Friday, September 22, 2023

የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ላይ ለውጥ ያስከትል ይሆን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የፌዴራል መንግሥቱን በሚመራው ገዥ ፓርቲ ብልፅግናና የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው ሕወሓት መካከል የነበረው የፖለቲካ መካረር፣ በስተመጨረሻ ላይ ሕወሓት የሚመራው ኃይል በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በሰነዘረው ጥቃት ምክንያት አይቀርም የተባለውን የጦር ግጭት አፍጥኖታል። 

በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በይፋ የተጀመረው የሁለቱ ወገኖች ውጊያ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ መቀመጫውን መቀሌ ያደረገውን የሕወሓት ኃይል ከመንግሥታዊ መንበሩ አውርዶ፣ ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ቢያስችልም በሁለቱ የአንድ አገር ኃይሎች መካከል የተጀመረው ውጊያ እስካሁን ማብቂያ አላገኘም። 

የፌዴራል መንግሥቱ ያሰማራው የአገር የመከላከያ ሠራዊት በርካታ የትግራይ ክልል ከተሞችን የተቆጣጠረ ሲሆንከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሠለፍ የሕወሓትን ኃይል የማጥቃት ዘመቻ ውስጥ የኤርትራ ጦር መሠለፉ ሲነገር ቆይቷል። 

የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥት ኃላፊዎች የኤርትራ ጦር ተሳትፎን ሲያስተባብሉ የቆዩ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) የኤርትራ መንግሥት ለብሔራዊ ደኅንነቱ በመሥጋቱ፣ የኢትዮጵያ ጦር በሕወሓት ጦር ላይ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ የለቀቃቸውን የኤርትራ ድንበር አካባቢዎች ድንበር አልፎ መቆጣጠሩን በይፋ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው በዚህ ግጭት በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በኤርትራና በኢትዮጵያ ሠራዊት መፈጸማቸውን የተመለከተ ሪፖርት በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጭምር ሪፖርት የተደረገ ሲሆንበትግራይ ክልል ግጭት ምክንያትአራት ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎች ለከፍተኛ የምግብ አቅርቦት ችግር መጋለጣቸውና ከጅምላ ጭፍጨፋ እስከ አስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የሚያመላክቱ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የውጭ ኃያላን መንግሥታት ከፍተኛ ጫና በማሳደር ላይ ናቸው። 

ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የአውሮፓ አገሮችና የአውሮፓ ኅብረት በቀዳሚነት መሰንዘር የጀመሩት ዲፕሎማሲያዊ ጫናየኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መቀሌን ከተቆጣጣረ ከሞላ ጎደል ከሁለት ወር በኋላ ማለትም ... ጃንዋሪ 20 ቀን 2021 ወደ ሥልጣን በመጣው አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር በከፍተኛ ሁኔታ ተጣምሮ፣ በስተመጨረሻም ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት መድረክ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች ተርታ ተሠልፏል። 

ይህ ፖለቲካዊ ጫና በዋናነት በትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለመግታት ያለመ ቢሆንም፣ ውስጥ ውስጡን ግን የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ የውስጥ ግጭት መሳተፉን ከሌሎች የጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር ተዳምሮ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የመዛመትና ቀጣናውን የመረበሽ አዝማሚያ ይኖረዋል የሚል ሥጋት የጫረው እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።

የአሜሪካ መንግሥትም ሆነ የአውሮፓ ኅብረትና የአውሮፓ መንግሥታት የሚያወጧቸው መግለጫዎችም ይህንኑ ሥጋት በግልጽ የሚጠቅሱና የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ በግልጽ የሚጠይቁ ናቸው።

ይሁን እንጂ በፕሬዚዳንት ባይደን የሚመራው የአሜሪካ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመውጣቱ አስቀድሞ የነበረው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ የትግራይ ክልል ግጭትን አስመልክቶ የያዘው አቋም ለዘብተኛ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። 

የፌዴራል መንግሥት የሕግ ማስከበር ዘመቻ ብሎ የሚጠራው በትግራይ ክልል ውስጥ በመካሄድ ላይ የነበረው የጦር ግጭት መቀሌን በፌዴራል መንግሥት ጦር ቁጥጥር ውስጥ መግባቱ ... ኖቬምበር 28 ቀን 2020 ይፋ በተደረገ በማግሥቱ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናዥና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ማይክ ራይነር ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ፣ በወቅቱ የነበረውን የአሜሪካ መንግሥት የትግራይ ክልል ግጭትን አስመልክቶ ይዞት የነበረውን የፖለቲካ ከቋም በግልጽ ከሚጠቁሙ መረጃዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።

ሁለቱ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት መግለጫውን በሰጡበት ወቅት ከውጭ ጋዜጠኞች ቀርበውላቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል አንዱ፣ በውጊያ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ኃይሎች ግጭቱን እንዲያቆሙና በድርድር ችግራቸውን እንዲፈቱ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ፖለቲካዊ ጫና ለምን አያደርግም? እስካሁንስ በዚህ ረገድ የአሜሪካ መንግሥት ምን ያደረገው ተጨባጭ ነገርን እንዲያብራሩ የሚጠይቅ ነበር። 

