የአገሪቱ ግብርና ዘመናዊ ባለመሆኑ ምክንያት በአምራች ዘርፍ የሚገኙ የቄራ ድርጅቶች፣ ለዕርድ የሚሆኑ በቂ የእንስሳት አቅርቦት እጥረት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ስድስት የማምረቻ ተቋማትን ችግሮች ለመቅረፍ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የግብርና ሚኒስቴርን ወክለው የተሳተፉት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የእንሰሳት ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)፣ ለአምራች ዘርፉ መጎልበት የግብርና ዘርፍ ቁልፍ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የግብርናና የአምራች ዘርፎችን ትስስሮች ለማጠናከር ግብርና ማዘመን አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ያስረዱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በአሁኑ ወቅት ግብርናው ዘመናዊ ባለመሆኑ የተነሳ፣ የቄራ ድርጅቶች ለዕርድ የሚሆን በቂ የእንስሳት አቅርቦት እያገኙ አለመሆናቸውን፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በቀጣይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
በሁዋጃያን፣ አርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ፣ ኩሞቶክ፣ ቢኤምቲ ኬብል፣ ዴምካና አላና ቄራ ፋብሪካ በተባሉት የማምረቻ ተቋማት የተደረገውን ጉብኝት የመሩት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አሉታዊ ተፅዕኖ ካሳደረባቸው ዘርፎች አንዱ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ዘርፍ ከውድቀት ለመታደግ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቅንጅት እየሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የአምራች ዘርፉን ማጎልበት አገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ አማራጭ የሌለው መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ዘርፉን ለማጎልበት የሚያግዝ ጠንካራ ፖሊሲ ለመቅረፅ ሚኒስቴሩ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ፖሊሲው ከአሁን ቀደም በማምረቻ ተቋማት ይስተዋሉ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡
ሌላዋ የጉብኝቱ ተሳታፊ የነበሩት የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ወ/ሮ ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው፣ ኮቪድ-19 ለማምረቻ ተቋማት ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን ትልቅ ተግዳሮት ለመቅረፍ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በይፋዊ የትዊተር ገጹ አስታውቋል፡፡
መንግሥት በልማት የዕቅዱ የመጀመሪያ አምስት ዓመታት (2013-2017) የግብርና ምርቶችን በጥሬ ዕቃነት በሚጠቀም ማኑፋክቸሪንግ ላይ በማተኮር፣ አስተማማኝ የኢንዱስትሪ መሠረት ለመገንባት እንደሚሠራ በልማት ዕቅዱ ሰነድ ላይ አስታውቋል። ከዚህ አኳያ በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ከፍተኛ ፍላጎት ባላቸው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ፣ በተለይም በምግብና ተያያዥ ምርቶች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ፣ በተጨማሪም በአገር ውስጥ ሀብትና አቅም ሊመረቱ የሚችሉ እንደ አግሮ ፕሮሰሲንግ በተለይም ለምግብ፣ መጠጥ፣ ስኳር፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ላይ ትኩረት በመስጠት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱ ተገልጿል።