Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተባባሰው የተመሳሳይ ፆታዎች አስገድዶ መድፈር ወንጀል

የተባባሰው የተመሳሳይ ፆታዎች አስገድዶ መድፈር ወንጀል

ቀን:

የቤተሰብ ትኩረት የተነፈጋቸውና ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 18 ዓመት የሚሆኑ ታዳጊዎችን ጨምሮ ድርጊቱን ይፈጽማሉ፡፡ የተመሳሳይ ፆታ አስገድዶ መድፈር (ግብረ ሰዶም) ወንጀል፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ እየተስፋፋ መሆኑን መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ዳይሬክተር ወ/ሮ ጽጌ የማነ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በአስገድዶ መድፈርና መሰል ድርጊቶች ክስ ላይ ያሉ ጉዳዮች 264 መዝገብ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 86ቱ አስገድዶ መድፈር ሲሆኑ፣ 44ቱ ደግሞ በሕፃናት ላይ የተፈጸሙ የግብረ ሥጋ ግንኙነትና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ 264 በአስገድዶ መድፈር፣ በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ ልጅ ወልዶ ጣልን ጨምሮ የክስ መዝገብ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 24ቱ የግብረ ሰዶም ወንጀል፣ 11 ደግሞ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጊቶች በአሥሩም ምድብ ችሎቶች የሚታዩ መሆናቸውንና 118 መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ወንጀሎቹ የሚፈጽሙት በቅርብ ቤተሰብ ናቸው፡፡ በኅብረተሰቡ የተደበቁ ወንጀሎችም በርካታ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተበራከቱ የወንጀል ዓይነቶች ውስጥ ግብረ ሰዶም አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ይመጣ የነበረው ጉዳይ ወንድ ለወንድ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ሴት ለሴት ወደ ክስ መምጣት መጀመሩን በቦሌ ምድብ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች አስተባባሪ ዓቃቤ ሕግ ወ/ሪት ሊያ እስክንድር ተናግረዋል፡፡ ችግሩን የጎላ የሚያደርገው ደግሞ በማስገደድ የሚፈጸም ግብረ ሰዶም ዕድሜያቸው 14 እና ከዚያ በላይ በሆኑ ሕፃናት ላይ መሆኑ ነው፡፡

የግብረ ሰዶም ወንጀል ፈጻሚዎቹ ዕድሜያቸው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች መሆናቸው ችግሩን የጎላ እንዳደረገውና የማኅበረሰቡ (የቤተሰብ) ጥፋት እንዳለበትም ባለሙያዋ አክለዋል፡፡

ታዳጊዎቹ በምን ምክንያት ድርጊቱን ሊፈጽሙ ቻሉ? የሚሉ ጥያቄዎች ቢጎርፉም በዚህ ላይ ሰፊ ጥናትና ውይይቶች በማድረግ የማኅበረሰቡ ሥነ ልቦና መታከም እንዳለበት የሴቶች ሕፃናት የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ሴኔት ታፈሰ አሳስበዋል፡፡

የግብረ ሰዶም ወንጀል የሚፈጽሙትና የሚፈጸምባቸው ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 18 ክልል ውስጥ ቢሆንም የአዋቂዎች የጎላ ነው፡፡ የ14 ዓመት ታዳጊ የግብረ ሰዶም ወንጀል ለምን እንደፈጸመ ሲጠየቅ ፊልሞችን በማየት መሆኑን እንደነገሯቸው የሥነ ልቦና ባለሙያዋ አክለዋል፡፡

ወ/ሮ ሴኔት ስለወንጀል ፈጻሚዎቹ በምሳሌነት ያነሱት አንድ የወንጀል ድርጊት የ11፣ የ16 እና የ18 ዓመት ታዳጊዎች የስድስት፣ የአሥርና የአሥራ አንድ ዓመት ታዳጊዎች ላይ ስለፈጸሙት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ነው፡፡

ወንጀሉን የፈጸሙ ታዳጊዎች ቤተሰቦች ‹‹በፍፁም ልጄ ይኼን አያደርግም፤›› ብለው የሚሞግቱም ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም ወላጆች ልጆቻቸው ወንጀል ይፈጸምባቸዋል እንጂ ወንጀሉን ይፈጽማሉ ብለው ስለማያስቡ ችግሩን የጎላ አድርጎታል፡፡

