Saturday, October 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  አጭር መልዕክት ለኢትዮጵያን ሁሉ፡፡ ልብ ብላችሁ አንብቡት፡፡ ወገኖቼ የኢትዮጵያ በሽታ ምንድነው እንበል፡፡ የኢትዮጵያ የአሁኑ ጊዜ መርዘኛ በሽታ የተጠነሰሰውና የተሠራጨችው በትሕነግ (የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር) ነው፡፡ የዚህ ግንባር ዓላማ ምን ነበር? ስሙ እንደ ሚያመለክተው የትግራይን ሕዝብ ነፃ ማውጣት ነው፡፡ በእርግጥ የማታለል ዓላማን ይዞ፣ የዓለምንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ያልሆነውን ነኝ በማለት አታሎ፣ ነፃ ያወጣውን አገር ይዞ በነፃነት መኖር ነበረበት፡፡ ዓላማው የውሸት ስለነበረና ኢትዮጵያንም የሚጠብቅ ሌላ ኃይል ስላልነበረ ባዶ ሜዳ አግኝቶ ኢትዮጵያን እንደ ልቡ ጨፈረባት፣ በዘበዛት፡፡

  ደጋፊዎቹ የሆኑትን የትግራይ ወጣቶች፣ ሌሎች ሆዳሞችንና ምንም የማያውቁቱን ሁሉ የተትረፈረፈ ብር በማሸከም ለ30 ዓመታት የኢትዮጵያውንን አዕምሮ ጠምዝዞ እርስ በርስ የሚጋጩ፣ ማንነቴን የማታውቅ ኢትዮጵያ ሺሕ ቦታ ትበጣጠስ የሚሉ ሰዎችን ፈጥሮ ጊዜው ሲደርስ ቢጠፋም፣ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ከረጨው በሽታ እስካሁን ሙሉ ለሙሉ ሊፈወሱ አልቻሉም፡፡

  ትሕነግ ጠፋ ተብሎ የሚታመነው ልክ አይደለም፡፡ ጠንሳሾቹ ሹማምንት ጠፉ እንጂ ሐሳባቸው ገና አልጠፋም፡፡ ተማሪዎቻቸውና ተጠቃሚዎቻቸው አሁንም መርዛቸውን እየረጩ ነው፡፡ ሕዝቡ ጠንክሮ ኢትዮጵያን መጠበቅ አለበት፡፡ ከምን?  ከትሕነግ መጥፎ ዓላማ፡፡

  ዓላማው በዝርዝር ሲታይ ምን ነበር? እኔ ልረዳው እንደ ቻልኩት እያንዳንዱ በኢትዮጵያዊነት የሚታወቀው ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ አሁን በስፋት ይዞ  የሚኖርበትን የኢትዮጵያ ምድር፣ የራሱን ቋንቋ የሚናገሩትን ሰዎቸ ብቻ ሰብስቦ፣ የራሱን የውስጥ አስተዳደር በነፃነት በማቋቋም ራሱን ችሎ ይኑር የሚል ነው፡፡ ሁሉም እንዲህ የራሱን ክልል መሥርቶ የሚኖር ከሆነ፣ ኢትዮጵያ እንዴት ትኖራለች? ለሚለው ጥያቄ ትሕነግ ሲመልስ በስምምነት የፌዴራል መንግሥት በመመሥረት ነው ይላል፡፡ ግን የፌዴራል መንግሥቱን የሚመራው ማነው? በምርጫ ሊሆን ነው፡፡ ምርጫውን ማነው የሚያካሂደው? ማነው የሚያሸንፈው? በትሕነግ ዘመን ያው አድራጊ ፈጣሪው ትሕነግ ነዋ! ሌላማ ካሸነፈ ይባረራል፣ ይታሰራል፣ ደጋፊዎቹ በስናይፐር ይገደላሉ፡፡

  እንዲያው ይሁን ቢባል ግን ይህ የክልል ዓላማ በተግባር በትክክል ሊውል ይችላል? እኔ አፌን ሞልቼ አይችልም ነው የምለው፡፡ ለምን? መልሱ ቀላል ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የሚመሠረት መንግሥት አይሠራም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስካሁን ተሰበጣጥሮ፣ ተጋብቶ፣ ከቦታ ቦታ በነፃነት ያለ መሳቀቅና ያለ መጠራጠር ተዘዋውሮ፣ እንደ ምንም አንዱ የሌላውን ቋንቋ ለመናገር እየሞከረና እየተሳሳቀ በአንድ ሉዓላዊ አገር ዜግነት ኮርቶ የሚኖር ሕዝብ ነበር፡፡ አሁን እንዴት ይበታተን? እንዴት በየበረቱ እየተከለለ ይኑር? በዚህስ የሚመጣ ነፃነት ምን ዓይነት ነፃነት ነው?

