አዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ከፀደቀ በኋላ፣ አዳዲስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተመዝጋቢዎች ቁጥር በ500 ፐርሰንት መጨመሩን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው የማኅበራቱ ቁጥር ከፍ ማለቱን የገለጸው ማክሰኞ መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩበት ዓውደ ርዕይ ሲከፈት ነው፡፡
በዚህም መሠረት 3,200 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥራቸውን በማከናወን እንደሚገኙ፣ 1,800 ድርጅቶች ዳግም መመዝገባቸውን 1,400 እንደ አዲስ ሥራ ላይ መሆናቸውን የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማኅበራትን ቁጥራቸው ከፍ በማድረግ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ቁልፍ ሚና እንዳላቸው የገለጹት አቶ ፋሲካው፣ በኤጀንሲው በአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ መሠረት 14 ሺሕ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ 150 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተሳተፉበት ዓውደ ርዕይ በኦሮሞ ባህል ማዕከል እየተከናወነ ይገኛል፡፡
አገር በቀልና የውጭ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥራዎቻቸውን ለኅብረተሰቡ የሚያሳዩበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፋሲካው፣ ዓውደ ርዕዩን መንግሥት፣ የግል ዘርፍና ማኅበራቱ በጋራ ያዘጋጁት መሆኑን ተጠቁሟል፡፡
አቶ ፋሲካው እንደተናገሩት፣ የዓውደ ርዕዩ ዓላማ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚሠሩትን ለኅብረተሰቡ ለማሳወቅና ሌሎች በበጎ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ማኅበራትን ለማብዛት ያለመ ነው፡፡
ረቡዕ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ኤጀንሲውና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርብበት መንግሥትና ባለድርሻ አካላት፣ ዘርፉን ለማሳደግ ማድረግ ስላለባቸው ተግባራት የሚወያዩበት መድረክ መሆኑን አቶ ፋሲካው ተናግረዋል፡፡
ከመጋቢት 28 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኦሮሞ ባህል ማዕከል እየተከናወነ የሚገኘው ዓውደ ርዕይ በየዓመቱ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርድቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዳልቦ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ዓውደ ርዕዩን አስጀምረዋል፡፡