Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለተቋማት ግንባታ ትኩረት የማይሰጥ አሠራር አያዛልቅም!

መንግሥት የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት ተቋማዊና በሕግ የተደገፉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ የመንግሥት ፕሮጀክት በጀቱ በመንግሥት ይደገፍ ወይም ከሌላ ምንጭ ይገኝ፣ እያንዳንዷ ሳንቲም በግልጽነት ለምን ዓላማ እንደዋለች መታወቅ አለባት፡፡ እያንዳንዱ መንግሥታዊ ተቋም በአዋጅ ሥልጣንና ኃላፊነቱ እንደተደነገገው ሁሉ፣ ተሿሚዎችም ተቋማቱን የሚመሩበት ሕጋዊ ሥልጣንና ኃላፊነት አላቸው፡፡ ማንኛውም ተሿሚ በሕግ ከተሰጠው የሥልጣን ገደብ አልፎ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጽም፣ ድርጊቱ በሥልጣን መባለግ ተብሎ ያስከስሳል፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 ማንኛውም የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት፣ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት እንደሚችልና ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን የሕግ የበላይነት ወደ ጎን በመገፋቱና በሕጋዊነት ውስጥ ውሎ ማደር ባለመፈለጉ ብቻ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙ ግፎች ከመጠን በላይ ግዙፍ ናቸው፡፡ ለተቋማት ግንባታና ለተገቢው ሥራ ተገቢው ሰው የሚለው መርህ ተጥሶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ አሁንም ከዚያ አዙሪት ውስጥ መውጣት የተቻለ አይመስልም፡፡ ሕግ አውጭው ፓርላማም ጠንከር ብሎ የአስፈጻሚውን አካል እንቅስቃሴ መቆጣጠርና የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ ሲገባው፣ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ ባለመሆኑ ከተቋማት አሠራር ይልቅ ግለሰባዊ የተክለ ሰውነት ግንባታ ላይ በመተኮሩ ብዙ ነገሮች እየተበላሹ ነው፡፡ በየቦታው ነውጠኝነት ነግሦ አገር የምትታመሰው ጠንካራ ተቋማት ባለመኖራቸው ነው፡፡

የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ኖሮት ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ማድረግ የሚቻለው ፓርላማው፣ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው ሲናበቡና ኃላፊነታቸውን በሕጉ መሠረት ሲወጡ ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም ሥርዓት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ሲንጠላጠል ተስፋ አይኖረውም፡፡ ሥርዓት አስተማማኝና ዘለቄታዊ መሆን የሚችለው ተቋማዊ ሲሆን ነው፡፡ ተቋማዊ መሆን ማለት በሕግ ብቻ የሚመራ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያገለግሉ ተቋማትን ማደራጀት ነው፡፡ ተቋማቱ መደራጀት ያለባቸው በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን በአግባቡ እንዲወጡ ነው፡፡ ተቋማቱ በዚህ መንገድ ሲደራጁ የመንግሥት ሥራ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት ይከናወናል፡፡ ኢትዮጵያዊያን መብታቸውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውንም ይረዳሉ፡፡ ሕገወጥ አሠራሮች ተቀባይነት ያጣሉ፡፡ ከሕግ ጋር የሚቃረኑ ብልሹ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ የብሔር፣ የእምነት፣ የፖለቲካ ወይም መሰል ልዩነቶች የቅራኔ ምንጭ አይሆኑም፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዕውቀቱና በጉልበቱ አገሩን ለመገንባት ዝግጁ ይሆናል፡፡ መንግሥት ለተቋማት ግንባታና ለሕጋዊ ማዕቀፎች ትኩረት ካልሰጠ ግን፣ ውጤቱ አሉታዊ እንደሚሆን መጠራጠር አይገባም፡፡ ተቋማት በጠንካራና በብቁ አመራሮች ሳይደራጁ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መነጋገር አይቻልም፡፡ አገር ከምንም ነገር በላይ በመሆኗ ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ይሰጥ፡፡ ለብልሹ አሠራሮች በር የሚከፍቱ ልማዳዊ ድርጊቶች ይወገዱ፡፡ በዚህም ምክንያት ሥርዓተ አልበኝነት እየነገሠ አገርና ሕዝብ አይታመሱ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ልማዳዊ አሠራሮች በመለመዳቸው ለተቋማት ግንባታና ለሕጋዊ ማዕቀፎች የሚሰጠው ትኩረት በጣም አናሳ ነው፡፡ ልማዳዊ ድርጊቶችን የሚሽሩ ሐሳቦችን ይዘው የሚቀርቡ እንደ ጠላት ይታያሉ፡፡ ደፈር ብለው ሐሳቦቻቸውን ማቅረብ ሲጀምሩ በሐሜትና በአሉባልታ ይከበባሉ፡፡ አገር የምታድገው በአዳዲስ አስተሳሰቦችና ጊዜውን በሚመጥኑ የድርጊት መርሐ ግብሮች በሚመሩ ተቋማት ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ተቋማት በአብዛኛው ይቻላል ልማዳዊ አሠራሮች ሰፍነውባቸዋል፡፡ ተቋማቱን የሚመሩት ደግሞ ለአዳዲስ አስተሳሰቦች ዕውቅና እንሰጣለን ቢሉም ከልባቸው አይደለም፡፡ ያቀዱት ሳይሳካ ሲቀር በአፈጻጸም ድክመት ያሳብባሉ፡፡ የአፈጻጸም ድክመት የሚመጣው እኮ ተቋማት በዘመናዊ አመራር ስለማይደራጁና ከልማድ እስረኝነት ስለማይላቀቁ ነው፡፡ ከግለሰብ እስከ ተቋም ለለውጥ ለመነሳት ዝግጁ መሆን የሚቻለው፣ ከልማድ እስረኝነት ራስን ለማላቀቅ ቁርጠኝነት ሲኖር ነው፡፡ በኋላቀር አሠራሮች ተተብትቦ ስለዕድገት በፍፁም መነጋገር አይቻልም፡፡ አገሪቱ አሁን የሚያስፈልጋት መሠረታዊ ለውጥ ነው ከተባለ፣ ተቋማትን ከልማዳዊ አሠራሮች በፍጥነት ማላቀቅ ይገባል፡፡ ግለሰቦች ቤት አዳይ፣ መሬት ሰጪ፣ ብድር ፈቃጅ፣ ከቀረጥ ነፃ ሸላሚና የሁሉም ነገር አዛዥ ሲሆኑ፣ ሥርዓቱ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ወይም ዘመነ መሣፍንት ውስጥ እንዳለ ለመረዳት ያዳግታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግላጭ ዜጎችን በማንነታቸው ብቻ እየለዩ የሚፈጁ ሲበራከቱ ደግሞ ያስደነግጣል፡፡

የተቋማት ተጠናክሮ መውጣት መሪዎች አገርን በሥርዓት እንዲመሩ፣ ሥልጣናቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖርበት፣ በግል ፍላጎታቸው ሳይሆን በሕግ በተሰጣቸው ኃላፊነት ብቻ እንዲመሩ ይረዳል፡፡ አለበለዚያ ግለሰቦች የነገሡበት የእንዳሻህ አሠራር እየሰፈነ ሕዝብ ሲቆጣ እንቢታ ይከተላል፡፡ ለምሳሌ በልማዳዊ አሠራር የተተበተበ ልማታዊ ነኝ የሚል የመንግሥት ፖሊሲ ሕዝብ ላይ ተጭኖ፣ ባለሥልጣናት ግን ጭልጥ ባለ ካፒታሊስታዊ የገበያ ኢኮኖሚአቋራጭ መንገድ ራሳቸውንና ቢጤዎቻቸውን በሀብት ሲያደልቡ ተስተውለዋል፡፡ ሌብነትና ዝርፊያ ከሚታሰበው በላይ ሆኖ ኢትዮጵያ መተንፈስ እስኪያቅታት ድረስ ዕዳ ውስጥ ስትዘፈቅ፣ እዚህ ግባ የሚባሉ ተቋማት ባለመኖራቸው ምክንያት ቁጥጥር ጠፍቶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ በልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ፍልስፍና የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ መጠን ያለው የአገር ሀብት እያገላበጡ፣ በአገር ላይ የደረሰው ውድመት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት የጎደለውና ተጠያቂነት ስሌለበት የአገር ሀብት እንዴት እየባከነ እንደነበረ፣ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን ተከታታይ ዓመታዊ ሪፖርቶች ማገላበጥ በቂ ነው፡፡ ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ መፍጠር የሚችሉ ተቋማት ስለሌሉ አገር የግለሰቦች መጫወቻ ሆናለች፡፡ ይህ የውድቀት ማሳያ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ካለፈው ስህተት በመማር ለተቋማት ግንባታና ጥንካሬ ትኩረት መስጠት የግድ መሆን አለበት፡፡ ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ካልተደረገ በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ አሁንም ምልክቶቹ እየታዩ ናቸው፡፡

የመንግሥታዊ ተቋማት ተጠናክሮ መውጣት አገርን በሥርዓት ለመምራት፣ የመንግሥት ሥልጣንን በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ ለማከናወን፣ የሕግ የበላይነት ለማስፈን፣ የሕዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈን፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ለመፍጠር፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር፣ ሕገወጥነትን ለማስወገድ፣ ወዘተ ይጠቅማል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ተማምነው የአገር ግንባታው መቀጠል የሚችለው የተቋማት የተበላሸ ገጽታ ሲለወጥ ብቻ ነው፡፡ ገጽታቸውን ለመለወጥ ደግሞ በአመራርነት የሚመደቡ ግለሰቦች በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ የትምህርት ዝግጅቱና ልምዱ እንዳለ ሆኖ፣ በሥነ ምግባር ጥራታቸው ምርጥ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንን ከያሉበት ማፈላለግ ተገቢ ነው፡፡ ራሳቸውን ችለው የማይቆሙ፣ ብሔርን፣ ፆታን፣ እምነትን ወይም ሌላ መሥፈርትን ብቻ የሚታከኩ ተሿሚዎች ለአገር ያላቸው ፋይዳ እምብዛም ነው፡፡ ተሿሚዎች ከሌብነት የፀዱ፣ ካላስፈላጊ ድርጊቶች ራሳቸውን ያቀቡና በራሳቸው የሚተማመኑ ከሆኑ ተቋማቱም ያንን መንፈስ ይላበሳሉ፡፡ በአስመሳዮችና በአድርባዮች የሚመሩ ተቋማት ግን ዘቅጠው ይቀራሉ፡፡ ራሳቸውን ችለው መቆም ስለማይችሉ የደላላ መጫወቻ ይሆናሉ፡፡ አሁንም አገር የሥርዓተ አልበኞች መቀለጃ እየሆነች ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ መንግሥታዊ ተቋማት በደመነፍስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በአዋጅ ተቋቁመው ሥልጣንና ኃላፊነታቸው በግልጽ ቢደነገግም፣ ብዙዎቹ በመፈክሮች ከማጌጥ ውጪ እዚህ ግባ የሚባል አፈጻጸም የላቸውም፡፡ በፓርቲ ፖለቲካ መሥፈርት ብቻ ተሹመው የሚመሯቸው ግለሰቦችም በአንድ በኩል ከፍተኛ በሆነ የአቅም ማነስ፣ በሌላ በኩል የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ሲያባርሩ ስለሚውሉ ተቋማቱ ውርጭ እንደመታው የስንዴ ቡቃያ ጠውልገዋል፡፡ ሹመት፣ ዕድገት፣ ዝውውር፣ የትምህርት ዕድልና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የሚገኙት በትውውቅና በኔትወርክ በመሆኑ፣ አንገታቸውን ደፍተው ሥራቸውን የሚያከናውኑ ንፁኃን እንደ አሮጌ ዕቃ ተጥለዋል፡፡ ተቋማቱንም የተመሰከረላቸው ባለሙያዎች ጥለዋቸው ሄደዋል፡፡ የፓርቲ አባልነትና የቡድን መሳሳብ የበረታባቸው ብዙዎቹ ተቋማት በባለሙያዎች ድርቅ የተመቱ ስለሆኑ፣ እንኳን ለኃላፊነት ለምንም ነገር ብቁ ያልሆኑ ግለሰቦች መጫወቻ ሆነዋል፡፡ በዚህና በመሰል ምክንያቶች የተሽመደመዱ ተቋማት በብቁ አመራሮችና ባለሙያዎች ተደራጅተው በፍጥነት ቅርፃቸውንና ይዘታቸውን ካልለወጡ፣ በነበሩበት መቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ የተቋማቱን አጠቃላይ ገጽታ ለመቀየር ግን የተለመደው አካሄድ አያዋጣም፡፡ ከላይ እስከ ታች ያሉት መንግሥታዊ መዋቅሮች ከሕገወጥ አሠራሮች የሚላቀቁት፣ ለተቋማት ግንባታና ለሕጋዊ አሠራሮች ዝግጁ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ የተቋማት ሪፎርም ቅርፅ ላይ ሳይሆን ይዘት ለውጥ ላይ ያተኩር፡፡ ለተቋማት ግንባታ ትኩረት የማይሰጥ አሠራር አያዛልቅም የሚባለው ለዚህ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...