አሁን ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ፣ በየፖሊስ ጣቢያው አንድ መርማሪ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ፆታዊ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የፖሊስ መምርያ ላይ እንዲጣራ የሚደረግ ሲሆን፣ አንዲት ሴት ጥቃት ሲደርስባት አካባቢዋ ላይ ወደሚገኝ ጣቢያ ብትሄድ ማስረጃ ሳይጠፋ ወደ ሕክምና ተቋም እንድትሄድ ትደረጋለች፡፡

ለዚህ ተብሎ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልና በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ ዋንስቶፕ ሴንተር ላይ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሕፃናትና ሴቶች ሕክምና እንዲያገኙ መንገድ ተመቻችቷል፡፡

ወ/ሪት ሊያ እንደገለጹት፣ የችግሩ ሰለባ የሆኑት ወንድም ሆነ ሴት ልጆች ቤተሰብ ከሌላቸው፣ እንዳይመሰክሩ ሊደረጉ ይችላሉ ተብሎ ከተገመተና ከደኅንነትም አንፃር ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር እንዲገቡ ይደረጋል፡፡

በተቻለ መጠን በሴቶችና ሕፃናት ላይ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ የተያዙ ተከሳሾች ፍርድ ቤት በሚሰጠው ቀጠሮ ውስጥ በዋስ ሳይወጡ በፍጥነት ክስ እንዲመሠረት ይደረጋልም ብለዋል፡፡

በሕፃናትና ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ላይ ብዙ ጊዜ መዝገቦች ተጓተቱ የሚሉ ቅሬታዎች እንደሚነሱ የሚናገሩት ወ/ሪት ሊያ፣ በክስ ሒደት ውስጥ ትልቁ ችግር ምስክሮች መጥፋታቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ብዙ ጊዜ እያጋጠመ ያለው ችግርም ምስክሮችን በገንዘብ በመደለል፣ የቤተሰብ ጫና፣ ፍላጎት አለመኖርና ፍራቻ ምስክሮች ከችሎት የሚቀሩበት አጋጣሚም ይጎላል፡፡

አንዳንድ ጊዜ የደኅንነት ፍራቻ ያለባቸው ምስክሮች ተጎጂዎች በሚቆዩበት ተቋም እንዲቆዩ እንደሚያደርግ፣ ዋናው ግን በመፍራት ብቻ ሳይሆን ወንጀል ከፈጸመው ግለሰብ ጋር እየታረቁ በቀጣይ ቀጠሯቸው ቀን ለመምጣት ፈቃደኛ የማይሆኑበት አጋጣሚ እንዳለም ተናግረዋል፡፡

ሕጉን ለማስፈጸም ወንጀል ፈጻሚዎችና የተፈጸመባቸው ጉዳዮን በሽምግልናና በርቅ መጨረሳቸው፣ አንዳንዴም መደለያ መኖሩ እንቅፋት ሆኗል፡፡

ወንጀል የተፈጸመባቸውም ወደ መጠለያ እንዲገቡና ፍትሕና የሥነ ልቦና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚሠራ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ክስ መቋረጡ ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡ 

ወ/ሪት ሊያ ችግሮች ብለው ካነሷቸው ዋስትና አሰጣጥ ይገኝበታል፡፡ የወንጀል መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 67 ላይ ዋስትና የሚከለከልባቸው ወንጀሎች አሉ፡፡ ፆታዊ ጥቃቶች ላይ የተቀመጡት ግን ዋስትና የሚከለክሉ አይደሉም፡፡

ዓቃቤ ሕግ የተለዩ ምክንያቶችን ቢያቀርብም ከወንጀሉ አንፃር የሚሰጠው ብይን ከፍ ያለ ባለመሆኑ ዋስትና ተፈቅዶ ተከሳሽ ተመልሶ ላይመጣ ስለሚችል አብዛኛውን ጊዜ ዋስትና ይቃወማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ምስክሮች እንዳይደለሉ በሚልና በተለያዩ ምክንያቶች ዋስትና የሚቃወሙ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ ዋስትናው ከተፈቀደ ተከሳሽ የሚጠፋበት አጋጣሚ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ከውጭ ፆታዊ ጥቃቶችን ያወግዛል፣ ይቃወማል ነገር ግን ወንጀለኛ አሳልፎ በመስጠት በኩል ክፍተቶች አሉ ብለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎች አንዳንዴ ዋስትና አግኝተው ከወጡ በኋላ በተሰጠው አድራሻ መሠረት ሲፈለጉ አለመገኘት፣ ቤተሰብ የመደበቅ፣ አድራሻ የማስቀየር ችግሮች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ ጥቃት የተፈጸመባትን ሴት፣ በሠፈር ውስጥ መኖር እስኪያቅታት መጠቋቆሚያ የሚያደርጉ እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ ምስክሮችና ተከሳሽ ባለመቅረብ ምክንያት የመዝገቦች መቋረጥ እንደሚያጋጥምም ተገልጿል፡፡  

ወ/ሪት ሊያ እንዳስረዱት፣ በቦሌ ምድብ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአስገድዶ መድፈር ክስ እየጨመረ ነው፡፡ ሰው ከጊዜ ወደ ጊዜ ሪፖርት የማድረግ ግንዛቤው እያደገ በመምጣቱ ይሆን ወይም በሌላ ምክንያት አይታወቅም፡፡ ቁጥሩ በትክክል ጨምሯል የሚለውን ለማወቅም ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በአዲስ አበባ ካሉት ክፍላተ ከተማ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው ቦሌ ሲሆን፣ ይህም ክፍለ ከተማ ሰፊ ከመሆኑ፣ ሪፖርት የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ከፍ በማለቱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በተለይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገሮች እንቅስቃሴዎች ስትገድብ አስገድዶ መድፈር ወንጀል መጨመሩ ይታወሳል፡፡

አርቲስቶች ባደረጉት እንቅስቃሴ ‹‹ለምን እንደዚህ ሆነ?›› እያሉ ለተለያዩ ሚዲያዎች ስለሁኔታው ያሰሙ ቢሆንም፣ ከጊዜያት በኋላ ወንጀሎቹን የሕግ ሥርዓቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳደረሳቸው ጠያቂ መታጣቱን ወ/ሪት ሊያ ይናገራሉ፡፡

ለጊዜው ሁሉም አውርቶ እንደተወው በማስታወስ ሰሙናዊ ብቻ መሆን እንደሌለበት፣ ዓቃቤ ሕግ በኮሮና ቫይረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመርያ ወቅትም ይሠራ እንደነበር፣ አሁንም ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

‹‹በእኛ በኩል ክፍተቶች ቢኖሩም ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ስለሆነ አሁንም የማኅበረሰቡ ትብብር እጅግ ወሳኝ ነው፤›› ሲሉ ወ/ሪት ሊያ አክለዋል፡፡

እንደ እሳቸው አገላለጽ፣ አስገድዶ መድፈር በባህልም፣ በሃይማኖትም፣ በሕግም የተወገዘ መሆኑን እያንዳንዱ የማኅበረሰቡ ክፍል ያውቃል፡፡ነገር ግን የመከላከያ ምስክር ሆነው የሚመጡትና በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁርዓን ላይ እጃቸውን ጭነው በውሸት የሚምሉበት እነዚሁ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ነፃ የተባሉ መዝገቦች ባይኖሩም የውሸት ክሶች የሚኖርበት አጋጣሚ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

አስገድዶም ሆነ በፈቃደኝነት ግብረ ሰዶም መፈጸም ወንጀል ነው፡፡ ነገር ግን ከሚመጡ ሪፖርቶች አብዛኛው የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ሲሆኑ፣ የሚፈጸሙት ደግሞ በቅርብ ሰው ነው፡፡ ወንጀሉ የሚፈጸመው በቤተሰብ አባት፣ ወንድም፣ አጎት፣ ዘመድ፣ ወዳጅና በአካባቢ ሰዎች መሆኑን በሩቅ ሰዎች የሚፈጽሙት በቁጥር አነስተኛ እንደሆኑ እነዚህ ወንጀሎች እንደ አገር ሊያሳስቡ የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡

ወላጆች የልጆቻቸውን የቀን ውሎና እንቅስቃሴ ማጤን፣ በስልኮቻቸው ምን እየተጠቀሙ እንዳሉ መመርመርና ወንጀለኛ እንዳይሆኑና ወንጀል እንዳይፈጸምባቸው መጠበቅ አለባቸው ያሉት ወ/ሪት ሊያ፣ ትውልድን የመታደግ ሥራው ለአንድና ለሁለት ተቋም የሚተው እንዳልሆነ፣ በፖሊስ፣ በዓቃቤ ሕግና በፍርድ ቤት ብቻ ችግሩ የሚፈታ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወንጀሎች ከመፈጸማቸው በፊት የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ አርቲስቶችና ሌሎችም ኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ እንዲሠሩና ቅድመ መከላከሉ ላይ ትኩረት እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወንጀሉ ከመፈጸሙ በፊት ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ሥራዎች መብዛት እንዳለባቸው፣ ማስቀጣቱ ለማስተማር እንጂ፣ ለተበዳይ የሚመልሰው ነገር ባለመኖሩ መከላከሉ ላይ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡  

ኅብረተሰቡ ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል ከሚችልበት መንገድ በግልጽ መነጋገር ሲሆን፣ በቤት ውስጥ የሚደረጉ ግልጽ ንግግሮች ወሳኝ እንደሆኑ ወ/ሪት ሊያ ያስረዳሉ፡፡

ብዙዎቹ ክሶች የሚመጡት ከወራትና ከዓመታት በኋላ ሆኖ፣ ማስረጃዎቹ ከጠፉ በኋላ እንደሆነ፣ ለምን እንደቆዩ ሲጠየቁም በፍርኃት መሆኑን የሚገልጹም መኖራቸውን በመጠቆም፣ ይኼ በአብዛኛው የሚያሳየው በቤተሰብ ውስጥ በግልጽ የመነጋገር ልምድ አለመኖሩንና ልጆች ነፃ ሆነው እንዲያውሩ የማድረግ ልማድ እጅግ አናሳ መሆኑን ያስገነዝባል ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችም በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸው በጠቆሙት ወ/ሪት ሊያ አገላለጽ፣ በሌሎች አገሮች ላይ አስገድዶ መድፈር የሚፈጽሙ ወንጀለኞች ተደጋጋሚ ድርጊት የሚፈጽሙበት አጋጣሚ የጎላ ነው፡፡ ተቀጥተው ከወጡም በኋላ ያንን ወንጀል ደግመው የመሥራት አጋጣሚ ስላለ ታራሚዎች ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ሕክምና መሠራት አለበት፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ የ2012/13 ዓ.ም. የዘጠኝ ወር ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከ64 መዝገቦች ክስ ከቀረበባቸው ጉዳዮች አስገድዶ መድፈርና መሰል ድርጊቶች 56 ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ 38ቱ አዋቂዎች ላይ የተፈጸሙ ናቸው፡፡ ሦስት ተጠርጣሪዎች የግብረ ሰዶም ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ከ64 የክስ መዝገቦች ውስጥ በ32ቱ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ውሳኔ ካገኙት ውስጥ 28 አስገድዶ መድፈርና መሰል ድርጊቶች፣ አራቱ ደግሞ የግብረ ሰዶም ድርጊቶች ናቸው፡፡በዚሁ ክፍለ ከተማ ምስክር ባለማግኘት ዘጠኝ መዝገቦች ተቋርጠዋል፡፡

ወ/ሪት ሊያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ወንጀል ፈጻሚዎች ከዚህ በፊት ወንጀል ተፈጽሞባቸው ነበር ወይ?›› የሚሉትንና አሁን ወንጀል የተፈጸመባቸው ሰዎች ነገ እንደማይፈጽሙ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል ሰፊ የማኅበረሰብ ጥናቶች ያስፈልጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...