አስገዳጅ የነበረው 20 በመቶ መዋጮ ይቀራል ተብሏል
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ይሰጥ የነበረው የሊዝ ፋናንሲንግ አገልግሎት ከቆመ 18 ወራት በኋላ ሊጀመር መሆኑንና በብድር ለሚያቀርባቸው ማሽኖችና የካፒታል ዕቃዎች ተጠቃሚዎች፣ በቅድሚያ የ20 ከመቶ የመዋጮ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስገድደውን የመመርያ ድንጋጌ ለማስቀረት አዲስ መመርያ እያዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ፡፡
የአዲሱ መመርያ ዝግጅት የተገለጸው ባለፈው መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠሪነት በተካሄደው ይፋዊ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ነው፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች በኦዲት ወቅት የተከለሱ ማስረጃዎችንና የናሙና ጥናቶችን መሠረት በማድረግ፣ ተዘጋጅቶ በቀረበው የኦዲት ሪፖርት መነሻነት፣ ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ልማት ባንክ ከ2009 በጀት ዓመት አስከ 2012 የመጀመርያው ሩብ ዓመት ድረስ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ባቀረበው የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ውጤታማነት ላይ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መሠረት የተደረገ ውይይት ነበር፡፡
የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባቀረበው ሪፖርት ውስጥ በተካተቱ የኦዲት ግኝቶችንና በተጠቆሙት የማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች በመንተራስ፣ በቋሚ ኮሚቴውና በአባላቱ በተናጠል በርካታ ጥያቄዎች ለባንኩ ኃላፊዎች ቀርበዋል፡፡ ከቀረቡት ዋነኛ ጥያቄዎች ውስጥ በአገሪቱ ሙያና ችሎታ ኖሯቸው ከመደበኛ ባንክ መበደር ለማይችሉ ወይም የባንክ ማስያዣ (ኮላተራል) ማቅረብ ለማይችሉ ኢንተርፕራይዞች፣ የካፒታል ዕቃዎችን በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታስቦ የተጀመረ ፕሮግራም ሆኖ ሳለ፣ አገልግሎቶ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በደንበኞች 20 በመቶ መዋጮ ከሕግ አግባብ ውጪ በሰርኩላር አስገዳጅ ድንጋጌ በመተግበር፣ በደንበኞች ላይ ቅራኔ መፍጠሩን፣ እንዲሁም መዋጮ መጠየቁ ከሊዝ ፋይናንሲንግ ፖሊሲና የአሠራር ፕሮሲጀር ስለመቃረኑ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡
ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)፣ የ20 በመቶ አስገዳጅ መዋጮን በተመለከተ በዋና ኦዲተር ሪፖርትም ሆነ በቋሚ ኮሚቴ አባላት የመነሳቱን ተገቢነት ተናግረዋል፡፡ የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎቱ በተጀመረበት ወቅት፣ በሥራ ላይ የነበረው የመጀመርያ መመርያ ተጠቃሚዎች መዋጮ የማይጠይቅ እንደነበር፣ ደንበኞች የዕዳ ክፍያና ብድርን በጊዜ ለመክፈል ፍላጎት ካለማሳየተቸው ጋር ተያይዞ፣ ባንኩ ያጋጠሙትን በርካታ ችግሮች ለመፍታት ታስቦ መመርያውን ለማሻሻል መገደዱን አስረድተዋል፡፡
‹‹ነገር ግን አሁን ይህንን መመርያ በመከለስ ቀድሞ በነበረው የአሠራር መመርያ መሠረት አዲስ መመርያ እያዘጋጀን ነው፡፡ በመሆኑም ደንበኞች ከዚህ በኋላ በሊዝ ፊይናንሲንግ ሲወስዱት ወይም ለሚከራዩት ምንም ዓይነት መዋጮ አይከፍሉም፤›› ብለዋል፡፡ ባንኩ ቀደም ሲል ባገጠሙት ዘርፈ ብዙ ችግሮችና በተለያዩ ምክንያቶች ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት አቋርጦት የነበረውን የሊዝ ፋይናንሲንግ ኪራይና ብድር፣ በቅርቡ መስጠት እንደሚጀምረም ፕሬዚዳንቱ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡
አገልግሎቱ ሲጀምር በሊዝ ፋይናሲንግ ለደንበኞች፣ ባንኩ ከውጭ ገበያ የሚያስገባቸውን ማሽኖች 80 በመቶ ወጪ የሚሸፈን ሆኖ፣ ደንበኞች 20 በመቶ የሚሆን የሥራ ማስኬጃ ካፒታል ማስመዘገብ ብቻ እንደሚጠበቅባቸው ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡ አክለውም ባንኩ ቀደም ሲል በነበረበት ብልሹ አሠራር በርካታ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ፣ ከሪፎርሙ በኋላ በአዲስ አመራርና ቦርድ ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያሉበትን የኦዲት ግኝቶች በገመገመበት ወቅት፣ ባንኩ ከሒደት ባለፈ ተጨባጭና አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ አለመሆኑን በመተቸት፣ አሠራሩን በአዳዲስ ዘዴዎች በመደገፍ የተሻለ የሥራ ክንዋኔ መተግበር የሚያስችል ዘዴዎችን እንዳዘረጋና ከፍተቶችን በፍጥነት ማሻሻል እንዳለበት አሳስቧል፡፡
የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት አዲስ አሠራር እንደመሆኑ፣ በተገልጋይ ኢንተርፕራይዞች፣ እንዲሁም በባለድርሻ አካላትና በባንኩ ሠራተኞች ጭምር ስለአሠራሩ በቂ ግንዛቤ ያለመኖሩ፣ በቅንጅት አሠራር ክፍተት ምክንያት አገልግሎቱን ሊያገኙ የሚገባቸው ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ኢንተርፕራይዞችን በመመልመል ሒደት፣ ችግር መኖሩና ወጥ የሆነ የአሠራር ፖሊሲ ባለመኖሩ፣ በተገልጋዮች ዘንድ ቅሬታ መፈጠሩ በቋሚ ኮሚቴው ተገልጿል፡፡
የካፒታል ዕቃዎች ለኢንተርፕራይዞቹ ከመቅረባቸው በፊት በሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች መዘጋጀታቸውን የማረጋገጥ ክፍተት መኖሩን፣ ከሚቀርቡት ማሽነሪዎች ውስጥ በዓይነት ያልተለዩና መሥፈርት የሌላቸው፣ ውስብስብ፣ ትልልቅና ለመትከል አስቸጋሪ የሆኑ በመኖራቸው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ማሽነሪዎቹን ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ ቢፈለግ ከቦታ ቦታ በቀላሉ ማንቀሳቀስ የማይቻል መሆኑ፣ ቋሚ ኮሚቴው ባቀረባቸው ጥያቄዎች እንደ ክፍተት ተነስተዋል፡፡
በተጨማሪም ለኢንተርፕራይዞች የሚቀርቡ የካፒታል ዕቃዎች ምዝገባ በሚመለከታቸው አካላት ስም በአግባቡ ሳይመዘገቡ ለተከራዮች የሚተላለፉ በመሆኑ፣ ከውጭ ለሚገቡ ዕቃዎች አስፈላጊውን የጉምሩክ ሰነድ በቅድሚያ ያለማዘጋጀትና ዕቃዎችን በወቅቱ ከወደብ የማንሳት ችግር በመኖሩ፣ ተገልጋዮች ለተጨማሪ ወጪና እንግልት መዳረጋቸው፣ እንዲሁም ዋና ብድርና የወለድ ክፍያዎች በወቅቱ ያለመሰብሰብ ችግሮች በባንኩ ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በተጨማሪም ባንኩ የግዥ መመርያ የሌለው መሆኑን፣ የግዥ መመርያን ያልተከተሉ ግዥዎች መፈጸማቸውና የመድን ዋስትና ያልተገባላቸው ዕቃዎች መኖራቸው፣ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመሥራት የጎላ ክፍተት መኖሩን፣ የኦዲት ግኝቱ እንደሚያሳይ በቀረቡት ጥያቄዎች አማካይነት ተጠቅሷል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው ክፍተት የነበረበት መሆኑን የጠቆሙት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት ክልሎችን ጨምሮ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ለተገልጋዮች፣ እንዲሁም ለባንኩ ሠተኞች ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጡ 2,500 አዳዲስና ነባር ኢንተርፕራይዞች በአደረጃጀት፣ በፋይናንስ፣ በአስተዳደርና በሌሎች ተዛማጅ የባንኩ አሠራሮች ላይ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውን በማሳያነት የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢንተርፕራይዞች የባንኩን አገልግሎት የሚያገኙት በአነስተኛ ወለድና ከማሽነሪያቸው ውጪ ሌላ ማስያዣና ዋስትና ሳይስፈለጋቸው መሆኑንም ግንዛቤ እየተሰጠ እንደሚገኝ ጨምረው አብራርተዋል፡፡
