Saturday, May 25, 2024

መጪው ምርጫ የተደቀኑበት የፈተና ጋራዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ አንድ ቃል የገቡለት ጉዳይ ቢኖር፣ በምርጫ አማካይነት የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበት ሥርዓት ለመፍጠር በቁርጠኝነት መሥራት ነው፡፡ በዚህም አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲ የሚያመራ መንገድ መቀየስ እንደሚቻል እንደሚያምኑም ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በእሳቸው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድን እንዲመሩ የተሾሙት የቀድሞ ፖለቲከኛና የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳም በተመሳሳይ፣ እስካሁን ከተካሄዱ አምስት ምርጫዎች የተለየና ኅብረተሰቡ በምርጫ ላይ ያለውን እምነት እንዲመልስ የሚያስችል ምርጫ ለማከናወን እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

በተደጋጋሚ የተገለጹት እነዚህ አባባሎች በርካቶች ተስፋ እንዲሰንቁ ያደረጉ ሲሆን፣ በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥርም እንዲታይ አድርጓል፡፡ በኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. የፖለቲካ ፓርቲዎች ባዘጋጁት የምርጫ የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 107 ሲሆን፣ በሒደትም ይኼ ቁጥር ከ160 በላይ ደርሶ ነበር፡፡

ይሁንና ከእነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በቦርዱ ማሟላት ያሉባቸውን ግዴታዎች ተጠይቀው በማሟላት በፖለቲካ ፓርቲነት ሊመዘገቡ የቻሉት 53 ብቻ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ  የምርጫ፣ የፖለቲካ  ፓርቲዎች  ምዝገባና የምርጫ  ሥነ ምግባር አዋጅ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ የ10,000 መሥራች አባላት ፊርማ፣ እንዲሁም የክልል ፓርቲዎች የ4,000 መሥራች አባላት ፊርማ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይኼንን አሟልተው ከተመዘገቡ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ደግሞ ለምርጫ የሚወዳደሩት 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ 47 ፓርቲዎች 8,209 ዕጩዎችን ለክልል ምክር ቤቶችና ለፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስመዘገቡ ሲሆን፣ በተጨማሪም 125 ዕጩዎች ለተለያዩ ምክር ቤቶች በግል ይወዳደራሉ፡፡

ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲከናወን ቀን የተቆረጠለት ይኼ ምርጫ ግን ከመነሻው ጀምሮ የመጣበት መንገድ ጎርበጥባጣ ነበር፡፡ በዕጩዎች ምዝገባ ወቅትና በምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር ምክንያት የታዩ የፀጥታ ችግሮችና እሰጥ አገባዎች፣ በተለይ እስከ ምርጫው ቀንና እስከ ውጤት ገለጻ ድረስ ሊዘልቁ እንደሚችሉ በርካቶች ይስማማሉ፡፡

በቅርቡ አዲስ ወግ በተባለውና ተከታታይ የፖሊሲ ውይይቶችን በሚያስተናግደው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዝግጅት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ በተለይ የፀጥታ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸውና ሥጋታቸው እሳቸው ቅጥረኞች የሚሏቸው ኃይሎች በመራጮችና በአስመራጮች ላይ ጥቃት በመፈጸም ሕዝቡ ወጥቶ ለመምረጥ ደኅንነት እንዳይሰማው ለማድረግ የሚሞክሩ መሆኑን ነው፡፡

‹‹ወደ እኛ [አገር] ሲመጣ [ምርጫን] ችግር የሚያደርገው በጣም ብዙ ኃይሎች ቋምጠው የሚጠብቁት ይኼንን ምርጫ ነው፡፡ በዚህ ምርጫ አማካይነት ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር መፍጠር ይቻላል ብለው ብዙ ሀብት የሚያፈስሱ አገሮች አሉ፡፡ እንግዲህ ይኼንን ችግር በደንብ የሚያዩና የሚገነዘቡ ሰዎች ምርጫው አያስፈልግም፣ ምርጫው ቅንጦት ነው የሚሉ ሰዎች ዝም ብለው ሳይሆን ክርክራቸው ችግሩን በማየት የኢትዮጵያን ቀጣይትና የኢትዮጵያን ህልውና ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎች ይጨነቃሉ፡፡ ምንድነው የምናገኘው በዚህ ምርጫ? ብዙ አገሮች ሊያጠፏት የሚፈልጓትን አገር በውስጥ ሳንግባባ ምርጫ ብለን ከነበረው ሁኔታ የዘቀጠ ሁኔታ እንዳይፈጠር ብለው ሠግተው እርሱን አጉልተው ባይኖር ይላሉ፡፡ በሌላ መንገድ ደግሞ ምርጫው አለመደረጉ መልሶ ለመራበሽ ለመበጣበጥ እንደ መነሻ የሚጠቀሙ ኃይሎች ስላሉ፣ የመንግሥት ቅቡልነትን የሚያሳጡ፣ ሰብሰብ ብለን ወደ ልማት፣ ወደ ብልፅግና እንዳናተኩር የሚያደርጉ ጉዳዮች ስላሉ ምርጫን ማድረግ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ቦታዎች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እያንዳንዱ ዜጋ ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት መሆኑን አውቆ ከዛሬ ጀምሮ ማንን ለምን እንደሚመርጥ እያሰበ ቆይቶ (ጊዜ ስላለው)፣ ከመረጠ በኋላ ግን ድንጋይ የሚወረወር ከሆነ በጋራ መቆም አለበት፡፡ በነገራችን ላይ እኔ በከተማ ውስጥ የድንጋይ ሠልፍ ዓይነት ነገር ብዙ አልሠጋም በአሁኑ ምርጫ፡፡ እንደዚያ ሥጋት የለኝም፡፡ ምክንያቱም ለሁሉም ታዛቢ ተፈቅዷል፣ ከሞላ ጎደል በምርጫው ብልሽት እንዳይኖር ጥረት ይደረጋል፡፡ የሚያስፈራኝ ቅጥረኞች፣ የተገዙ ሰዎች፣ ራሳቸውን ከሕዝብ ጋር አመሳስለው አንዳንድ ቦታ መራጭን አስመራጭን በማጥቃት ጥፋት እንዳያስከትሉ ነው፡፡ በ97 የገጠመንን ችግር ከአሁኑ ጋር እንዳታመሳክሩት፡፡ 97 ድምፅ የሚሰርቅ፣ ኮሮጆ የሚሰርቅ መንግሥት፣ ኮሮጆ የሚሰርቅ ፖሊስ፣ ኮሮጆ የሚሰርቅ አስፈጻሚና አይሰረቅብኝ የሚል ሰው፣ የሚሉ ሕዝቦች ናቸው የተጋጩት፡፡ እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ መንግሥት ኮሮጆ አይሰርቅም፡፡ አሁን ችግር የሚያጋጥመን ኮሮጆ መሰረቅ ብቻ ሳይሆን፣ ወጥቶ መምረጥ የደኅንነት ስሜት ዜጎች እንዳይሰማቸው ማድረግ የሚፈልጉ የተገዙ፣ በሽፍታነት የሚሠሩ፣ ዘር እየመረጡ የሚገድሉ፣ የኢትዮጵያን አንድነትና ህልውና የማይፈልጉ ኃይሎች ግን ታጥቀው የደንብ ልብስ ለብሰው ስለማናገኛቸው፣ ተመሳስለው ስለሆነ የምናገኛቸው ጥፋት ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች መከላከል የምንችለው እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ከወሰደ ብቻ ነው፡፡ መረጃ ከሰጠ፣ ሁኔታውን ከሚመለከተው አካል ካስታወቀ፣ ከወዲሁ እየገመትን፣ እያወቅን፣ ቦታ እየለየን ከሄድን የጥፋት ኃይሎችና የተቀጠሩ ሰዎች ጥፋት እንዳያመጡ ማድረግ ይቻላል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያለ የሥጋት መግለጫ በመንግሥት ይፋ ሲደረግ የመጀመርያው ሲሆን፣ ይኼም የደኅንነት ሥጋት ምርጫውን ሊያስታጉል እንደሚችል ከአሁን ቀደም በተለያዩ መድረኮች አስተያየታቸውን የለገሱ ፖለቲከኞችና ምሁራን አስገንዝበው ነበር፡፡ ለአብነት ያህልም በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የመጀመርያው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ከመሰረዙ አስቀድሞ ይደረጉ በነበሩ ውይይቶች ላይ ሐሳብ ይሰነዝሩ የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ልደቱ አያሌው፣ አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ስለምርጫ ለመነጋገር የሚያስችል አይደለም ሲሉ ይደመጡ ነበር፡፡ ይልቁንም የምርጫ መደላድል ለመፍጠር የሚያስችል ብሔራዊ ውይይት ማካሔድን ጨምሮ የሽግግር መንግሥት ማቋቋምን ያካተቱ ምክረ ሐሳቦችን ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የዜጎች ደኅንነት ይቅደም ሲሉም ነበር፡፡

በተመሳሳይ እንዲህ ያለ ሐሳብ ያቀርቡ የነበሩት ዕውቁ ፖለቲከኛና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር መረራ ጉዲና (ፐሮፌሰር) አገሪቱ ወደ ብሔራዊ መግባባት የሚያመሩ ብሔራዊ ውይይቶች መደረግ አለባቸው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ሆኖም ግን እንዲህ ያሉ ውይይቶችን ለማስጀመር የነበሩ ጥረቶች በራሳቸው በችግር የታጀሉ የነበሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የውዝግብ መነሻ ሲሆኑም ተስተውሏል፡፡ ለዚህ እንደ ማሳያ ሊቀርብ የሚችለው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የነበረውና መረራ (ፕሮፌሰር) ራሳቸው የመወያያ ወረቀት ያቀረቡበት ውይይት ላይ፣ የኢትዮጵያ ታሪክን የተመለከተ ሐሳብ አቅርበው ከመንግሥትና ከሌሎች አካላት ጭምር ወቀሳና ትችት ያስከተለባቸውን ውዝግብ አስነስቶ ነበር፡፡

እነዚህ ውይይቶች ተደርገው የአገር ግንባታ ችግሮች ልየታና የወደፊት መንገድ መስመር ቅየሳ ሳይካሄድ በመቆየቱ፣ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት ፓርቲ ውስጥ ባሉ ክፍፍሎች ሳቢያ አገሪቱ እሳቸው ከመምጣታቸው አስቀድሞ የነበሩ ችግሮችን ተሸክማ እንድትጓዝ አድርገዋል፡፡

በተለያዩ ቦታዎች እየተደጋገሙ የመጡ የንፁኃን ግድያዎች፣ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃቶች፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችና ጥቃቶች፣ እንዲሁም የሰዎች ስደትና መፈናቀል በየሳምንቱ የሚሰማ ክስተት ሆኗል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን እስከ ደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ድረስ፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እስከ አማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ በሁሉም አቅጣጫዎች የሕዝብ ደም መፍሰሱ አሌ የማይባል ሀቅ ነው፡፡ በአማራ ክልል አጣዬ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈውን የታጠቁ ኃይሎ ጥቃት ተከትሎ የነበረው ጩኸት ሳይረግብ፣ በምዕራብ ወለጋ ሰሞኑን ተመሳሳይ ጥቃት ተሰንዝሮ ንፁኃን ለሞት ተዳርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለምርጫው ተብሎ የተቋቋመውና በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የምርጫ ፀጥታ ግብረ ኃይል አባል ቢሆንም ቅሉ፣ እነዚህ ግጭቶች መከሰታቸውንም ሆነ የመከሰት ዕድላቸውን የሚተነብይ የደኅንነት ትንታኔ ለምርጫ ቦርድ እንደማይቀርብለት በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረው ነበር፡፡

የደኅንነትና የፀጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ ከመንግሥት አካላት ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ እንደማይሰጣቸው የተናገሩት ሰብሳቢዋ፣ ‹‹ይህ ትክክል አይደለም፣ ሌሎችም ተቋማት እንዲህ ያደርጋሉ፡፡ ወይ ሥራውን አይሠሩትም፣ ከሠሩት ደግሞ የእኛን ተቋም እንደ የውጭ አካል ይቆጥሩታል፡፡ ተቋሙ ከእነሱ ውጪ ነው፡፡ ነገር ግን መታገዝ ያለበት ነው፡፡ የማገዝ ግዴታም አለባቸው፡፡ ከዚያ አንፃር ያገኘነው ምላሽ በጣም የሚያረካ አይደለም፡፡ ውሳኔያችንንም አዘግይቶብናል፡፡ በተመሳሳይ ከፌዴራል መሥሪያ ቤቶችም የምንፈልጋቸው መረጃዎች እንደዚያው ተደራጅተው እየመጡ አይደለም፡፡ በተለይ የሕግ ማስከበርና የፀጥታን ሁኔታ በተመለከተ፤›› ሲሉም ተችተዋል፡፡

ከመንግሥት አካላት ማግኘት ያለበትን ድጋፍ በአግባቡ እያላገኘ የሚገኘው ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማከናወን በተለይ የፀጥታ ጉዳዮች ፈተና የሚሆኑበት ሲሆን፣ አዳዲስ ከሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ባለፈ ከአሁን ቀደም የነበሩና እስካሁንም መፍትሔ ያላገኙ እንደ መተከል ያሉ ግጭቶች የፈተናው አንድ አካል ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ አመንቴ ግሺ እንደሚሉት፣ ሕዝቡ በደረሰበት ሰቆቃና በሚገኝበት የስደት ጣቢያ ምክንያት ካርድ ወስዶ ለመምረጥ ይቅርና ወደ አካባቢው ተመልሶ ኑሮውን ዳግም ለመመሥረት የሥነ ልቡና ዝግጁነት የለውም፡፡ ስለዚህም ሕዝቡ ምርጫ እንዲያደርግ ከመገፋፋት ይልቅ፣ ጊዜ ተሰጥቶት ሲረጋጋ የሚከናወንበት መንገድ ቢመቻች ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፀጥታ ችግር ምንጭ ሊሆን እንደሚች ሥጋት ያጠላበት በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መካከል የታየው ውዝግብ ሲሆን፣ ካሁን ቀደም የቆየ የወሰን ጥያቄ ቢኖራቸውም የምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያዎችን ሥፍራ ይፋ ሲያደርግ እሰጥ አገባው ተመልሶ እንዲያንሰራር ሆኗል፡፡

ይኼንንም ተከትሎ ቦርዱ ከስድስት ዓመታት በፊት ለአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ጥቅም ላይ የዋለው የምርጫ ካርታ ለውጥ እንዳላደረገ በማስታወቅ ይፋ ያደረገውን የምርጫ ጣቢያ ዝርዝር በመቃወም የአፋር ክልል ለቦርዱ ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን፣ ቦርዱም የአፋር ክልል ያነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ክርክር በሚያስነሱት በጋላእቶ/አዳይሌ፣ በአዳይቱ/አዳይቱ፣ በቴውኦ/አላሌ፣ በጉርሙዳሊ/ዳንሌሄላይ፣ በኡንዳፎኦ/ኡንዱፎ፣ በጋዳማይቱ/ጋርባኢሴ፣ በአፍዓሶ/አፉአሴ፣ እንዲሁም በባላእቲ ጎና/መደኒ ቀበሌዎች ሊመሠረቱ የታሰቡ የምርጫ ጣቢያዎች አንዳይቋቋሙና መራጮች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ሄደው እንዲመርጡ ወስኗል፡፡

ይሁንና የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ይኼ ውሳኔ እስካልታጠፈ ድረስ በምርጫው ለመሳተፍ እንደማይፈቅዱ አስታውቀው ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ የጻፉ ሲሆን፣ ቦርዱ በምላሹ በምርጫ የሚሳተፈው የክልሉ መንግሥት ሳይሆን ፓርቲዎች በመሆናቸው የክልሉ መንግሥት በፕሬዚዳንቱ ተፈርሞ በወጣው ደብዳቤ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለውና በሕግ የተቀመጠውን የመተባበር ግዴታውን ብቻ እንደ መንግሥት እንዲወጣ ሲል ጠይቋል፡፡

ሆኖም የሁለቱ ክልልሎች ውዝግቦች በዚህ የሚያበቁ እንዳልሆኑ፣ በምርጫ ሰላምና ደኅንነት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ሥጋት ያላቸው አልጠፉም፡፡

እነዚህንና መሰል የፀጥታ ሥጋቶች ከፊቱ የተደቀኑበት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በውጣ ውረዶች ታጅቦ የዕጩዎች ምዝገባው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጀመረው የመራጮች ምዝገባ ላይም ተመሳሳይ ችግሮች ሊታዩ እንደሚችሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥጋት ይጠቁማል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -