Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኦቲዝም ላለባቸው የኮቪድ ክትባት በቅድሚያ እንዲሰጣቸው ጥሪ ቀረበ

ኦቲዝም ላለባቸው የኮቪድ ክትባት በቅድሚያ እንዲሰጣቸው ጥሪ ቀረበ

ቀን:

ለኦቲዝም ተጠቂዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ኒያ ፋውንዴሽን ጥሪ አቀረበ፡፡

ጥሪው የቀረበው የዓለም የኦቲዝም ቀንና የሚያዝያ ወርን ‹‹የኦቲዝም ግንዛቤ ወር›› እንደሚሆን በማስመልከት መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የኦቲዝም ተጠቂዎች እንደሚኖሩ ይገመታል ያሉት የኒያ ፋውንዴሽን መሥራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ ዘሚ የኑስ፣ ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በይበልጥ ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ በመሆናቸው ክትባቱን ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኦቲዝም ተጠቂዎች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ  መከላከል ስለማይችሉ፣ ቤተሰቦቻቸውን ጭምር ለቫይረሱ ያጋልጣሉ ብለዋል፡፡

ከተመሠረተ 19 ዓመታትን ያስቆጠረው ኒያ ፋውንዴሽን በዓሉ በኢትዮጵያ የሚከበረው ‹‹በሥራ ዕድሎች መካተት፣ ኮቪድ-19ን ተከትሎ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችና መልካም ዕድሎች›› በሚል መሪ ቃል ነው፡፡

የኦቲዝም ቀን እንደ ሌሎች ዓመታት የአደባባይ ትርዒቶችን በማቅረብ ባይከበርም መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች ወሩን ሙሉ እንደሚካሄድ ወ/ሮ ዘሚ ተናግረዋል፡፡

ኦቲዝምና ትምህርት፣ ኦቲዝምና ኮሮና ወረርሽኝ፣ ሌሎችም ጽንሰ ሐሳቦችን በማንሳት ኅብረተሰቡ ሰፊ ግንዛቤና ለውጥ እንዲያመጣ የሚያግዙ ንቅናቄዎች በሚዲያዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የሕክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ያዕቆብ ሴሚን (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ኦቲዝምና የሥነ አዕምሮ ሕክምናን ጨምሮ ሕክምና የሚሰጡ ተቋማት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ስድስት፣ በክልሎች ደግሞ 83 ደርሰዋል፡፡

በእነዚህ ሆስፒታሎች ተገልጋዮች እንዲሄዱ ለኅብረተሰብ ስለኦቲዝምና ተያያዥ ጉዳዮች ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር ሚዲያዎች ጉልህ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር ለእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፣ ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ደግሞ ሁሉም ዘርፎች በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ዘላቂ የአዕምሮ ዕድገት እክል ምክንያት ኦቲዝም የሚከሰት ሲሆን፣ በዚህ የተያዙ ሰዎች ለመግባባት መቸገር፣ ለድምፅ፣ ለንክኪ፣ ለጣዕም፣ ለሽታ፣ ለብርሃንና ለቀለም የተለየ ስሜት ማሳየት ከሚታይባቸው ችግሮች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሁሉም በኦቲዝም የተጠቁ ሰዎች መግባባት አለመቻል፣ የሌሎች ሰዎችንም ሆነ የራሳቸውን ስሜት መግለጽ ባለመቻላቸው ከማኅበረሰቡ ጋር መግባባት ይቸገራሉ፡፡

መንስዔው እስካሁን በውል ያልታወቀ ሲሆን የአዕምሮ ሕመም እንዳልሆነ ግን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አዲስ ከሚወለዱ 57 ሕፃናት አንዱ ኦቲስቲክ መሆኑን ጥናቶች እንደሚያሳዩና ይህም ኦቲዝም የዓለም ዋነኛ ችግር እየሆነ መምጣቱን ወ/ሮ ዘሚ አብራርተዋል፡፡

ለኦቲዝም እስካሁን ምንም ዓይነት መድኃኒት ያልተገኘለት፣ ነገር ግን በመማርና  ሌሎች ዘዴዎች በመጠቀም ችሎታቸውን ከፍ የሚያደርጉ አማራጮች እንዳሉም አውስተዋል፡፡

የድምፅና የቋንቋ፣ የሥራና ስሜት ኅዋሳት ማቀናጀት እንዲሁም የማየትና ሙዚቃ የመስማት ቴራፒዎችን በመስጠት ክህሎታቸው ከፍ ማድረግ ይቻላል፡፡

በኒያ ፋውንዴሽን ሥር የሚገኘው ጆይ የኦቲዝስቲክ ልጆች ማዕከል በአሁኑ ወቅት 80 ተማሪዎችን ያቀፈ ሲሆን፣ እየተገነባ ባለው ሰፊ ማዕከል ደግሞ 400 የኦቲስቲክ ልጆችን ማስተናገድ እንደሚችል ወ/ሮ ዘሚ ገልጸዋል፡፡

ሰሚት አካባቢ በ5,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እየተገነባ ያለው የኦቲስቲክ ልህቀት ማዕከል 250 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና ባለሀብቶች፣ ተቋማት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ዕገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...