ቀደም ሲል በነበረው የባንኩ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ወጥ የሆነ አሠራር ያልነበረና የባንኩ ሠራተኞችም ጭምር የተሳተፉባቸው የተንዛዙና ብልሹ አሠራሮች የእንደነበሩ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ ከብልሹ አሠራሮች ጋር ግንኙነት በነበራቸው ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በተንዛዛ፣ በብልሹ አሠራርና በግንዛቤ ጉድለት ምክንያት ዋና ብድርና ወለድን በወቅቱ ያለመሰብሰብ ችግር በባንኩ አሠራር ላይ ሲታይ የነበረ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በተካሄደው የሪፎርምና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ፣ እንዲሁም በተደረገው ከፍተኛ ጥረት ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን በዋቢነት አንስተው፣ የተበላሸ የብድር መጠንም በፊት ከነበረበት ዝቅ እንዲል መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በተለያዩ የባንኩ አሠራሮች ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመሥራት ሒደቱን ለማሻሻል፣ ከክልሎችም ሆነ ከከተማ መስተዳድሮች፣ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዮሐንስ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የኦዲት ሪፖርቱን መሠረት በማድረግ የድርጊት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ፣ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያለ መላኩና የተወሰዱ የማስተካከያ ዕርምጃዎች ሪፖርት ያለ መደረጋቸው ክፍተት በመሆናቸው ወደፊት የሚስተካከሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው የክዋኔ ኦዲት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወይንሸት ገለሶ በበኩላቸው፣ ባንኩ የነበሩበትን ችግሮች በሪፎርም ውስጥ አካቶ ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፣ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በወቅቱ መላክ የነበረባቸው የድርጊት መርሐ ግብርና የማስተካከያ ዕርምጃ ሪፖርቶች ያለ መላካቸውን በመተቸት፣ ወደፊት መስተካከል የሚገባው ነው ብለዋል፡፡ ባንኩ እያከናወነ ያለው የሪፎርም ሥራ ፈጣን ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆን እንደሚገባው ወ/ሮ ወይንሸት አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ ባንኩ የሪፎርም እንቅስቃሴና ለለውጥ ያለው ፍላጎት አበረታች መሆኑን ቢገልጹም፣ የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት በአገሪቱ አዲስ አሠራር እንደ መሆኑና የታዩት አብዛኞቹ ክፍተቶችም ከግንዛቤና ከሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ ባለመሥራት የተፈጠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአሠራሩ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫና ተቀናጅቶ የመሥራት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
የባንኩ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ያለመሆኑን የኦዲት ግኝቱ የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ኦዲተሯ፣ ኢንተርፕራይዞችን ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ለማሸጋገርና ባንኩን ወጥ በሆነ ፖሊሲና የአሠራር መመርያ ለመምራት ያለው ዝግጁነት የበለጠ መጠናከር እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሐመድ የሱፍ ባንኩ ያሉበትን ችግሮች ለማስተካከል ጥረት እያደረገ መሆኑን በቀረበው ማብራሪያና ምላሽ ለመረዳት የተቻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ችግሮቹን በዳሰሳ ጥናት በማስደገፍ ለመቅረፍ ቀጣይ ጥረቶች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የባንኩን ዓላማ ለማሳካትም በተለይ ከክልሎች ጋር ያለውን አሠራር የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ በማሳሰብ፣ የተለያዩ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማሳለጥ፣ የባንኩን የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በየጊዜው የሚሰጠውን አስተያየት በግብዓትነት በመውሰድ፣ የባንኩን አሠራር ማጎልበት እንደሚገባ ሰብሳቢው በማጠቃለያ ንግግራቸው አሳስበዋል፡፡