ውይይቱን የሁለቱ ክልሎች ፕሬዚዳንቶች መርተውታል
መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ ሰዴቃ ቀበሌ ‹‹ኦነግ ሸኔ›› በሚባል ታጣቂ ቡድን በግፍ የተጨፈጨፉት ንፁኃን ዜጎችን አስመልክቶ፣ የሕዝብ ቁጣ በማስነሳቱና በተለይ የአማራ ክልል መንግሥት ለፌዴራል መንግሥት ጠንከር ያለ ጥያቄ በማንሳቱ ጭምር፣ ማክሰኞ መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ለውይይት ተቀምጠዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ በድረ ገጹ እንዳስታወቀው፣ በሁለቱም ክልሎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በንፁኃን ዜጎች ላይ ሞትና መፈናቀል ደርሷል፡፡ በሁለቱም ክልሎች ላይ በተደጋጋሚ በሚከሰት የፀጥታ ችግር፣ ጥቃት እየደረሰባቸው የሚገኙት ንፁኃን ዜጎች በመሆናቸው፣ አመራሮቹ በትብብር በመሥራት ችግሮቹን መቅረፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ገልጿል፡፡
ውይይቱ በአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አገኘሁ ተሻገርና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደሚመራ ጠቁሞ፣ በውይይቱ ላይ ትኩረት የተሰጠው በሁለቱም ክልሎች ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሞትና መፈናቀል ማስቀረት መሆኑን አውስተዋል፡፡
የግጭት ጠንሳሾችና ተዋናዮች ላይ አስፈላጊውን ዕርምጃ ከመውሰድ በተጨማሪ፣ በተከሰቱ ግጭቶች ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ፍትሕ እንዲያኙና በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠሩ ለሕግ እንዲቀርቡ ለማድረግ፣ በትብብር መሥራት እንዳለበት አቋም ወስደዋል፡፡
የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው በመመለስ ማቋቋምና በክልሎች ዘላቂ ሰላም ለማሥፈን መሠራት እንዳለበት አመራሮቹ መምከራቸውን ብልፅግና አብራርቷል፡፡
አማራና ኦሮሞ ወንድማማች ሕዝቦች፣ ዘመን ተሻጋሪ ትስስርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር፣ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን በተቀናጀ ሁኔታ መከላከል አስፈላጊ ስለመሆኑም መምከራቸውን አክሏል፡፡
በውይይቱ የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጋራ ልማትና ሰላም ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ነው ተብሎ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ቢዘገብም፣ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በተደጋጋሚ የተፈጸሙ ግድያዎችና ውድመቶች ከፍተኛ መቃቃር በመፍጠራቸውና ለአገር ህልውናም አሥጊ በመሆናቸው፣ የችግሮቹን ምንጭ ከመነሻቸው በመለየት ላጋጠሙ ችግሮች የጋራ መፍትሔ መፈለግ ግድ በመሆኑ፣ ውይይቱ መካሄዱን ከምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