  አሁን ከዚህ ማጥ እንዴት ወጥተን፣ የትሕነግን መርዝ  አርክሰን፣ ደኅንነት ተሰምቶን በሰላም እንኑር ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ መልሱን ለመስጠት ልሞክር፡፡ አንደኛ በእግዚአብሔር ፈቃድ ያለ አብዮት በሰላም ለውጥ መጥቷል፡፡ የለውጡም ዓላማ ክልል ጠፍቶ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በነፃነት ትኑር የሚለው ጥሩ ሐሳብ  ነው፡፡ ይህን ሐሳብ ዕውን ለማድረግ የተቻለው በአማራና በኦሮሞ ወጣቶች የተባበረ ትግልና በከፈሉት ደም ነው፡፡ ደም ጠጥቶ የሚወፍረው ትሕነግ ግን ተወራጨ፡፡ በለውጡ ሒደት የተፈጠረውን የብልፅግና ፓርቲ አልቀበልም አለ፡፡ ሲያስበው የሚገፋው ሀብት፣ በትግራይ ስም እየተበደረ ብድሩን በኢትዮጵያ ላይ እየጫነ በመንፈላሰስ በስድነት መኖሩ ስለቀረበት ወደ እዚያው ወደ ጀመረው ትሕነግነቱ ተመለሰ፡፡ የተሻሻለውን አዲሱን ትሕነግን በአዲስ መልክ ጀመረው፡፡ ‹‹የዱሮ መስሎሻል፣ ግቢና ሞክሪው ምስጥ ያነክትሻል›› አለ የአገሬ ሰው፡፡ ይኸው የእኛ መድፍ ጥይት ዋሻ አነከተው፡፡

  ሁለተኛ አሁንስ የትሕነግ መርዝ ጠፍቷል? እንዴት ሆኖ? እንዲሁ በቀላሉ?  መርዝ እኮ ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ሲመሠረት ትሕነግ አልደመርም አለ፡፡ እንቢ ምን ታመጣላችሁ አለ፡፡ የሚመጣበት መጣበት፣ ግሩም፡፡ አሁን ብልፅግና ፓርቲ ቀረ፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ ይህ ፓርቲ ዕውን ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ነው? እኔ በምንም ምንም መንገድ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ነገር በሩቁ ይታየኛል፡፡ ብልፅግና ውስጥ ትሕነግ የዘራው መርዝ አለ፡፡ ምልክቱ ምንድነው ለሚለው ጥያቄ ትንሽ ማለት ይቻላል፡፡ ትዕዛዞች ከአንድ ማዕከል የሚወጡ አይመስልም፡፡ ለምሳሌ ቀላል ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡ የዘንድሮ ምርጫ ምዝገባ የሚጀመረው መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው ተባለ፡፡ ምዝገባው የት ነው? መዝጋቢው ማነው? ምዝገባው በስንት ሰዓት ይጀምራል? እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልስ እስካሁን የለም፡፡

  ሌላም ምልክቶች አሉ፡፡ ኦነግ ሸኔ ማነው? ድሮ የሚንቀሳቀሰው በወለጋ አካባቢ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ አጣዬ እንዴት ሊያልፍ ቻለ? ለምን እሳት በየቦታው ይቀጣጠላል? ለምን አገሪቱን የሚበጠብጥ ኃይል ዝም ይባላል? ይህ ሁሉ ጥርጣሬን ያመጣል፡፡ ዶ/ር ዓብይ የሚመሩት አንድ ለኢትዮጵያ የቆመ ፓርቲ ብቻ አይመስልም፡፡ የትሕነግ የክልል በሽታ ተሸካሚዎች በአጠገባቸው ሆነው የሚሠሩ ያሉ ይመስላሉ፡፡ ሌላም ችግር ፈጣሪ አይጠፋም ይሆናል፡፡

  ይህ ሁሉ ተጣርቶ ብልፅግና ለኢትዮጵያ የቆመ፣ ጠንካራ የሆነ፣ ውስጡን ያጠራ፣ አንድ አቋም የያዘና ለአንዲት ኢትዮጵያ የቆመ ፓርቲ ቢሆን ይመረጣል፡፡ አረሞች ይነቃቀሉ፡፡ አረሙ ተነቃቅሎ፣ ዶ/ር ዓብይ ብርታት አግኝተው፣ ፓርቲያቸው አንድ ኢትዮጵያን በማዳን መንፈስ መምራት ቢችል አገራችን ፈውስ አገኘች ለማለት ይቻላል፡፡ ምርጫው በሰላምና በሥርዓት ይካሄድ፣ ሰው እንሁን፣ መርዛችንን ከደማችን እናስወግድ የሚለውን መርህ ብንከተል ጥሩና ገንቢ ሐሳብ ይመስላል፡፡

  (ደበላ ሐሩማ፣ ከአዲስ አበባ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img