Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባለፉት ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገኘ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዓምና ጀምሮ መሻሻሎች የታየበት የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ 2013 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አስገኘ፡፡

ይህ 2012 .. ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 16 በመቶ ዕድገት የታየበት ሲሆን፣ ዘንድሮ በስምንት ወራት የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ እስካሁን በስምንት ወራት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊገኝበት ችሏል፡፡

የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ገቢ የሚያመላክቱ ተከታታይ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በስምንት ወራት ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የተገኘበት ዓመት የለም፡፡ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚደርሰው ከአሥረኛው ወር በኋላ ነው፡፡  

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2013 ዓ.ም. የስምንት ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸምን በተመለከተ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ በበጀት ዓመቱ በስምንት ወራት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከዓምናው አንፃር ሲታይ የ290 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም ለመጀመርያ ጊዜ ከ290 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡

በስምንት ወራት ውስጥ ከውጭ ንግድ ይገኛል ተብሎ ታቅዶ የነበረው 2.55 ቢሊዮን ዶላር በመሆኑ ይህም ከዕቅዱ አንፃር ማሳካት የተቻለው 82 በመቶውን እንደሆነ የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል፡፡ በ2012 በጀት ዓመት በስምንት ወራት ኢትዮጵያ ከውጭ ንግድ አግኝታ የነበረው 1.8 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በተመሳሳይ በ2011 ዓ.ም. በስምንት ወራት ተገኝቶ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ይታወሳል፡፡ በየዓመቱ በየስምንት ወራት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተወሰነ ደረጃ ዕድገት እየታየበት ቢሆንም ዕቅዱን ማሳካት አልተቻለም፡፡

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2013 በጀት ዓመት በስምንት ወራት ውስጥ የትኛው ምርት ምን ያህል ገቢ እንዳስገኘ ዝርዝሩን ይፋ ባያደርግም፣ ባለፈው ወር የሰባት ወሩን አፈጻጸም ይፋ ሲያደርግ፣ በሰባት ወራት ውስጥ ከተገኘው 1.8 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ የግብርና ምርቶች 1.17 ቢሊዮን ዶላር፣ ማኑፋክቸሪንግ 211.4 ሚሊዮን ዶላር፣ የማዕድን ዘርፍ ደግሞ 373.7 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ ሲያስገኙ፣ ሌሎች ምርቶች ደግሞ 50.6 ሚሊዮን ዶላር አስገኝተዋል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት ከሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶች በተለየ የማዕድን ዘርፍ የወጪ ንግድ ገቢ ዕድገት ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየበት ሆኗል፡፡ ከማዕድን ምርቶች በተለይ የወርቅ የወጪ ንግድ ገቢ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የሚያስገኘው ውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በሒሳብ ዓመቱ በስምንት ወራት ውስጥ ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ችሏል፡፡

ይህም ከቡና፣ አበባና ሰሊጥ ቀጥሎ ከፍተኛ ውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ዘርፍ እየሆነ መምጣቱን አመላክቷል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት የወርቅ ወጪ ንግድ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ በ2011 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ ውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ወደ 30 ሚሊዮን ዶላር ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ግን መሻሻል አሳይቶ በ2013 በጀት ዓመት በስምንት ወራት ውስጥ ከማዕድን ዘርፍ ከ373.7 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲገኝ ካስቻሉት ውስጥ ወርቅ የአንበሳውን ድርሻ ይዟል፡፡

የወርቅ ወጪ ንግድ ባለፉት ሁለት ዓመታት መሻሻል ያሳየበት ዋነኛ ምክንያት የብሔራዊ ባንክ ወርቅ የሚረከብበትን ዋጋ ቀድሞ ከነበረው እንዲሻሻል በማድረጉ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ የወርቅ ወጪ ንግድ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በጀት ዓመቱ እስኪጠናቀቅ ባሉት አራት ወራት ውስጥ የሚያስገኘው ገቢ የማዕድን ዘርፉን አጠቃላይ ውጭ ምንዛሪ በማሳደግ ከሦስቱ ዋና ዋና የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አሳድሯል፡፡

በአንፃሩ በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ማስገኛ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እያሽቆለቆለ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በተለይ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በኋላ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ገቢ ከማሽቆልቆሉም በላይ አንዳንድ ፋብሪካዎች እስከመዘጋት በመድረሳቸው ከዘርፉ የሚጠበቀውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኘት አልተቻለም፡፡

ዘርፉ የገጠመው ችግር አሳሳቢ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ያሻዋል ተብሎ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ችግሩን ለመፍታት ያስችላል ያላቸውን ሥራዎች እንደሚሠራ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች