እነሆ ጉዞ ከኮተቤ ወደ መገናኛ። ምን እንደገጠማቸው ያልታወቀ ሁለት ሴቶች ፊት ለፊት ተላተሙ። ‹‹አንችዬ!ምነው ዓይንሽ ቢያይ?›› ብላ ግንባሯን እያሸች አንደኛዋ ቆመች። አንዱ ከአንዱ እያረፈደ ታክሲያችን ውስጥ የሚሞላው ተሳፋሪ ገሚሱ ሲስቅ ገሚሱ እንዳፈጠጠ ነው። ‹‹ምነው አንቺ ያላየሽኝ?›› አለች ሌላዋ ጥያቄን በጥያቄ መሆኑ ነው። ‹‹ይገርማል! የመኪና ግጭትና አደጋ ባሰለቸበት አገር እንዴት ሰውና ሰው ይጋጫል?›› ብሎ ወያላው ወደ ሥራው ተመለሰ። ‹‹አዬ! ምን ብርሃን ቢሆን ምን አገር ቢለማ የልቦና ዓይን ጨልሞ ሰው ማስተዋል ከተሳነው እኮ አበቃ!›› ይላሉ ነጠላ አዘቅዝቀው ከለቅሶ የሚመለሱ አዛውንት ሴት። ‹‹ጀመረ እንግዲህ ይኼ አሽሙር…›› ይላል መሀል ወንበር ላይ አብሮኝ የተቀመጠ ተሳፋሪ። የሰዎቹ ምልልስ እያዝናናኝ ዓይኔ በሚያየው ስገረም ጥቂት ደቂቃዎች አለፉ። ከትርምስምሱ መሀል ምሕረት የሞላባት የፀሐይ ብርሃን ፍንትው ብላ በርታለች። መንገዱ የጠበበውና የገዛ ጉዳዩ አዕምሮውን የወጠረው እንዲህ ላለው መገረም ጊዜ ያለው አይመስልም። ሐሳብ በዝቶ ነዋ!
‹‹ትቀልዳለህ ዘመኑ ‹የቻፓ› ነው…›› የሚል አባባል ድንገት ሐሳቤ መሀል ድንቅር አለ። ሦስተኛ ወንበር ላይ ከተቀመጡት ወጣቶች አንደኛው ነው። ‹‹ታዲያስ! ያለ እሱ ምን አለ ወንድሜ? ብታለቅስ አያምርብህ ብትስቅ ብቻህን፡፡ ከመኪና እስከ መኖሪያ ቤት ሁሉም የሚገኘው በገንዘብ ብቻ ነው፡፡ ቆነጃጅቱም ልባቸው ገንዘብ ላይ ነው…›› እያለ ፀጉሩን ያካል። ‹‹ሥነ ሥርዓት! ሴት በወለደች እህት በሆነች እንዲህ ተፈርጃ መጠራቷ ሚስጥሩ ምንድነው?›› ቱግ ያለች ቆንጆ ከኋላ ወንበር ጮኸችበት። ለመብቱ ተቆርቋሪና ለስሙ ተሟጋች እየበዛ ነው። ‹‹ኧረ ተረጋጊ እህቴ ጨዋታ ነው እኮ!›› ይመልስላታል ክሱ የሚመለከተው ወጣት። ቆንጆይቱም አጉረምርማ ዝም። ዝምታዋ የንዴት ነው፡፡ ነገር ከቆሰቆሱ በኋላ ‹‹ተረጋጉ›› ማለት በሕዝብ መብት ላይ እያሴሩ ከደሙ ንፁህ ነን ማለትን እንኳን ለእሷ ለቀሪዎቻችንም የተዋጠልን አንመስልም። ታክሲውም በዝምታ ዋግ ተመትቶ በአንዴ እረጭ አለ፡፡ እንዲያ ነው!
ወያላው ሲያሰኘው ፎክሮ፣ ወይም ለምኖ፣ አልሆን ሲለው ደግሞ ተለማምጦ እንደ ምንም የመጀመሪያ ተልኮውን ተወጥቶታል። ተልዕኮው ታክሲዋን መሙላት መሆኑ ነው። ሁሉም ከአሰኘው ጋር የጨዋታ አንድ ሁለት ይላል። አዛውንቷና አጠገባቸው ያለ ወጣት ይጠያየቃሉ። ‹‹…አይ ጉድ ሰው አለቀ!›› ይላሉ አዛውንቷ። ‹‹ትልቅ ሰው ነበሩ?›› ይጠይቃል ከቀብር መመለሳቸውን አስተውሎ ስለተሸኙት ሰው። አዛውንቷ ኮስተር ብለው፣ ‹‹ምነው ልጄ የሰው ትንሽ አለው? ምንም ቢሆን ሰው እኩል መሆኑን ዕድሜ አስተምሮኛል እኮ…›› ይሉታል ቆፍጠን ብለው ወጣቱ ደንግጧል። ፈጣን፣ ከእሱ በላይ አዋቂ፣ ከእሱ በላይ ያለ የማይመስለው የዚህ ዘመን ወጣት ተወካይ የሆነው ይኼው ጎረምሳ መልሳቸው እንደ ብራ መብረቅ ልቡን ተርክኮ ጣለው። ‹‹እንደዚያ ማለቴ ሳይሆን…›› ሲላቸው፣ ‹‹እህ ምን ማለት ነው ታዲያ?›› ሲሉት፣ ‹‹በቃ እሺ ይተውት ይቅር…›› አለ የሚናገረው እየጠፋው። አለመጀመር ነው የሚሻለው!
‹‹አይዞህ ተናገረው ካሰኘህም በአማሪካኛ (እንግሊዝኛ ማለታቸው ነው) በለው። መቼም የዛሬ ልጆች በአሜሪካ ናላችሁ ዞሮ አማርኛውን ረስታችሁታል። ምናለበት ግን ግራ ገብቷችሁ ግራ ባታጋቡን?›› ይሉታል። ወጣቱ አባባላቸውና ሁኔታቸው እያሳቀው፣ ‹‹ቋንቋ ማወቅ እኮ ክፋት የለውም እማማ! አይደለም ዓለም እንዲህ በተቀራረበችበት ወቅት ቀርቶ፣ ድሮም ቋንቋ ማወቅ ወንዝ ያሻግራል ይባላል እኮ…›› ብሎ፣ ‹‹ግን እርስዎ ይህችን አሜሪካ የምትባል አገር ለማየት ተመኝተው አያውቁም?›› ብሎ ጠየቃቸው። ለሚመልሱለት መልስ የሁላችንም ጆሮ ቆመ። መልሳቸው ግን አጭር ነበረ። ‹‹የማያውቁት አገር ሲናፍቅ እኮ ነው?›› አሉት። አጠገቤ የተቀመጠው ‹‹ምነው ግን ዘንድሮ አባባሉ፣ ተረቱ፣ ንትርኩ፣ አሽሙሩ፣ ሽርደዳው በዛሳ?” ይለኛል። ወራጅ አይባል መድረሻው ገና ነው!
ወያላው ከተሳፋሪዎች የሚቀበላቸውን ብሮች መልሶ መላልሶ ሲቆጥራቸው ላስተዋለ፣ በምርቃና ዓለም ውስጥ የት እንዳለ ለማሰብ ይቸግራል። በስሱ ማላመጡንም ዘግይተን እያየን ነው። ‹‹እየው ይኼን ወያላ! ከዓለም ባንክ ካዝና የተዘረገፈለት ይመስል ብሮቹ ላይ እንዴት ነው የሚያፈጠው?›› ይላል አንዱ ከኋላ መቀመጫ። ‹‹ወዶ መሰለህ? ገንዘቡን ደጋግመን ካላየን የሥራ ሞተራችን መቼ በቀላሉ ይነሳል? እንዲህም አልቻልነው እንኳን በባዶ ኪስ…›› ትለዋለች ከጎኑ የተቀመጠች። ‹‹ይቅርታ ይህንን በመጠየቄ ለመሆኑ አንቺ ከዚህ ቅጠላ ቅጠል ሞክረሽ ታውቂያለሽ?›› በማለት የማይጠየቅ ጥያቄ በይቅርታ ሽፋን ሲጠይቅ እንሰማዋለን። እኛም ታክሲ ውስጥ የማይወራ የለም ብለን ሁሉን ችለን እንሰማለን፣ የማይቻል የለምና። ‹‹ከማምረቻ ፋብሪካዎች ይልቅ የጫት መሸጫዎች ቁጥር ባሻቀበት አገርና ዘመን እየኖርኩ እንዴት ብዬ ላመልጥ ወንድሜ?›› ብላ ምፀት አዘል መልስ ወረወረችለት። በተናገረችው ሀቅ ምክንያት አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች በዓይናቸው ተጠቃቀሱባት። የዘመኑ ፈሊጥ ነው!
