ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን በግል ችሎት እንዲያሰማ ትዕዛዝ ተሰጠ
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት 3፡30 ሰዓት አካባቢ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ከተገደለው የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ የተከሰሱት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ (24 ተጠርጣሪዎች)፣ ዓቃቤ ሕግ የቆጠረባቸው ምስክሮች ስም ዝርዝር እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ተደረገ፡፡ በተመሳሳይ ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹ በዝግ ችሎት እንዲሰሙለት ያቀረበው ጥያቄም ውድቅ ተደርጓል፡፡
ጉዳዩን እያየው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ማክሰኞ መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ብይን እንዳስታወቀው፣ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባና አቶ ሃምዛ አዳነን ጨምሮ 24 ተከሳሾች (ሁለቱ በሌሉበት) ዓቃቤ ሕግ የቆጠረባቸውን 146 ምስክሮች ስም ዝርዝር እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን አስታውሷል፡፡ ነገር ግን የምስክሮችን ስም ዝርዝር ለደኅንነታቸው ጥበቃ ሲባል ማንነታቸው እንደማይገለጽ በማሳወቅ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
በተመሳሳይ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ለምስክሮቹ ደኅንነት በማለት በምስክር ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 4(1ሸ እና ቀ) ድንጋጌ መሠረት፣ ምስክርነታቸውን በዝግ ችሎት እንዲሰጡ መጠየቁን ፍርድ ቤቱ በብይኑ አስታውሷል፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ አዋጁንና አንቀጹን ከመጥቀስ ባለፈ በምስክሮቹ ላይ ይደርሳል ብሎ ስለሠጋበት ጉዳት በማስረጃ የተደገፈ ነገር ስላላቀረበ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ፣ ምስክሮቹን በግልጽ ችሎት እንዲያሳይ ብይን ሰጥቷል፡፡ ምስክሮቹንም ለመስማት ለሚያዚያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