ለጥያቄው ቀዳሚ ምላሽ የሰጡት የወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናዥ፣ ‹‹የሁለቱ ወገኖችን አቋም በቅርበት ለሚረዳ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡትን ምላሽ አስቀድሞ ሊገነዘብ ይችላል፡፡ ልዩነቶቻቸውን በድርድር እንዲፈቱ ማገዝ አንድ አማራጭ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ለማድረግ ለመደራደር ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል፤›› ብለው ነበር።

ለጊዜው የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ግጭት በተመለከተ ያስቀመጠው ግብ ድርድር ሳይሆን ሰላም እንዲፈጠር ማድረግ እንደሆነ የሚገልጽ ምላሽ በመስጠት፣ ባልደረባቸው የሆኑት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ከሁለቱ ኃይሎች ጋር ያደረጉት ንግግር እንዳለ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጋብዘዋቸው ነበር።

በወቅቱ የአዲስ አበባ አምባሳደር የነበሩት ማይክ ራይነር በሰጡት ምላሽጋዜጣዊ መግለጫውን ከሰጡበት ከአንድ ሳምንት አስቀድሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) እና ከሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (/) ጋር በስልክ እንደተወያዩና የድርድር አማራጭን እንዳቀረቡ በመጥቀስ፣ ሁለቱም ኃይሎች ጥያቄውን ውድቅ እንዳደረጉት ገልጸው ነበር። 

በሁለቱ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚለው በአጭር ጊዜ ካልተጠናቀቀ ወደ አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሊዛመት ይችላል የሚለውን ሥጋት የአሜሪካ መንግሥት እንዴት እንሚመለከተው የተጠየቁት ሁለቱም ባለሥልጣናትግጭቱ ቶሎ መቆምና ሰላም መፈጠር እንዳለበት አሜሪካ የምታሳስበው ግጭቱ ተስፋፍቶ ወደ አፍሪካ ቀንድ ግጭት ይሸጋገራል ወይም ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ይሸጋገራል በሚል እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ነገር ግን ማንኛውም ግጭት በፍጥነት መፍትሔ ካላገኘ ተጓዳኝ ችግር ይዞ መምጣቱ የማይቀር እንደሆነ፣ አሜሪካም በዚሁ ምክንያት ሁለቱ ወገኖች ግጭቱን እንዲያቆሙ እያሳሰበች እንደሆነ ገልጸዋል። 

ይህ የአሜሪካ መንግሥት አቋም ግን ዘላቂ አልነበረም። አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ ከፍተኛ ጫና በኢትዮጵያ ላይ ማድረስ ችሏል። 

አሜሪካ ግጭቱ በፍጥነት እንዲያቆም በተናጠል ከሰነዘረችው ጫና ባሻገር፣ የአውሮፓ አገሮችን በማስተባበርና የተመድ የፀጥታ ምክር ቤትን በመጠቀም እስከ መጨረሻው ጥራለች። 

ነገር ግን በተመድ የፀጥታ ምክር ቤት በኩል የተሰነዘረ ጫና በዋናነት በሩሲያና በቻይና፣ እንዲሁም የተወሰኑ አባል አገሮች ባደረጉት መከላከል ኢትዮጵያ ሊጣልባት ከሚችል ማዕቀብ አምልጣለች። ቢሆንም ግን ከተመድ ውጪ በተናጠል ማዕቀብ ለመጣል ያዘነበለ ፍላጎት ስለመኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራርያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከማንም አገር ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ አተካራ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ፍላጎት ካላቸው አገሮች ጋር ኢትዮጵያም ጥቅም ያላት በመሆኑ፣ በዲፕሎማሲያዊ ውይይት መቀራረብ እንደሚቻል ከዚህ ውጪ ግን የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ እንደማይቻል አስረድተዋል። ለዚህ ያላቸውን ቁጥርጠኝነት ሲገልጹም ‹‹አንገቴ ይቀላል›› ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን በተናገሩ በቀናት ውስጥ የሩሲያና የአፍሪካ መንግሥታት ገዥ ፓርቲዎች ውይይት ላይ በመሳተፍ ባደረጉት ንግግርበአገሮች የውስጥ ጉዳይ የሚገቡ የውጭ መንግሥታትን ጫናና ፍላጎት በማርከስ ረገድ ሩሲያና የአፍሪካ መንግሥታት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው በመጥቀስ፣ ይህንን ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ዛሬ ዳግም እንዲያንሰራራ ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሩሲያ የፖለቲካ ፈላስፎች ለአፍሪካ አገሮች ነፃነት ባደረጉት ከፍተኛ የሞራል ድጋፍ ለኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ፣ ለጋናው ንኩሩህማ፣ ለጀሞ ኬንያታ፣ ለደቡብ አፍሪካው ማንዴላ ስንቅ ሆኖ አገራቸውን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ማውጣት አስችሏቸዋል ብለዋል።

‹‹አፍሪካና ሩሲያ የቆየ ልምድ አላቸው። የውጭ ተፅዕኖን ያለ መቀበል፣ የመጠየቅና አዳዲስ አማራጮችን የማስቀመጥ ልምድ አላቸው። እነዚህን ልምዶቻችን በድጋሚ እንዲያንሠራሩ እናድርግ፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -