በኢትዮጵያ በርካታ ዜጎች መደበኛ ትምህርት ቤት ሳይሄዱ ማንበብ፣ መጻፍና ማስላት ይችላሉ፡፡ ለዚህም የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ የሃይማኖት ተቋማት በገጠርም ይሁን በከተማ ያሉት ሰዎች መደበኛ ትምህርት ቤት ሳይሄዱ ፊደልን በማስቆጠር፣ ንባብን በማስነበብና ቁጥርን በማስላት ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ያበረከቱትም ሆነ እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ሁሌም የሚነሳ ነው፡፡
በእንዲህና በሌሎች ኢመደበኛ መንገድ ዕውቀት ያካበቱትን ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል ያለው ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ የትምህርት ብርሃን ምዘና መርሐ ግብር አስጀምሯል፡፡
መርሐ ግብሩ በተለይ በኢመደበኛ መንገድ መሠረታዊ ዕውቀት አካብተውና በዕውቀታቸው እየሠሩበት ለሚገኙት ምዘና ሰጥቶ ዕውቅናን የሚቸር ነው፡፡
የትምህርት ብርሃን ምዘና መርሐ ግብር በይፋ ሲጀመር የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት፣ የምዘና ሥርዓቱ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ዕውቀት የቀሰሙ ሰዎችን ያነቃቃል፣ ሌሎች ዜጎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡና መደበኛ ትምህርት እንዲማሩ ያስችላል እንዲሁም የትምህርት ምጣኔን ያሳድጋል፡፡
ማንበብ፣ መፃፍና ማስላት ለሚችሉ ዜጎች ዕውቅና የሚሰጠው የትምህርት ብርሃን ምዘናን አስመልክተው የትምህርት ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ይህ ሥርዓት አንዱ የትምህርት ሥርዓቱ የለውጥ አካል ነው፡፡ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው በመደበኛው ትምህርት ሳይሆን በኢመደበኛ መንገድ ማንበብ፣ መጻፍና ማስላት የሚችሉ ዜጎችንም ዕውቅና ይሰጣል፡፡
ከዚህ ቀደም በተለያየ መልኩ ሲተገበር የቆየው መሠረተ ትምህርት፣ የጎልማሶች ትምህርት፣ እንዲሁም አሁን የተጀመረው የትምህርት ብርሃን ንቅናቄ ቀጣዩን ትውልድ የሚያነሳው መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ከ1889 ዓ.ም. ጀምሮ ያሉ መንግሥታት ሁሉ ለትምህርት ቅድሚያ የሰጡና ማይምነትን ሲዋጉ እንደኖሩ ያስታወሱት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ በተለይ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ እየተተገበረ ያለው የጎልማሶች ትምህርት ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት 75 ዓመታት ማይምነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በተሠራው ሥራ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ከማይምነት ማላቀቅ መቻሉን፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ የትምህርት ቀመር ሥርዓት በአግባቡ ሳይሰነድ ቆይቷል ብለዋል፡፡
የትምህርት ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን አካል የሆነው የትምህርት ብርሃን ምዘና ሥርዓት ማንም ዜጋ ማንበብና መጻፍ ከቻለ ብሔራዊ ምዘና ወስዶ የሦስተኛ ክፍል ሰርተፊኬት የሚያገኝበት እንደሆነም ትምህርት ሚኒስትሩ አሳውቀዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ፈተናን በመስጠትና ላለፉት የሦስተኛ ክፍል ሰርተፊኬት በመስጠት ብቻ የሚቆም ሳይሆን፣ እስከ ስድስተኛ ክፍል የሚዘልቅና ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 60 ዓመት የሆኑና መደበኛ ትምህርት ለመማር ዕድል ያላገኙ ወጣቶችና ጎልማሶች ሁሉ የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ማንበብና መጻፍ የተረጋገጠበት፣ ገበሬው በግብርና፣ ነጋዴው በንግዱ፣ ሁሉም በየሙያው ምርታማና ውጤታማ የሚያደርግ የትምህርት ምዘና ምዕራፍ ነውም ብለዋል፡፡
የትምህርት ብርሃን ንቅናቄ ብዙ ሚሊዮኖችን የሰርተፊኬት ባለቤት እንደሚያደርግም ታምኖበታል፡፡