አንዳንዱ ገልመጥ እያለ ያያትና ድፍረትና ግልጽነቷን ያዳንቃል። ‹‹እውነትም ይህች አገር እያደገች ነው። እንዲህ በአደባባይ ለንስሐ ቅርብ የሆኑ ገመናዎቻችንን ማጋለጥ ከጀመርን ምን እንፈልጋለን? ብራቮ! ብራቮ!” ብሎ አጠገቤ የተቀመጠው ይቦጭቃታል። ከወደ ጋቢና ገልመጥ ብለው፣ ‘ማነች እንዲህ የምታወራው?’ ዓይነት ያዩዋት ተሳፋሪዎች፣ ‹‹እንዲያው ትንሽ አታፍርም? እርባና ቢስ ትውልድ!›› ሲባባሉ መሀል ሰፋሪዎቹ እናዳምጣለን። እንተራረም፣ እንማማር ብለን የሕይወታችንን ሀቅ ከላይ እስከ ታች፣ ከመንግሥት እስከ ግለሰብ እያጥፋፋን አገርን እንዴት ብለን ልንለውጥ እንደምናስብ ለማሰብ ይከብዳል። በአደባባይ የሚታየውን ችግራችንን እንደሌለ ወይም እንደማናውቀው ሆነን ስንኮፈስ፣ ሁላችንንም በሚመለከተን ጉዳይ አያገባንም በሚል መንፈስ ስንሸሽ፣ ሀቁን ፍርጥ አድርገው የሚያወጡትን ስናወግዝ፣ በአጠቃላይ ከእውነት ጋር ተኳርፈን የምንኖር መብዛታችንን የታክሲው ሁኔታ ይገልጸዋል፡፡ ተለመደ እኮ!
መንገድ በክስተት የተሞላ ነውና ታክሲያችን መካከለኛ ፍጥነቱ ተገትቶ መሀል መንገድ ላይ ቀጥ ብሎ ሲቆም ሁላችንም ወደ መንገዱ አሰገግን። በእግረኞች መሻገሪያ ዜብራ ላይ አንድ ሰው ተዝናንቶ ይጓዛል። ለካስ ልንገጨው ኖሯል። ‹‹ደግሞ ይዝናናል እንዴ?›› ይላል ሾፌራችን ድንጋጤው ሳይለቀው። ወያላው መስኮቱን ከፍቶ፣ ‹‹ፍሬንድ ለምን አንደኛህን ዜብራውን ይዘኸው አትሄድም?›› ሲለው ፈገግ ብለን እርስ በርሳችን ተያየን። አዛውንቷ በአንክሮ ሁኔታውን ሲከታተሉ ቆይተው፣ ‹‹የዘንድሮ ሰው የሚፈራው ነገር ምን ይሆን?›› ብለው በነጠላቸው አፍንጫቸውን አበሱ። ‹‹እንዴት?›› አላቸው አጠገባቸው ያለው ወጣት። ‹‹መኪና አይፈራ፣ ሕግ አይፈራ፣ ታላላቆቹን አያከብር፣ እስራት አይፈራ፣ ፈጣሪን አይፈራ፡፡ ይኼንን ሕዝባችንን እየፈጀ ያለውን ገዳይ ኮሮናማ ንቆት አፉን አይሸፍን፣ ርቀቱን አይጠብቅ፣ በዚያ ላይ በብሔር ተቧድኖ እንደ ጠላት እርስ በርሱ ሲጋደል ርኅራኄ የለው፣ ብቻ ምን የልብ ልብ እንደ ሰጠው እንጃለቱ?›› ብለው አሁንም በነጠላቸው ዓይናቸውን አሻሹ። በኮሮና ሕይወታቸው ያለፈው የጥንት ወዳጃቸው ሐዘን ቶሎ ከልባቸው የወጣ አይመስልም። ሲያሳዝኑ!
ከጎኔ ያለው ጎልማሳ ደግሞ፣ ‹‹ምን የልብ ልብ የሚሰጥ ነገር አለ፣ ልብ የሚያዝል ሁሉ ተሰብስቦ…›› ብሎ ወደ እኔ ያፈጣል። ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። ወያላውና ሾፌሩ የበኩላቸውን እንዲህ ይጨዋወታሉ። ‹‹አስበኸዋል በዚህ ዕዳችን ላይ ሰው ገጭተን?›› ሾፌሩ ነው የሚጠይቀው። ‹‹ኧረ በጣም! ሰው እንደሆነ ኑሮ ከሚገጨው መኪና ቢገጨው የመረጠ ይመስላል፤›› ይላል ወያላው። ‹‹እንዲህ ከሆነስ በቁም ከመሞት ይሻላው ነበር። እኛን ያውጣን እንጂ!” ሲል ጨከን ባለ አነጋገር ሾፌሩ ያጉረመርማል። አንዲት ቀዘባ ደግሞ፣ ‹‹ዘንድሮማ ለይቶልናል ማለት ይቀላል፡፡ የአንድ አገር ልጆች ተጨካክነን እንፋጃለን፡፡ ሰብዓዊነት ከውስጣችን ተንጠፍጥፎ አልቆ እንወነጃጀላለን፡፡ ትምህርት ቤት ለዓመታት ቆይተን ዕውቀት መሸመት አቅቶን፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደመና ማዝነብ ሮኬት ሳይንስ ሆነብን እንደናቆራለን፡፡ ከማዳመጥ ይልቅ ማውራት ሱስ ሆኖብን በድንቁርና እንንገላወዳለን…›› ስትል ፀጥ አልን፡፡ ምን እንበል ታዲያ!
ወደ መዳረሻችን መገናኛ ተቃርበናል። ታክሲ ጥበቃ ሌላ ረጃጅም ሠልፎች ይታዩናል። ‹‹ወዴት ነው ይኼ ሠልፍ?” ትጠይቃለች ከኋላ መቀመጫ። ‹‹ወደ ኮተቤ!›› ወያላው ፈጠን ብሎ መለሰላት። ‹‹ምነው ዘንድሮ በየአቅጣጫው ሠልፍ በዛሳ? ሠልፍ ፋሽን ሊሆን ነው? ወይስ ምን ገጠመን?›› ይላል አንዱ፡፡ ‹‹እርግማን! የእሱ ቁጣ! መቼም ፊደል ለቆጠረ የማይዋጥ ቢመስልም ሌላ ሰበብ የለውም…›› ይላሉ አዛውንቷ። የተቀናቀናቸው አልነበረም። የሚታየውን ከማይታየው ለማጣመድ ማስተዋል የሚጠይቅ ይመስላል። ምድራዊ ምክንያቶች መፍትሔ መውለድ ካልቻሉ ለበላይ አካል እንዲህ ነገርን እርግፍ አድርጎ መተው አማራጭ የሌለው ዘዴ ከሆነ ሰነባብቷል። ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎን ከወረድን በኋላ አዛውንቷ፣ ‹‹ልጆቼ መጪው ጊዜ የእናንተ ነው፡፡ በእናንተ ጊዜ በዕጣ ፈንታችሁ ላይ እናንተ እንጂ ማንም ሊወስን አይችልም፡፡ ነገር ግን በማስተዋል ተራመዱ፣ ጥራት ያለው ዕውቀት ቅሰሙ፣ የሳይንስ ዕውቀትን እንጂ የጥንቆላና የአጉል ነቢዮችን ወሬ አታነፍንፉ፣ ዳግማዊ ምኒልክ ያኔ ሥልጣኔ ለአገራቸው ሲያመጡ የገጠማቸውን ፈተና በዚህ ዘመን አትሞክሩ፣ ተማሩ፣ ተመራመሩ፣ ከአሉባልታና ከሐሜት ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ አሉባልታና ሐሜት የመኃይምነት መገለጫ ናቸው፡፡ በኮሮና እንዳትቀጩ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ ምርጫችሁ ደግሞ ለጊዜያዊ ሆይ ሆይታ ሳይሆን ለአገር ዘለቄታዊ ጥቅም ቅድሚያ ይስጥ…›› ብለው ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ እንዲህ ነው እንጂ በዕድሜ የታሸ ዕውቀት፡፡ በባዶ ሜዳ አቧራ ማስጨስ በዛብን እኮ! ኧረ እናረጋጋው! መልካም ጉዞ!