Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የንግድ ፈቃድ ብቃት ማረጋገጫ አሠራር ይፈተሽ

የንግድ አሠራርን ለማዘመን ብሎም የተቀላጠፈ አገልግሎትን ለማዳበር ብዙ አሠራሮቻችን ማስተካከል ይጠበቅብናል፡፡ አድምተን ልንሠራቸው የሚገቡ ብዙ ሥራዎችም ይቀሩናል፡፡ ዛሬም ከተተበተበው ቢሮክራሲ አልወጣንም፡፡ ለዓመታት ስንጠቀምባቸው የነበሩ አሠራሮቻችን አልተቀየሩም፡፡ አሠራሮቻችን ብቻ ሳይሆን ብዙዎች ወንበሩን የያዙ አስፈጻሚዎች አሰልቺ አሠራራቸውን እየጫኑብን ነው፡፡

በኢትዮጵያ አንድ ችግር ሆኖ ለመለወጥ ያቃተ ጉዳይ ቢኖር ይኼው ተገልጋይን በአግባቡ የማገልገል ልማዱ ደብዛዛ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም አለፍ ብሎ ዘመኑን የዋጀ አሠራር መተግበር አለመቻል ነው፡፡ በቀላሉ ልንፈታውና በመልካም ልናራምዳቸው የምንችላቸውን ሥራዎች አወሳስቦ በማሰነካከልም ቢሮክራሲያችን ይታወቃል፡፡ በደቂቃ መወሰን የሚቻልን ጉዳይ ጠረጴዛ ላይ ጥሎ ነገር የሚያመነችክም ሞልቷል፡፡ እንዲህ በማድረግ አገር ምን ያህል እንደምትጎተት ለመረዳት አያዳግትም፡፡

ከአገር አንፃር በተለይ ኢትዮጵያ በዓለም በአሉታዊ ከምትጠቀስባቸው መገለጫዎች ውስጥ ከንግድ አሠራር ቅልጥፍናና በቀላሉ ቢዝነስን ለመተግበር በሚወጣው የምዘና ውጤት ያለንበት ደረጃ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ለመጀመር ምን ያህል የተመቻቸች ነች? ሲባልና ሲመዘን በደረጃ ሠንጠረዙ ላይ ያለውን ውጤት ለማየት ከወደ መጨረሻ መጀመር ሥራ ያቀላል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ስንል ችግሩ የራሳችን ስለመሆኑ አውቆ ለመቀበልና ለማስተካከል ሳይጣር በመቅረቱ ነው፡፡

ይህ ጉዳይ ታስቦበትና ሻሻል ተብሎ ከሁለት ዓመታት ወዲህ የተሠሩ ሥራዎች በተለይ ከንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ጋር የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የታየው ተነሳሽነት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ አሠራሩን ለማስተካከል የተደረገው ጥረትና የተገኘው ውጤት አበረታች ቢሆንም፣ አሁንም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በተለይ አንድን ንግድ ለመጀመር በአስገዳጅነት የሚቀርበው የብቃት ማረጋገጫ ጥያቄ ምክንያታዊ አለመሆኑ በብዙ መንገድ የሚገለጽ ነው፡፡

በእርግጥም የብቃት ማረጋገጫ ከሚጠየቅባቸው 330 ከሚሆኑ የቢዝነስ ዘርፎች ውስጥ አብዛኛዎቹ እንዲህ ያለው ጥያቄ ሊቀርብባቸው አይገቡም ተብሎ 52 ብቻ ቀርተዋል፡፡

ከእነዚህ 52 ዘርፎች ውስጥም ብዙዎቹ የብቃት ማረጋገጫ የሚጠየቅባቸው ሊሆኑ አይገባም ተብሎ እየተሞገተባቸው ነው፡፡፡ ዳግም በተደረገ ፍተሻ ለእነዚህ የብቃት ማረጋገጫ መጠየቅ የለበትም ተብሎ ሙያዊ አስተያየት ጭምር የተሰጠባቸው ቢሆንም፣ ጉዳዩን በቶሎ ዓይቶ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጥ በመጥፋቱ ብዙ ቢዝነሶች ኢኮኖሚውን እንዳይቀላቀሉ ብሎም እንዳይደግፉ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡

በዚህ ወቅት ቢዝነሱ ያለ ችግር እንዲገባ ተደርጎ ለጥቂቶችም ቢሆን የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር ምክንያት መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፡፡ በአጠቃላይ ብዙም ትርጉም በሌለው የ‹‹ብቃት ማረጋገጫ አምጡ ስም›› ፈቃድ አይሰጥም መባሉ ቢዝነሶቹ ኢኮኖሚው ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ እንቅፋት ሲሆን እያየን ነው፡፡

ችግሩ በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ በዓለም ፊት ምቹ የቢዝነስ ድባብ በመፍጠር ዓለም ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ደረጃ እንዳይሻሻል እንቅፋት ሆኗል፡፡

የተሻለ ደረጃ ለማግኘት ታስቦ የተጀመረውን ሪፎርም በተወሰነ ደረጃ ሰንካላ ያደርገዋል ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ያሉ የምዘና ዓለም አቀፍ መረጃዎች ሌሎችን ለመሳብ ጭምር የሚጠቅሙ በመሆኑ እንደ ዋዛ መታለፍ የለበትም፡፡

በአንድ በኩል 62 ዓመታት አብሮን ያረጀው የንግድ ሕግ ሲሻሻል፣ ለቢዝነስ ሥራዎች እንቅፋት የሆኑ አሠራሮች እንዲቃለሉ ያደርጋል ተብሎ ተመስገን ሲባል፣ በሌላ በኩል አንድ ቢዝነስ ለመጀመር ለቢዝነሱ ምንም ፋይዳ የሌለው ነገር አሟሉ፣ ይህንን ካላሟላችሁ ፈቃድ አታገኙም መባሉ ያስተዛዝባል፡፡

ለአገርም ለሕዝብም ደኅንነት ሲባል በአግባቡ የብቃት ማረጋገጫ የሚያስፈልጋቸው የቢዝነስ ዓይነቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ግን ማረጋገጫውን ለማግኘት የሚታይባቸው ፍዳ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ሌላው አስተዛዛቢ ጉዳይ አንድ ቢዝነስ ለመጀመር ብቃት አረጋጋጭ የሆኑ ተቋማት ለተመሳሳይ ቢዝነስ የተለያዩ ነገሮችን አሟሉ እየተባሉ መሆኑ ነው፡፡

የብቃት ማረጋገጥ ጉዳይ አገልግሎት ፈላጊውን ለሙስና ተጋላጭ እያደረገውና የተገልጋዮች መማረሪያ እየሆነ መምጣቱን መጠቆም አግባብ ነው፡፡ አሁን ዶሮ ለማርባትና እንቁላል አምርቶ ለመሸጥ ለአንዱ የሚፈቀድበት ለሌላው መሥፈርቱ የሚበዛበት ምክንያት ምንድነው?

ሌላው ጉዳይ ደግሞ አንድ ቢዝነስ ለኅብረተሰቡ አደጋ እስካልሆነ ድረስ፣ ሰው ባለው አቅም ቢሠራና ገበያና አገልግሎቱ ቢዳኘው ምን ችግር ይኖረዋል? ችግር ካለበት ገበያው ይጥለዋል፡፡ ችግር ካለበት ሕግ ይዳኘዋል፣ ካልሆነ ለትንሹም ለትልቁም ነገር የብቃት ማረጋገጫ እየተጠየቀ ቢዝነሶቻችንን ባናስተጓጉል ይመረጣል፡፡

ለሥራ የተዘረጋን እጅ፣ እጅ ስሞ ማስገባት እንጂ በሰበብ አስባቡ ማንገላታት ለአገር አይጠቅምምና የተሻለ አሳቢና ቀልጠፋ እንሁን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት