተቀመጡ የክልከላ ዕርምጃዎችን ተከታትሎ ማስተግበርና ማስፈፀም አስፈልጓል ያለው ተቋሙ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ተከታዩን ማስገንዘቢያ ከማስጠንቀቂያ ጋር ሰጥቷል፡፡
ማንኛውም የኮቪድ-19 ቫይረስ ያለበት ግለሰብ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ
- ቫይረሱ የተገኘበት ሰውም ወደ ማኅበረሰቡ እንዳይቀላቀል
- ማንኛውም ሰው በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) ሳያደርግ እንዳይንቀሳቀስ
- የንግድና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማስክ ያላደረገ ግለሰብን አገልግሎት እንዳይሰጡ
- ይህንን ጨምሮ ሌሎች የመመርያ 30/2013 ዝርዝር ደንቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
መመርያውን በማይተገብሩ አካላት ላይም እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲሁም ሌሎች ቅጣቶች እንደሚያስቀጣ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡
አራቱ የ‹‹መ›› ሕጎች
- መራራቅ፡ አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣
- መታጠብ፡ እጅን በተደጋጋሚ በውኃና በሳሙና መታጠብ፣
- መቆየት፡ አስገዳጅ ካልሆነ ቤት ውስጥ መቆየት፣
- መሸፈን፡ ከቤታችን ወጥተን ስንንቀሳቀስ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) መጠቀም፡፡