Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአዲስ አበባ አስተዳደር ለዋሊያዎቹ 5.6 ሚሊዮን ብር ሸለመ

የአዲስ አበባ አስተዳደር ለዋሊያዎቹ 5.6 ሚሊዮን ብር ሸለመ

ቀን:

ዓለምን ከጥግ እስከ ጥግ ልክ እንደ ሙዚቃ ከሚያግባቡት አንዱ እግር ኳስ ነው፡፡ በፖለቲካዊ ዕይታ አልያም በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሳይገደብ ሁሉንም ሰብዓዊ ፍጡር ከጫፍ ጫፍ ማነቃቃት የሚችል የስሜት ማዕበል ያዘለ ክዋኔ ነው፡፡ እግር ኳስና የእግር ኳስ ጥበብ የእገሌ ነው የማይባል፣ በውበቱና በስሜቱ አውሮፓውያን ከአፍሪካውያን፣ እስያውያን ከአሜሪካውያን፣ ላቲኑን ከአውስትራሊያውያን፣ ነጩን ከጥቁር፣ ሴቱን ከወንዱ ወጣቱን ከዕድሜ ባለፀጋው የማጋመድ ኃይል ያለው በቡድናዊ ጥበብ የሚተወን ገፀ በረከት ነው፡፡

ስሜትን ፈንቅሎ የሚያወጣ አንዱን የሩቅ ዓለም ሰው ከሌላው የሩቅ ዓለም ሰው የሚያገናኝ፣ አንዳች መግነጢሳዊ ኃያልነት የተቸረው የሰው ልጆች በአንድ ቋንቋና ስሜት የሚግባቡበት ታላቅ ዘርፍ ነው፡፡ እግር ኳስ በእያንዳንዱ ግጥሚያ የሚስተዋለው ድርጊት ሁሉ ለዚህ ምስክር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚቀጥለው ዓመት በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 11 ምዕራፍ አፍሪካዊቷ ኃያል የእግር ኳስ አገር አይቬሪኮስት፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ምድብ ተደልድሎ ከምድቡ ዘጠኝ ነጥብ ይዞ 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የሚያበቃውን ትኬት ቆርጧል፡፡ በውጤቱ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በአንድ ቋንቋ ደስታቸውን ገለጹ፣ ተቃቀፉ፣ ዘለሉ፣ ደስታው እስካሁን እንደቀጠለ ነው፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከአንደኛው እስከ ሰባተኛውና  በአሥረኛው የአፍሪካ ዋንጫ  ለአኅጉራዊ መድረክ ሩቅ አልነበረም።  እንደ አለመታደል ሆኖ ዘመን ሲዘምን አብሮ መዘመን ሲገባው ተግዳሮቶቹ እየበዙ ሁሉም ነገር ‹‹ነበር›› እየተተካ ከሦስት አሠርታት በኋላ (ማለትም ከስምንት ዓመት በፊት) ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ መብቃቱ አይዘነጋም፡፡

ቡድኑ ከስምንት ዓመታት በኋላ ለአኅጉራዊ መድረክ መብቃቱን ተከትሎ ከመንግሥታዊ ተቋማት ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የተለያዩ አካላት ለዋሊያዎቹ  ድጋፍና አድናቆት እየሰጡ ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ ባለፈው ሐሙስ አዲስ አበባ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ጀምሮ በነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (/) ጨምሮ የስፖርት ኮሚሽን አመራሮች ኮሚሽነሩ አቶ ኤልያስ ሸኩርና ምክትላቸው አቶ ዱቤ ጅሎ እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም የስፖርቱ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይና ሌሎችም በመድረኩ የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡

ኃላፊዎቹ ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለሚኖረው ተሳትፎ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡           

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ለብሔራዊ ቡድኑ ማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ካበረከቱ መንግሥታዊ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይጠቀሳል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ላሳካው ውጤት መጋቢት 23 ቀን 2013 .. ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት 5.6 ሚሊዮን ብር ሸልሟል።
የገንዘብ ሽልማቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ 90 ሺሕ፣ ከቡድኑ ጋር ወደ አይቮሪኮስት ለተጓዙት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለእያንዳንዳቸው 40 ሺሕ ብር፣ ለቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ 200 ሺሕ ብር፣ ለረዳት አሠልጣኖች ለእያንዳንዳቸው 150 ሺሕ ብር፣ ለቋሚ ተጨዋቾች ለእያንዳንዳቸው 150 ሺሕ ብር እና ለተጠባባቂ ተጨዋቾች ለእያንዳንዳቸው 100 ሺሕ ብር እንዲከፋፈል መደረጉ ጭምር ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ባለፈው ዓርብ መጋቢት 24 ቀን  2013 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ለተጨዋቾቹና ለቡድኑ አባላት የገንዘብ ሽልማት ለመስጠት መወሰኑ ታውቋል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ‹‹በኢትዮጵያ የብሥራት ዜና ብርቅ በሆነበት በዚህ የጭንቀት ወቅት ብሔራዊ ቡድኑ ለስምንት ዓመት ከራቀበት የአፍሪካ መድረክ በድጋሚ መገኘት የቻለበትን ዜና በመላው ሕዝባችን ዘንድ የፈጠረውን ደስታ በማየቴ ፈጣሪን አመሠግናለሁ፤›› ብሎ ‹‹እኛ የስፖርት ሰዎች ነን የተሰባሰብነው ከተለያየ የአገሪቱ ክፍልና ሃይማኖት እንዲሁም የብሔር ስብጥር ጭምር ነው፡፡ በመካከላችን አንዳች መከፋፈል ሳይኖር በኢትዮጵያ ባንዲራ ሥር አንድ በመሆን ለጋራ ድል በሙያችን አገራችንን ለማገልገል ተሠልፈን ኢትዮጵያን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ አድርገናል፤›› በማለት በውጤቱና በተጨዋቾቹ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡
እንደ አሠልጣኝ ውበቱ፣ ሁሉም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍና ሙያ ተሰማርቶ ለአገሩ የበኩሉን ድርሻ ከተወጣ የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር እንደሚቻል ጭምር ተናግሯል፡፡

የቀድሞ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በበኩሉ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንድትመለስ የነበረንን ልባዊ ምኞትና ሐሳብ በተባበረው ኅብረታችሁና ጥንካሬያችሁ እንዲሳካ በማድረጋችሁ ትልቅ ምስጋና ይገባችኋል፤›› ብሎ ድሉ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ መነቃቃት የሚኖረው ፋይዳ እጅጉን የጎላ እንደሚሆን በትዊተር ገጹ አስፍሯል፡፡ በርካቶች ዋሊያዎቹ ባሳኩት ድል የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡  

ቡድኑ ከስምንት ዓመታት በኋላ ለአኅጉራዊ መድረክ መብቃቱ ስኬት ኖሮት እንዲዘልቅ እንጂ፣ እንዳለፉት ዓመታት ብቅ ብሎ የሚጠፋ እንዳይሆን ከወዲሁ መከናወን የሚገባውን ሁሉ  በዕቅድ መፈጸም  ይገባል የሚል አስተያየትም እየተሰነዘረ ነው፡፡                

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...